መስከረም 1 ቀን የ2007 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፥ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
የመልካም ስጦታ ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ከ2006 ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማርቆስ ወደ 2007 ዓመተ ምሕረት ዘመነ ሉቃስ በሰላም አደረሳችሁ፡፡
“ወዓመቲከኒ ዘኢየኃልቅ — ዘመንህም አያልቅም።»
(መዝ 101÷27)
ሁሉን ፈጥሮ የሚመግብ እግዚአብሔር አምላክ በባሕርዩ ፍጹም ነውና በእርሱ ዘንድ ኅልፈት መለወጥ፤ ማርጀትና የዘመን ፍጻሜ የለም፡፡
እግዚአብሔር አምላክ እርሱ ራሱ ወደር የሌለው ብርሃን ነው፣የሚገለጽበት ዓለምም በሚያስደንቅ ብርሃን ያሸበረቀና ጨለማ የማይፈራረቀው በመሆኑ ዘመን አይቈጠርለትም፡፡ በዚህ ተለዋዋጭ ዓለም የምናየው የዘመናት ኅልፈትና መተካት፣ ኀላፊው የብርሃን ዑደት ከጨለማ ጋር እየተፈራረቀ የሚፈጥረው ሂደት እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ያስቀመጠውና እኛም በዐይናችን የምናየው ነው። (ዘፍ. 1÷14-19)
የምንኖርበት ዓለምና ከእርሱ የወረስነው ሁሉ ኀላፊ እንጂ ቀዋሚ ባለመሆኑ ዘመን ጨምሮ ሁሉም ሲያልፍና ሲተካ እናያለን፡፡ የመንፈሳውያን ፍጥረታት መኖሪያ የሆነው ብርሃናዊው ዓለም ግን ዘመን የማይቈጠርለት፣ ኅልፈትና ውላጤ የሌለበት፣ ጨለማ የማይፈራረቅበት፣ የብርሃናት ዑደት የማይታይበት ነው፣ ነዋሪዎቹም እንደዚሁ የማያልፉና የማያረጁ፣ ዘመንም የማይቈጠርላቸው ቀዋሚና ዘለዓለማዊ ሕይወት ያላቸው ናቸው፡፡ በኀላፊው ዓለም ያሉና በብርሃናት ዑደት ምክንያት የሚቈጠሩ ዘመናት ኀላፍያን ቢሆኑም፣ በእነርሱ መሣርያነት ዘመን ወደማይቈጠርለትና ወደ ማያልፈው ብርሃናዊ ዓለም ሊያደርስ የሚችል ሥራ መሥራት ስለሚቻል፣ ዘመናት በሰው ልጅ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት ውስጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ የሥራው ዐይነት የተለያየ ቢሆንም፣ ሁለቱም ዓለማት የሚያመሳስላቸውና አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ሥራ ነው፤ በሁለቱም ዓለማት ያሉ ፍጡራን በሥራ ተጠምደው እንዲኖሩ እግዚአብሔር ፈጥሮአቸዋል፡፡
ሥራ የመንፈሳዊም ሆነ የሥጋዊ ሕይወታችን መድኅን ነው፣ ለሥራ የተፈጠርን ስለመሆናችን አካላችንና ባሕርያችን ራሱ ይመሰክራል፣ አፍኣዊ አካላችንም ሆነ ውሳጣዊ ባሕርያችን ሥራን ካልሠራ ሰላምና ጤና አያገኝም፤ እግዚአብሔር አምላክ ለሥራ የሚያገለግሉ ውጫዊ መሣሪያዎችን በብዛት ሰጥቶናል፡፡ ከሰጠን ብዙ ስጦታዎች አንዱና ዋነኛው ዘመን ነው፤ ሥራን መሥራት የምንችለው በዘመን ውስጥ ሆነን ነውና ጊዜን በሥራ መጠቀም ትልቅ ብልህነት ነው፣ ዘመን በሥራ ከምንቀድመው በቀር ሮጦ የማይደክም ፍጡር ስለሆነ ለአፍታ እንኳ የማናስቆመው ነገር ነው፡፡ ስለሆነም ጊዜን ለሥራ የማንጠቀም፣ ይልቁንም በተራ ነገርና በአሉባልታ፣ በነገር ትብትብና በጠማማ አስተሳሰብ ጊዜን የምናባክን ከሆነ፣ በአንገት ላይ ሰይፍን እንደመሳብ ይቈጠራል።
ቀደምት ኢትዮጵያውያን አበው የሥራን ክቡርነት ጠንቅቀው በመረዳታቸው እስከዛሬ ድረስ የዓለም ጠበብቶች ሊደርሱበት ያልቻሉ ጥበባዊ ሥራን ሠርተው እንዳስረከቡን በእጃችን ያለ ውድና ብርቅ ቅርስ ምስክር ነው፡፡ በመካከሉ በተፈጠረው ክፍተት ጥበባዊ ሥራችንና ሥልጣኔአችን ለተወሰነ ጊዜ ቆም ቢልም፣ አሁን በአዲስ መንፈስ እየተጋጋለና እየተቀጣጠለ መታየቱ እጅግ የሚያስደስትና የሚያኮራ ነው፤ ኢትዮጵያ ሀገራችን ለብዙ ዘመናት አጥታው የነበረው ይህንን ዕሴት ነው፤ አሁን የሕዳሴ ዘመን ተበሥሮአል፤ ልማቱና እድገቱ በሁሉም መስክ በአራቱም መዓዝን ተጧጡፎአል፣ ይህ የእግዚአብሔር በረከትና ስጦታ ነው፣ ሕዝባችንም ይህ ዕድል እንዳይቀለበስ አጥብቆ መንከባከብና መጠበቅ አለበት፡፡ ሕዝባችን ከልማት፣ ከአንድነት፣ ከሰላምና ከእኩልነት የተሻለ ሌላ ጠቃሚ ነገር ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለሆነም በአዲሱ ዘመን ጅምር የልማትና የሰላም ሥራዎቻችንን ከግብ በማድረስ፣ አዳዲስ የልማት ሥራዎችንም በመጀመር የሀገራችንን የሕዳሴ ጒዞ ማፋጠን አለብን፡፡ የተጀመረው የልማትና የእድገት ሥራ ሁሉ ግቡን ሊመታ የሚችለው ሰላም፣ ፍቅር ስምምነት፣ አንድነት መቻቻል፣ መከባበር፤ ፍትሕና እኩልነት የነገሠበት ማኅበረ ሰብ ሲኖረን ነው፤ ስለሆነም እያንዳንዱ ቅን ዜጋ ይህንን በመገንባትና በማስጠበቅ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፣ እያንዳንዱ ዜጋ ሠርቶ ከመልማት በቀር ሌላ አጀንዳ ሊኖረው አይገባም፡፡
በመጨረሻም፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በጤናው ዘርፍ በተለይም በእናቶች የጤና እንክብካቤ፣ በአካባቢያዊ የሰላም ጥበቃ፣ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት፣ በመልካም አስተዳደርና በፍትሕ አሰጣጥ ወዘተ በመሳሰሉት ዐበይት ተግባራት እየፈጸመችው ያለ ተግባር ኢትዮጵያ ሀገራችን በዓለም መድረክ ያላትን ተሰሚነትና ተቀባይነት በእጅጉ የሚያሳድግና መልካም ገጽታችንን የሚያጎላ መሆኑን የተገነዘብንበት ወቅት በመሆኑ ሕዝቡ በቀጣዩ አዲስ ዓመትም ይህንን አጠናክሮ እንዲቀጥልበት መልእክታችንን እናስተላልፋለን፣ አዲሱን ዓመት የሰላም፣ የልማትና የእድገት ዘመን ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ አሜን፡፡