መጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. የዐብይ ጾም መግቢያ ቃለ ምዕዳንና ቡራክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፣ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣

እንኳን ለጌታችን፣ ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የ2ዐዐ5 ዓ.ም. መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“እብለክሙ በመንፈስ ሑሩ፤ ወፍትወተ ሥጋክሙ ኢትግበሩ
በመንፈስ ተመላለሱ እንጂ የሥጋችሁን ምኞት ከቶ አትፈጽሙ እላችኋለሁ”
(ገላ. 5፣16)

የሰው ልጅ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የተገኘ ፍጡር እንደመሆኑ በሥጋዊ ፍላጎቱ ሳይሸነፍ ራሱን ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ማስገዛት እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡ ከዚህም አንጻር በመንፈስ ተመላለሱ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ፤ ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና ይላል የእግዚአብሔር ቃል፡፡ ለእግዚአብሔር ሕግ መገዛት እስከተቻለ ድረስ ክፉዉንና በጎውን ለይቶ ማወቅ ስለማያዳግት በተቻለ መጠን በፊታችን ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም. በሚጀመረው በታላቁ ጾማችን በዐቢይ ጾም ወራት ጎጂ ከሆኑ ተግባራት ሁሉ መራቅ አለብን፤ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን የማዳን ሥራ ከመጀመሩ በፊት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በመጾም ድኅነተ ነፍስ እንዳስገኘልን ሁሉ እኛም ፈለጉን ተከትለን ጾም በመጾም ጥንካሬን አግኝተን ረቂቅ የሆነውን የዲያብሎስ ፈተና ማሸነፍ በሚያስችለን ቀጥተኛ መንገድ ለመጓዝ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ከዚህ አንጻር ለሥጋዊው አካላችን ጥንካሬ፣ ምግበ ሥጋ እንደሚያስፈልገው ሁሉ መንፈሳዊው ሕይወታችንም እንዲጠነክር መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልገዋል፡፡ ከጥንት ጀምሮ ወደ እግዚአብሔር ቅርበት የነበራቸው ቅዱሳን አበው በተሞክሮአቸው እንዳስተማሩንና ቅዱሳት መጻሕፍትም እንዳስረዱን መንፈሳዊ አካላችን የሚጠነክረው የሥጋዊ አካላችን ፍላጎት በጾም ኀይል እንዲደክም ስናደርግ ነው፡፡

ሰይጣንና ክፉ ተግባሩ በሰው ላይ ኀይል የሚያገኙበት ምክንያት እኛ ወደ ምግበ ሥጋ ስናዘነብል እንደሆነ በአዳምና በሔዋን የሆነውና በጌታችን ላይ የተቃጣው በምግበ ሥጋ የመፈተን ሙከራ ማስረጃዎቻችን ናቸው፤ የጾም መንፈሳዊ ጥቅም በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን በማያሻማ ሁኔታ ተረጋግጦአል፡፡ ጾም ማለት ቀጥተኛ የቃሉ ትርጒም መተው፣ ወይም እግዚአብሔር ከማይወደው ነገር ሁሉ መራቅ ማለት ነው፤ እንዲህ ከሆነ ከእንስሳትና የእንስሳት ውጤቶችን ጨምሮ ከሌሎች ፍላጎቶች ሁሉ በመራቅ ራሳችንን ተቈጣጥረን በፍጹም አእምሮአችን፣ በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ኀይላችን እግዚአብሔር አምላካችንን ልናመልክና ለእርሱ ፍጹም ታዛዦች መሆን ይጠበቅብናል ፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ሁል ጊዜ ለሀገርና ለኅብረተሰቡ የሚጠቅም መልካም ሥራን ከመሥራት በቀር ጒዳት የሚያደርሱ ተግባራትን ማራመድ ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡ በየአቅጣጫው የተዘረጋው የሀገሪቱ የልማት ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን እየተደረገ ያለውን ጥረት የምንመለከተው በታላቅ አድናቆት ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥረቱ አካል በመሆን ጥሪውን ተቀብላ የሚጠበቅባትን ድርሻ ስታበረክት የቈየች ቢሆንም፣ የልማት ፕሮጀክቱ እውን ሆኖ ውጤታማነቱን እስከሚያረጋግጥ ድረስ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታደርገው የተግባር ተሳትፎ ዘወትር ይቀጥላል፡፡ ተግባራችን ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ሊሆን የሚችለው ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ምጽዋትን፣ ትዕግሥትን፣ ፍቅርን፣ ስምምነትን፣ ትሕትናን፣ መረዳዳትን፣ መተዛዘንን ገንዘብ አድርገን የጾምን እንደሆነ ነው ፡፡

በጾም ወራት ልንፈጽማቸው የሚገቡን የትሩፋት ሥራዎች ብዙዎች ቢሆኑም በተለይ መሠረታዊ የሆነ የኑሮ ፍላጎት ላልተሟላላቸው ወገኖቻችን ማለትም፣ ልብስ ለሌላቸው ልብስ በማልበስ፤ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው የሚቻለንን በመለገስ፤ ማረፊያ ለሌላቸው መጠለያዎችን በመቀለስ ወገኖቻችንን መርዳት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የጾም ዋና ዐላማው ለእግዚአብሔር ቃል በሙሉ ኀይላችን በመታዘዝ መዘጋጀት ነውና እግዚአብሔር በቃሉ የነገረንን ሁሉ ከመፈጸም ጋር ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ግዴታችንን በመወጣት፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ መርሐ ግብራችንን በማፋጠን፣ መልካም የሆኑትን የልማት ሥራዎቻንን ሁሉ በማከናወን ወርኀ ጾሙን ልናሳልፍ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን መዋዕለ ጾሙን በሰላም እንዳስጀመረን ሱባዔውን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም እንዲያደርሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ አሜን፡፡