ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሊቢያ ሀገር በንጹሓን ወገኖች ላይ ስለተፈጸመው አሠቃቂ ግድያ ስለማውገዝ በቅዱስነታቸው የተሰጠ የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ/ም ከእኩለ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም ያሉ የዜና ማሰራጫዎች በሰሜን አፍሪካ በሊቢያ የሜዲትራንያን ባሕር ዳርቻ አካባቢ አይኤስ በተባለ አሸባሪ ቡድን በንጹሓን ወገኖች አሠቃቂ ግድያ እንደተፈጸመባቸው ዘግበዋል፡፡
ዘገባው ከምኑም ከምኑ የሌሉበት ንጹሓን ክርስቲያን ወጣቶች በታጠቁና ፍጹም ሰብኣዊነት በሌላቸው አሸባሪዎች ሲገደሉ የሚያሳየው ምስልም በመላው ዓለም እየታየ ይገኛል፡፡ አሠቃቂው ግድያ ስለተፈጸመባቸው ንጹሓን ወጣቶች ዜግነትና ማንነት ግልጽና አስተማማኝ የሆነ መረጃ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በበርካታ የዓለም ዜና ማሰራጫዎች ሲነገር እንደሚሰማው የዚህ የግፍ ወንጀል ሰለባዎች ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች መሆናቸውን የዜና ማሰራጫዎቹ አክለው እየገለጹ ነው፡፡
የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፈጣሪ የተሰጠች የማንኛውም የሰው ልጅ ሕይወት ኀላፊነት በማይሰማቸውና በእነርሱ ላይ ሊደረግ በማይፈቅዱ ምንም ዐይነት ሰብኣዊ ርኅራኄ በሌላቸው እንድትቀጠፍ ስለማትፈቅድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን አሠቃቂ ድርጊት በጽኑ ትቃወማለች፣ አጥብቃም ታወግዘዋለች፡፡
ስለዚህ የዚህ ግፍ ሰለባ የሆኑት ወገኖቻችን ማንነት ተረድተን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት መሠረት አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑና መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ተገንዝበው ሁኔታውን በትዕግሥት እንዲጠብቁ፤ እንደዚሁም የተፈጸመው የጭካኔ ተግባር የማንኛውም ሃይማኖት ተቋምና እምነት የማይወክል የአሸባሪዎች ተግባር መሆኑን ተገንዝበው ኢትዮጵያውያን የሆኑ ሁሉ እንደቀድሞው በአንድነት በማውገዝ የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች ኪሳራ እንጂ ምንም ዐይነት ትርፍ የማያገኙ መሆናቸውን በተግባር እንዲያሳዩዋቸው እናሳስባለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፡፡ አሜን።