መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ.ም፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የኮሮና ቫይረስ እንዳይስፋፋ ምእመናን በቤታቸው ሆነው እንዲጸልዩ መግለጫ ሰጠ፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የቆየውና በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ኢትዮጵያ የገባው የኮረና ቫይረስ በሽታ ዕለት ዕለት እየተስፋፋ ጥቂት የማይባሉ ወገኖቻችን በወርሽኙ መያዛቸው ታውቋል፡፡ በመሆኑም ይህ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋና በቀጣይም ሌሎች ወገኖቻችን እንዳይያዙ መከላከሉ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ቋሚ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ስብሰባ በማድረግ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የሕዝቡን ሁሉ ምሕላና ጸሎት፣ የካህናቱን አስተበቊዖት በርኀራኄው ሰምቶ፣ በቅዱሳኑ ቃልኪዳን፣ በወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም አማላጅነት ቍጣውን በምሕረቱ መዓቱን በትግዕሥቱ አሳልፎ ፍጹም ደኅንነትን እንደሚሰጠን እያመንን፡-
1. በአሁኑ ጊዜ እየደረሰ ያለው የወረርሽኝ በሽታን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች እየተሰጠ ያለውን የጤና አጠባበቅ ምክርና ትምህረት እንዲሁም በፍትሕ መንፈሳዊ እንደተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በማድረግ ወረርሽኑን ማስቆም እንዲቻል በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጣም በተወሰኑ ካህናት መንፈሳዊ አገልግሎቱ እንዲሰጥ ሌሎች ካህናትና ምእመናን ለጊዜው በየቤታቸው በጸሎት እንዲወሰኑ፣ በአገልግሎት ላይ ለሚገኙ አገልጋይ ካህናትም በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽረ ግቢ እንዲወሰኑ ሆኖ አስፈላጊው ሠርከ ኅብስት የምግብ አቅርቦት እንዲዘጋጅላቸው እንዲደረግ፣
2. በአሁኑ ጊዜ የወረርሽኙን ፍጥነት ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ በቀጣይ በበሽታው እየተያዙ ለሚመጡ ወገኖቻችን ማቆያ ቦታ ማዘጋጀቱ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር ከአዲስ አበባ ጀምሮ በመላው አህጉረ ስብከት የሚገኙ፡ (ሀ) መንፈሳዊ ኮሌጆች (ለ) የካህናት ማሠልጠኛዎች (ሐ) ዘመናውያን ት/ቤቶች አስፈላጊው ዝግጅት እንዲደረግላቸውና መሟላት የሚገባቸው ሁሉ ተሟልቶ ለሕሙማን ማቆያ እንዲውሉ ለማድረግ ወረርሽኙ እስከሚያበቃ ድረስ አገልግሎት መስጫ እንዲሆኑ የሚመለከተው አካል ተረክቦ እንዲያስተናግድባቸው ተወስኗል፡፡
3. በአሁኑ ጊዜ በወረርሽኙ ምክንያት መንግሥት ሕሙማንና የተቸገሩ አካላትን ለመርዳት እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ከመንበረ ፓትርያርክ ለጊዜው ብር3,000,000 (ሦስት ሚሊየን ብር) በመንግሥት ደረጃ ለተቋቋመው ርዳታ አሰባሳቢ በቤተ ክርስቲያናችን ስም እንዲሰጥ፣
4. በቤተ ክርስቲያናችን ሥር ለሚገኙ የሕጻናትና ማሳደጊያ ቦታዎች የሚገኙ ሕጻናትን እና ችግረኞችን በምግብና በንጽሕና መጠበቂያ መደጐም የሚያስፈልግበት ጊዜ በመሆኑ አስፈላጊው ርዳታ የማሰባሰብ ሥራ እንዲሠራና እንዲረዱ በቤተ ክርስቲያናችን ሥር በተቋቋመው ተስፋ ግብረ ኀይል በኩል የማስተባበሩ ሥራ እንዲሠራ፣
5. ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አሁን የያዝነውን የጾምና የጸሎት ጊዜ ምክንያት በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ቅዳሴውን በመምራትና በመባረክ መቆየታቸውን ቋሚ ሲኖዶስ ተገንዝቧል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ያለው ወረርሽኝ በእጅጉ እየተስፋፋ በመሆኑና የተለየ አባታዊ ጸሎትና ሱባኤ የሚያስፈልግ ሆኖ በመገኘቱ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ከዛሬ መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለዓለም ሰላምና ለሕዝቦች ደኅንነት ሲባል ለጊዜው ለብቻቸው በልዩ የጾምና የጸሎት የሱባኤ ጊዜ እንዲቆዩ ቋሚ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ዓለማችንንና ሀገራችን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን ለሕዝባችንም ምሕረትንና ፈውስን ይስጥልን !አሜን !