ሚያዝያ 11 ቀን 2012 ዓ.ም የበዓለ የትንሣኤ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤ በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤ በእርሱ ያመኑ ሕሙማንን ያድን ዘንድ የታመመው የሞተውና ሞትን ድል አድርጎ የተነሣው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!

“ሐመ ወሞተ ወተቀብረ ወተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት ዕለት
ታመመ፣ ሞተ፣ተቀበረ፣ በሦተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ። ”
(1ኛቆሮ 15፥3-4)

የክርስቲያኖች መሠረተ ሃይማኖት ወልደ እግዚአብሔር የሆነው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛና ስለ ድኅነታችን ሲል በለበሰው ሥጋ ታመመ፣ ሞተ፣ተቀበረ፣ በሦስተኛውም ቀን ሞትን ድል አድርጎ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሣ የሚለው ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሁሉ ጸዋትወ መከራ የተቀበለው ያለ ምክንያት አልነበረም፤ እኛ ሰዎች በተከተልነው የተሳሳተ ምርጫ በነፍሳችንም ሆነ በሥጋችን ለጸና ሕመም ተጋልጠን ስለነበረ ለሕመም የተጋለጠውን ሰብኣዊ ባሕርያችን በተዋሕዶ የራሱ ገንዘብ አድርጎ በሕማሙ የሕመማችን ቤዛ በመሆን ሊያድነን ነው፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ ከኀጢአት በቀር ሁለንተና ሰብኣዊ ባሕርያችንን በድንግል ማርያም ማሕፀን ተዋሕዶ ሰው ሆኖአል፤ በሠላሣ ዓመቱ ከተጠመቀ በኋላም ለሦስት ዓመታት ያህል ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን አስተምሮአል፤ ሕሙማንን ፈውሶአል፤ ሙታንንም አንሥቶአል፤ ይህ አምላካዊ ኀይል በነፍስም በሥጋም ሊያድነን የመጣ እውነተኛ መድኀኒት እሱ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነበረ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የታመሙትን በማዳን፣ በኀጢአት የሞቱትን ኀጢአታቸውን ይቅር በማለት፣ በሞትና በመቃብር የተያዙትን ከሞት በማንሣት፣ ፍጹም አዳኝነቱን ለዓለም ካሳወቀ በኋላ፣ የቤዛነታችን መሥዋዕት ለመሆን በፈቃዱ በፍጡራን እጅ ብዙ መከራን በመቀበል ታመመ፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕሙማንን ያድን ዘንድ መታመሙ አንድ የሚያስገነዝበን ታላቅ ነገር አለ፤ እሱም የሰዎችን መታመም የማይወድና የማይፈቅድ መሆኑ ነው፤ ጌታችን የሰዎች መታመም የማይገደው አምላክ ቢሆን ኖሮ ለሕሙማን ብሎ እስከ መሰቀል ድረስ ደርሶ መከራ ባልተቀበለ ነበር፡፡ ነገር ግን “ሐመ ከመ ሕሙማነ ያድኅን እለ ተወከሉ በላዕሌሁ፤ በእሱ የታመኑትን ያድን ዘንድ ታመመ” እያሉ መጻሕፍት እንደሚነግሩን ለሕሙማን የተሟላ ድኅነትን ያድል ዘንድ እስከ ሞት ድረስ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቶአል፡፡ በመሆኑም በሕማሙ ሕመማችንን፣ በሞቱ ሞታችንን፣ በመቃብሩ ሙስና መቃብርን አስወግዶ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አብሥሮናል፤ በዚህ የጌታችን ቤዛነት ዕዳችን ሁሉ ከላያችን ላይ ስለተነሣልን በትንሣኤው ላመን ሁሉ የድኅነት ሽልማታችን እሱም ፍጹም መዳናችን ለጌታ ቀን ተዘጋጅቶልን በፊታችን ይጠብቀናል፤ በዚያን ጊዜ በእርሱ ሕመም ሕመማችን ጠፍቶ፣ በእርሱ ሞት ሞታችን ተሸንፎ፣ በእርሱ መቃብር መቃብራችን ባዶ ሆኖ በክብር እንነሣለን፤ በዚያን ጊዜ እኛም እንደ እሱ የማይታመም፣ የማይሞትና መቃብር የማይነካው አካል ተጐናጽፈን ከእርሱ ጋር ፍጻሜ በሌለው ሕይወት በመንግሥቱ እንኖራለን፡፡

በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተጠብቆልን ያለውን ፍጹምና ሁለንተናዊ ድኅነት በጌታ ቀን እስክንረከብ ድረስ በዚህ ዓለም ባለው ምድራዊ ሕይወታችን ሥጋዊ ሕመም፣ሞተ ሥጋና ለጊዜውም ቢሆን ርደተ መቃብር አይቀርልንም ፡፡ ይህም በመሆኑ በየጊዜው በልዩ ልዩ በሽታ እንታመማለን፣ እንሠቃያለን፣ በመከራም እናልፋለን፣ ነገር ግን ይህ ሁሉ በእኛ ላይ እንዲሆን የእግዚአብሔር ፈቃድና ፍላጎት ነው ወይ? ካልን የመጽሐፍ ቅዱስ መልስ አይደለም የሚል ነው፤ ሕሙማንን ለማዳን የታመመው አምላክ ሕሙማን በልዩ ልዩ በሽታዎች እንዲጠቁ ይፈቅዳል ማለት የማይቻል ነው፤ ይሁን እንጂ ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጭ የሆነ በሽታ የለምና በሃይማኖታችን፣ በጸሎታችን እሱ በሰጠን አእምሮ ተጠቅመን እንድንከላከል ብቻ ሳይሆን በምንችለው ሁሉ እንድንመክተው እግዚአብሔር ይፈልጋል፡፡ ሁላችንም ከጌታችን አስተምህሮ እንደምንረዳው በእግዚአብሔር የተሰጡ ሕጎች በሙሉ ዐላማቸው ሰውን ለማዳን ብቻ ነው፤ ስቅለቱም፣ ሞቱም፣ ትንሣኤውም የተደረገው ለሰው ነው፤ ሰንበትም የተፈጠረችው ለሰው እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም፤ እንደዚሁም ሁሉ ጾሙ፣ ጸሎቱ፣ ሱባዔው የተፈጠረው ለሰው ነው፤ ሰው ከሌለ ጸሎቱም፣ ጾሙም፣ ሱባዔውም፣ ሃይማኖቱም ሳይቀር ሌላው ሁሉ የለም፤ ምክንያቱም ይህ ሁሉ የተፈጠረው ለሰው ነውና ሰው ከሌለ ለማን ተብሎ ይደረጋል፤ እግዚአብሔር መጀመሪያውኑ ሲፈጥረን በዚህ ዓለም እንደ ፈቃዱ ልንኖር እንጂ በአሠቃቂ በሽታ ተሠቃይተን ተዋርደንና የሚቀብረን አጥተን እንደቅጠል ረግፈን ልንቀር አይደለም፤ እውነት ነው እግዚአብሔር ይህንን አሠቃቂ የኮረና በሽታ በከሃሊነቱ አንድ ቀን ያስወግደዋል፤ ግን እኛስ በሰጠን አእምሮና ባለሙያዎቻችን በሚነግሩን (በሚሰጡን) ምክር ተጠቅመን የዓቅማችንን ያክል መከላከል የለብንም ወይ? ነው ጥያቄው፤ አዎ መከላከል አለብን እንዲያውም እግዚአብሔር ዕውቀቱን በፈቀደላቸው የጥበብ ባለሙያዎች ልጆቻችን ችግሩንና መፍትሔውን እየነገረን እያለ እግዚአብሔር ያውቃል እያልን ቸል የምንል ከሆነ ጌታችን እንደነገረን እግዚአብሔርን መፈታተን ነው የሚሆነው፤ ይህም ኀጢአትም ነው ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ምድራዊ ወኪል በሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት ምእመናን በቤታቸው ሆነው በመጸለይ የኮረና ቫይረሱን እንዲከላከሉ ያስተላለፈው ውሳኔ እንዲሁ ዝም ብሎ አይደለም፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ራስን የመጠበቅና የመከላከል ውሳኔ ያስተላለፈው፦
(1) እግዚአብሔር አንድ ሰው ስንኳ በጥንቃቄ ጉድለት እንዲጐዳ የማይፈቅድ መሆኑን ስለሚያውቅ፤
(2) አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በቤት ሆኖ መጸለይና መጾም ሱባዔንም መፈጸም የተፈቀደ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም እንደዚህ ያለ ችግር ሲያጋጥም “ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በሥውር ላለው አባትህ ጸልይ” የሚል የጌታችን ትእዛዝና ትምህርት መኖሩን ስለሚያውቅ፤
(3) ምእመናንም ሆኑ ካህናት እስካሉ ድረስ እግዚአብሔር ምሕረቱን በላከልን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ ላይ ሆነን መጸለይ፣ ማመስገንና ማስቀደስ፣ ማምለክና መቊረብ እንደሚቻል በመገንዘብ ነው፤
(4) ምእመናን ከሌሉ ሁሉንም እናጣለን ከሚል አባታዊ ርኅራኄና አርቆ አስተዋይነት በመነሣት እንደዚሁም በተሰጠን ሥልጣን ይህንን ነገር ለሕዝባችን ባናስታውቅ በእግዚአብሔርም በሥነ ምግባርም ከባድ ወቀሣና ተጠያቂነት እንደሚያስከትልብን በመረዳት ነው፡፡

ስለዚህ አሁንም ቢሆን ከቅዱስ ሲኖዶስ በተላለፈውና ለወደፊትም እንደ አስፈላጊነቱ በሚተላለፈው ሲኖዶሳዊ ብይን መሠረት በየቤታችሁ ሆናችሁ ከልብ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ በሽታውን እንድትከላከሉ፣ ለተቸገሩ ወገኖችም ባላችሁ ዐቅም ሁሉ እንድትረዱና እንድታግዙ በእግዚአብሔር ስም አደራችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም፤ በእርሱ የታመኑትን ሕሙማን ሊያድን፤ የታመመው፣ የሞተው፣ የተቀበረውና በሦተኛው ቀን ሞትን ድል ነሥቶ የትንሣኤውን የምሥራች ያሰማን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበሽታውን መጥፋትና መወገድ የምሥራች አሰምቶን የተለመደውን ሃይማኖታዊና ዕለታዊ ተግባራችንን በሰላም እንድናከናውን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ መልካም የትንሣኤ በዓል ያድርግልን፣

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ፣ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡