ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ በሰማዕትነት ስለተሠዉ ኢትዮጵያውያን የቅዱስነታቸው መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ግፉዓን ይትማሠጥዋ ለመንግሥተ ሰማያት በሃይማኖታቸው ምክንያት ግፍ የሚደርስባቸው መንግሥተ ሰማያትን ይናጠቋታል፡፡ (ማቴ. 11፣12)

በሰሜን አፍሪካ ሊቢያ ውስጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀልን በተመለከተ ከኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በድጋሚ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ፡፡ ራሱን አይ ኤስ እያለ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰሜን አፍራካ በሊቢያ ውስጥ በሜዲትራንያን ባሕር አካባቢ በንጹሓን የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ላይ ግፍ በተሞላበት አሠቃቂ ሁኔታ ግድያ እንደፈጸመ ታውቆአል፡፡ በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው የሁሉም ሃይማኖቶች ተልእኮ ሰውን ማዳን እንጂ ሰውን መግደል እንዳይደለ ይታመናል፡፡

ይሁን እንጂ በማንኛውም ሃይማኖት ተቀባይነት የሌለው ንጹሓን ዜጎችን በሃይማኖት ምክንያት በአሠቃቂ ግድያ የመግደል ወንጀል በዓለማችን መታየት ከጀመረ ሰነባብቶአል፡፡ ኢትዮያውያን ወገኖቻችንም በተለያየ ጊዜና በተለያየ አካባቢ የዚህ ዐይነቱ ግድያ ሰለባ መሆናቸውን አልቀረም፡፡ ከዚህ አንጻር በዚህ ሰሙን በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች በሆኑት ልጆቻችን ላይ የተፈጸመው አሠቃቂ ግድያ ከምንም ጊዜ በላይ ቤተ ክርስቲያናችንን ያሳዘነና ያሳሰበ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡

በመሆኑም የኢትዮያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተፈጸመው ድርጊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የዓለም ሃይማኖቶች ላይ የተቃጣ የወንጀል ተግባር መሆኑን በማመን መላው የሀገራችን ሕዝቦችና የሃይማኖት ተቅዋማት እንደዚሁም መላው የዓለም መንግሥታትና ማኅበረ ሰብ ይህንን ድርጊት በጽኑ ከመቃወምና ከማውገዝ በተጨማሪ ትርጒም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ፈጣንና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያፈላልግ እየጠየቀ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቶአል፡፡

1. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተከታይ ልጆችዋ ላይ በአይ ኤስ አሸባሪዎች የተፈጸመው አሠቃቂ ግድያ ደረቅ የወንጀል ተግባር በመሆኑ በጽኑ ታወግዛለች፤

2. በሁሉም እንደሚታወቀውና በተግባርም እንደታየው የአሸባሪዎች የጥፋት ዕልቂት ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ጾታንና አካባቢን ሳይለይ በአጠቃላይ በሰው ዘር ላይ የዘመተ የጥፋት ተልእኮ ስለሆነ የዓለም መንግሥታትና በአጠቃላይ የዓለም ማኅበረ ሰብ፣ እንደዚሁም ሁሉ የሃይማኖት መሪዎችና የፀረ ሽብር ተቅዋማት ለዓለማችን የሰላም መረጋገጥና ለሰው ልጆች በሕይወት የመኖር መብት መከበር ተባብረው እንዲሠሩ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ትጠይቃለች፤

3. የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ዐቀፍ ማኅበረ ሰብና ከየሀገሩ መንግሥታት ጋር በመሆን የሚያካሂደውን የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል የዜጎች ሕይወት በአሸባሪዎች እንዳይቀጠፍ ከእስከ አሁኑ በበለጠ እንዲንቀሳቀስ ቤተ ክርስቲያናችን ትጠይቃለች፤ በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ከመንግሥትና ከሕዝብ ጎን ተሰልፋ የሚጠበቅባትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆንዋን ታረጋግጣለች፣

4. የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሃይማኖትና በሌላው ሁሉ ሳንለያይ ከጥንት ጀምሮ ጠብቀን ያቆየነውን በኅብረት፣ በአንድነት፣ በፍቅርና በመቻቻል የመኖር ጸጋ አሁንም አጥብቀን በመያዝ የጋራ ጠላት የሆነውን ግብረ ሽብር የመመከት ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እናሳስባለን፡፡

5. የመዋች ቤተ ሰቦች የሆናችሁ ወገኖቻችን ሁሉ በዚህ ግፍ የተሞላበት ጭካኔ የተገደሉት ልጆቻችን በዚህ ዓለም የመኖር መብታቸው ባጭሩ ቢቀጭም ጌታችን የተገፉ መንግሥተ ሰማያትን ይናጠቋታል ማለትም ይወርሱአታል ባለው አምላካዊ ቃል እግዚብሔር ዕንባቸውን አብሶ በመንግሥቱ የሚቀበላቸው መሆኑን ዐውቃችሁ፣ እንደዚሁም ልጆቻችን «ወኩን መሃይምነ እስከ ለሞት ወእሁበከ አክሊለ ሕይወት – እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፤ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሀለሁ፤» (ራእ. 210) ያለውን የሐዋርያው ቃል ጠብቀው ሃይማኖታችንን አንክድም በማለት የሃይማኖት ሰማዕትነትን የተቀበሉ የሃይማኖት መስተጋድላን ስለሆኑ የጀግና እናት አታለቅስም እንደተባለው የልጆቻችሁ ሰማዕትነት በእግዚአብሔር መንግሥት ታላቅ ዋጋ ስላላቸው በዚህ ከኀዘናችሁ እንድትጽናኑ ቤተ ክርስቲያን ታሳስባለች፡፡

6. ቅዱስ ሲኖዶስ በሃይማኖታቸው ምክንያት ለተሠዉ ክርስቲያኖች ሊሰጥ የሚገባውን የሰማዕትነት ክብር በቀኖናው መሠረት መፈጸም ይቻል ዘንድ በአይ ኤስ አሸባሪ ቡድን በግፍ የተገደሉት ልጆቻችን ቤተ ሰብ የሆናችሁ ሁሉ የመዋቾቹን ስመ ክርስትና፣ ፎቶና ሙሉ አድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በተቻለ መጠን በፍጥነት እንድታቀርቡ ቤተ ክርስቲያን ታሳስባለች፡፡

7. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ከመውጣት፣ አስተማማኝ የሕይወትና የንብረት ዋስትና ወደሌለበት ሀገር ከመሄድ ተቈጥቦ በሀገሩ ውስጥ ሠርቶ ኑሮውን እንዲመራ ቤተ ክርስቲያን በአጽንዖት ትመክራለች፤

8. ቅዱስ ሲኖዶስ በየትኛውም አካባቢ የሚገኙትን ወገኖቻችንና የቤተ ክርስቲያን ልጆቻችን ከመሰል ጥቃት ለመታደግ እንዲቻል ከመንግሥት ጋር በቅርበት የሚሠራ ዐቢይ ኮሚቴ በአስቸኳይ የሚያቋቁም መሆኑን ይገልጻል፤

9. ከነገ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለ7 ቀናት ያህል በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በግፍ ለተገደሉት ወገኖች ጸሎተ ፍትሐት፣ ለሀገራችንና በአጠቃላይ ለዓለሙ ሁሉ ሰላም መጠበቅ፣ ለሰው ልጆች በሕይወት የመኖር መብት መከበር ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡

ወስብሐት ለእግዚብሔር እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!