መስከረም 1 ቀን የ2008 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤ በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤ የዘመናት ፈጣሪ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ያለፈውን ዓመት በሰላም አስፈጽሞ እንኳን ለአዲሱ የሁለት ሺሕ ስምንት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አደረሰችሁ!!
‹‹ወኀሊ ዓመተ ለትውልደ ትውልድ
የብዙ ትውልድን ዓመታት አስብ።››
(ዘዳ. 32፥7)፡፡
የሁሉም አስገኝና ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን ከፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል አንድ ስንኳ ጥቅም የለሽ የሆነ ፍጥረት አይገኝም፡፡ ፍጥረታት ሁሉ በእርሱ ዘንድ ውብና የየራሳቸው ዐላማና ተግባር ያላቸው ናቸው (ዘፍ.1፥25)
እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት በፍጡር ዐቅም ሙሉ በሙሉ ተቆጥረው የሚዘለቁ አይደሉም፤ ከጥቂቶቹ በስተቀር ሁሉንም በዐይነ ፍጡራን ማየት ስለማይቻል ቅዱስ መጽሐፍ ፍጡራንን ጠቅለል አድርጎ በአጭር ቃል ሲገልጽ ‹‹በሰማይና በምድር ያሉት፣ የሚታዩትና የማይታዩት›› ይላቸዋል፤ (ቈላ. 1፥15) በምድር ላይ እያሉ ከማይታዩት መካከል አንዱ ዘመን ወይም ጊዜ ነው፤ ጊዜ በድርጊት ከሚታወቅ በቀር በዐይን የሚታይ ግዙፍ አካል ወይም ልዩ ቀለም ያለው ፍጡር አይደለም፡፡
ይሁን እንጂ ባለመታየቱ ብቻ የለም ብሎ መደምደም ወይም መናገር አይቻልም፤ ምክንያቱም ከድቁቅ ስፍረ ጊዜ አንሥቶ ሰዓታትን በቀናት፣ ቀናትን በሳምንታት፣ ሳምንታትን በወራት፣ ወራትን በዓመታት ከዚያም በልዩ ልዩ አዕዋዳት እየጠቀለለ ሲያሽከረክር በተግባር እናያለንና ነው፡፡ ዘመን የድርጊት መሣሪያ ስለሆነ በአንድ ወቅት በተፈጸመ መልካም ወይም መጥፎ ነገር ይገለጻል፤ ከዚህም የተነሣ ዘመኑ መልካም ነው ወይም መጥፎ ነው ሲባል እንሰማለን ፡፡ ይሁንና የእኛ መሠረታዊ ጉዳይ ሊሆን የሚገባው የዘመን መታየትና አለመታየት ሳይሆን ለፍጡራን ከሚሰጠው ጥቅም አኳያ ግንዛቤ ወስደን ተጠቃሚ ለመሆን መንቀሳቀሱ ላይ ነው ፡፡
ዘመን ከዓለም መፈጠር በፊት ያልነበረ ከዓለም ጋር አብሮ የተፈጠረ፣ በሰማይ የሌለና ለምድራውያን ፍጡራን ብቻ አገልግሎት ሊሰጥ የተፈጠረ ነው፤ (ዘፍ.1፡14) ፡፡ የዘመን ሀብት ባይኖር ሰው ምድራዊ ሕይወቱን በትክክል መምራት አይችልም ነበር፡፡ በመሆኑም ምድራውያን ፍጥረታት በአጠቃላይ፣ በተለይም ደግሞ የሰው ልጅ ሥርዐት ባለውና ቅደም ተከተሉን ጠብቆ በዕቅድ ሥራውን በማከናወን ሕይወቱን በትክክል መምራት ይችል ዘንድ ሀብተ ዘመን ያስፈልገዋል ፡፡
ዘመን ለተግባር ከሚያበረክተው አገልግሎት በተጨማሪ በትምህርት ሰጪነቱ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ያለፈውን ዘመን እንድናስታውስ እንጂ እንዳንረሳ የልጅ ልጅ ዘመናትን አስብ ብሎ እግዚአብሔር ይነግረናል፡፡ ምክንያቱም ለወደፊቱ የተሻለ ሥራ መሥራት የምንችለው ካለፈው ዘመን ትምህርት ቀስመን፣ ልምድና ተሞክሮ ወስደን ስለሆነ ነው፤ ሥራን ከዘመን ለይቶ ወይም ነጥሎ ማስቀመጥ በፍጹም አይቻልምና ፡፡ ስለሆነም ዘመን ለአጠቃላዩ ሥራችን ተቀዳሚ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግለን እግዚአብሔር የሰጠን ሀብት ነውና ጊዜን በከንቱ ሳናባክን በምልአት ልንጠቀምበት ይገባል ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁሉንም የተፈጥሮ ሀብት ተሟልቶ የተሰጣት፣ ድንቅና ውብ ሀገር ናት፤ ምድራዊት ገነት በሆነች በዚች ሀገር ተቀምጠን ስለድህነት ማውራት ከእንግዲህ ወዲህ እንዲያከትም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት መረባረብ አለበት፤ ልማታችንን በአስተማማኝ ደረጃ ዘላቂ ለማድረግ የድህነታችን ምሥጢር የት እንዳለ በውል ማወቁ ይጠቅማል ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የድህነታችን ምሥጢር ተደብቆ ያለው የሥራ ባህልን አዳብሮ፣ የጊዜን ጥቅም ዐውቆና አንዲት ደቂቃ ስንኳ ሳያባክን በሀገሩ ውስጥ ሠርቶ ለመለወጥ ያለን ተነሣሽነት አናሳ መሆኑ ላይ ነው፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ይህንን ተገንዝቦ መሠረታዊ የአስተሳሰብና በጊዜ ሠርቶ የመለወጥ ባህል ሊያጎለብት ይገባል፤ ይህንን ክፍተት በውል ስናውቅና በሥራ ስንታገለው ድህነትን ከሥር መሠረቱ ነቅለን መጣል እንችላል ፡፡
ዛሬ አደጉ በለጸጉ ተብሎ የሚነገርላቸው ሀብታም ሀገሮች አብዛኛዎቹ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ለእርሻና ለልዩ ልዩ አዝርእት የተመቸ ለም መሬት፤ ለእንስሳ ርባታና ለሰው ኑሮ የተመቸ አየርና ንጹሕ ውኃ፣ በልዩ ልዩ ማእድን የተሞላ ነገር ግን ገና ያልተፈተሸ ድንግል መሬት ኖሮአቸው ሳይሆን፣ ያላቸውን ውሱን ሀብት በበለጸገ የሥራ ባህል ማለትም ሥራን ሳያማርጡ፣ ጊዜን በከንቱ ሳያባክኑ ያለ ዕረፍት ሌት ተቀን በመሥራታቸው ያገኙት ጸጋ እንደሆነ ማስተዋል አለብን፡፡ በመሆኑም ኅብረተ ሰባችን በአጠቃላይ በተለይም ወጣቱ ትውልድ አዲሱን ዘመን ሲቀበል አዲሱን ዓመት ከሀገራችን የሕዳሴ መርሐ ግብር ጋር በማቀናጀትና ጠንክሮ በመሥራት ግዙፍ የሆነ የልማትና የእድገት ስኬት ለማረጋገጥ ከዳር እስከ ዳር ተባብሮ እንዲንቀሳቀስ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን መልካም አዲስ ዓመት ያድርግልን፡፡ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ አሜን፡፡