መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የርእሰ ዐውደ ዓመት ቃለ ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
በሕመም ምክንት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵውያት በሙሉ፤

የዘመናት ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ሁለት ሺሕ ዐሥራ ሁለት ዓመተ ምሕረት ወደ ዘመነ ማቴዎስ ሁለት ሺሕ ዐሥራ ሦስት ዓመተ ምሕረት በሰላም አደረሳችሁ።
«ተዘከርኩ ዓመተ ዓለም ወአንበብኩ
ዓመተ ዓለምን አሰብሁ፥ አነበብሁም፤»
(መዝ. 77፥5)

ሁሉም እንደሚገነዘበው ፍጡር የሆነ ሁሉ የዕድሜ ልክ አለው፤ ፍጡር የሆነ ሁሉ መነሻም፥ መገሥገሻም፥ መድረሻም አለው፤ ፍጡር የሆነ ሁሉ ከዚህ ውጭ አይደለም። መነሻም፥ መገሥገሻም፥ መድረሻም የሌለው አንድ ብቻ ነው፤ እሱም እግዚአብሔር ነው። ሌላው ፍጡር ግን መነሻውም፥ መድረሻውም፥ መገስገሻውም እግዚአብሔር ነው።

ስፍር ቍጥር ከሌላቸው ፍጡራን መካከል አንዱ ጊዜ ነው። እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አቈጣጠር ሳድሲት ተብላ ከምትታወቀው የመጨረሻዋ ደቃቅ የጊዜ ስሌት እስከ ዓመተ ዓለም ያለው ሰፊ የቊጥር ስሌት በተለያዩ ምዕዋዳት እየተሽከረከረ እንደሚኖር እንገነዘባለን። ይህ የጊዜ እሽክርክሪት በእግዚአብሔር ሕግና ቊጥጥር ሥር ያለ በመሆኑ ፍጡራን ሊቈጣጠሩት አይችሉም። ይሁን እንጂ ባይቈጣጠሩትም ሊጠቀሙበት ይችላሉ ብቻ ሳይሆን እንዲሠሩበት በእግዚአብሔር ታዘዋል። እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሲፈጥር ለፍጡራን ጥቅም እንጂ እንዲሁ ለከንቱ አልፈጠረም። እንደሌላው ሁሉ ጊዜም ሠርተን ልንጠቀምበት እንደተፈጠረ ተግባሩ ራሱ ምስክር ነው። በሰው የሚደርሱ ኪሳራዎች ሁሉ በተለያየ ስልት ሊተኩ ይችላሉ፤ የጊዜ ኪሳራ ግን መተካት አይቻልም። ያለው ብቸኛ አማራጭ ጊዜን ሳናባክን ጥቅም ላይ ማዋል ነው።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

የእግዚአብሔር ቃል ዓመተ ዓለምን እንድናስብ የሚያስተምረን ያለ ምክንያት አይደለም፤ ሰው በተፈጥሮ ዐዋቂ ሆኖ የተፈጠረ ቢሆንም ከተሞክሮ የሚወስደው ዕውቀት ከፍ ያለ እንደሆነ የሚያከራክር አይደለም። የተግባር ተሞክሮ የሚገኘው ደግሞ ከሚመጣው ዓመት ሳይሆን ካለፉት ዓመታት ነው። ስለሆነም እግዚአብሔር ዓመተ ዓለምን እንድናስብ የሚያዘን ካለፈው ዘመን ተሞክሮ ወስደን ድክመትን በጥንካሬ በመለወጥ በቍጭት ለተሻለ ሥራ እንድንነሣ ለማስቻል ነው። ከዚህ አንጻር ያለፈውን ዓመት ስንመዝነው በሀገራችን ብዙ ምስቅልቅል እንዲከሠት ምክንያቶች ሆነን መገኘታችን ይታያል።

የአማንያን ሀገር እንደሆነች ኮርተን በምንመሰክርላት ኢትዮጵያ አብያተ ሃይማኖት ሲቃጠሉ፥ አማንያን ሲገድሉ፥ ዜጎች በተለያየ ምክንያት አካላዊ፥ ሥነ ልቡናዊና ኢኮኖሚያዊ ጒዳት ሲደርስባቸው በሀገራቸው በሥጋትና በጭንቀት ሲኖሩ ተስተውሎአል። ይህ የተፈጸመው በሌሎች ባዕዳን ሳይሆን ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸምነው ኢሰብኣዊ ድርጊት በመሆኑ እጅግ የምናፍርበት ሆኖ ተገኝቶአል። በመሆኑም ይህንን ሁናቴ ለማስተካከል ባለፉት ወራት በተነሣው ግርግር የሞት፣ የአካል ጒዳትና የንብረት ውድመት ያጋጠማቸውን ወገኖች ለመርዳትና ለማቋቋም ቤተ ክርስቲያናችን በምታደርገው መጠነ ሰፊ ርብርብ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለዚህ ለተቀደሰው ዐላማ እጃችሁን በመዘርጋት እንድትተባበሩ ወቅታዊ መልእክታችን ነው ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በኢትዮጵያ ርእሰ ዐውደ ዓመት ቀን ቆመን አዲሱን ዓመት አንድ ብለን ስንጀምር ያለፈውን ዓመት ላፍታ ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል። ቀጥሎም ባለፈው ዓመት የተከሠቱትን ድክመቶች በአዲሱ ዓመት ላንደግማቸው ቊርጥ ውሳኔ አሳልፈን ወደ ሥራ መግባት ይገባናል። በአዲሱ ዓመት አብያተ ሃይማኖት የማይቃጠሉባትና የማይደፈሩባት፥ ዜጎች በወገኖቻቸው የማይሞቱባት፥ የማይፈናቀሉባትና የማይሠጉባት ሀገር ለማረጋገጥ እያንዳንዱ ዜጋ ቃል ኪዳን መግባት አለበት። ይህ እውን ሊሆን የሚችለው አስተማማኝ ሰላም ሲኖር ነው። ይህ ዐይነቱ አስተማማኝ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስለ ሰላም፥ ስለ ሀገር አንድነት፥ ስለ ዜጎች እኩልነትና ስለጋራ ጥቅም አንድ ላይ ሆነው በጥልቀት በመመካከር በሚፈጥሩት ሀገራዊ መግባባት እንደሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ መገንዘብ አለባቸው።ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዚሁ ዙሪያ በአዲሱ ዓመት በአጽንዖት እንዲያስቡበት እንመክራለን። የእልክና የበቀል አመለካከት ሀገራችንን ዋጋ እንዳያስከፍላት መጠንቀቅ አለብን።

በመጨረሻም፤ በአዲሱ ዓመት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭም ለሚገኙት ለመላው ኢትዮጵያውያን የምናስተላልፈው ጽኑዕ መልእክት፦ ግጭት መፍጠር የተሸናፊነት እንጂ የአሸናፊነት ፍኖት አለመሆኑ፥ በአንጻሩ ደግሞ በክብ ጠረጴዛ ተወያይቶ ችግርን መፍታት ትልቁ ድል እንደሆነ ግንዛቤ ተወስዶ በአዲሱ ዓመት ሁሉም ወገኖች ለሰላም መስፈን ዝግጁ እንዲሆኑ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። አዲሱ ዘመን የሰላም፥ የልማትና የአንድነት ዘመን ያድርግልን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤ ይቀድስ።ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን።