ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጅጅጋ፣ በጎዴ ከተማና በሌሎችም ከተሞች በደረሰው አሠቃቂ ግድያና ዘረፋ እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጥተዋል

ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጅጅጋ፣ በጎዴ ከተማና በሌሎችም ከተሞች በደረሰው አሠቃቂ ግድያና ዘረፋ ምክንያት በየመጠለያው በረኃብ፣ በጽምና በዕርዛት ለሚሠቃዩ ካህናትና ምእመናን መንግሥት ተፋጥኖ እንዲደርስላቸውና የነፍስ አድን ሥራ እንዲሠራ በአጽንዖት አሳሰበ፡፡ ማሳሰቢያውን ቅዱስነታቸው እንደሚከተለው አስታውቀዋል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረዥም የታሪክ ጒዞዋ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በእኩልነት ደረጃ ስታገለግል የኖረች እናት ቤተ ክርስቲያን ናት አሁንም አገልግሎቷን ከመፈጸም የተገታችበት ጊዜ የለም፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረ ሰቦችና ሕዝቦች ሀገር ብትሆንም ሕዝቦቿ በሃይማኖት፣ በጎሣና በቋንቋ ሳይለያይዩ ሀገርን የሚወር፤ ነፃነትን የሚገፍፍ ጠላት በሀገር ላይ ሲነሣ አንድነቱን አጠናክሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ የሀገሩን ነፃነት ሲያስከብር ኖሮአል፡፡ በተለይም የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች በወንድማማችነት ተሳስበው የኖሩት አንዱ የሌላውን እምነትና ሥርዐት ሳይነካ ከኢትዮጵያዊነት ስሜት በመነጨ መተሳሰብና እውነተኛ ፍቅር ነው፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕግና መንግሥት ባለበት ሀገር በአንዳንድ የክልልና የዞን መስተዳድሮች በባሌ ጎባ፣ በጣና በለስ፣ በኦሮምያ ክልል፣ አሁን ሰሞኑን ደግሞ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልና በአንዳንድ ቦታዎች በተለያየ ምክንያት በሚፈጠር የርስ በርስ ግጭት መነሻነት በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠረ፣ በቅዱስ ረድኤቱ የከበረ፣ ሕያዊት፣ ነባቢት ነፍስ የተዋሐደችው፣ ፍጹም አእምሮና ዕውቀት የተሰጠው የሰው ነፍስ እየጠፋ እናያለን፤ ይልቁንም በሱማሌ ክልል ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ካህናት ተገድለዋል፤ ንብረት ተዘርፎአል፡፡ ዛሬ በመላ ሀገራችን ከመሐል ኢትዮጵያ እስከጠረፍ ዳርቻ ባሉት ክልሎችና የመስተዳድር ዞኖች ሰላም፣ ፍቅር አንድነት መከባበርና መቻቻል፤ እየተደማመጡና እየተናበቡ መሥራት በበለጠ እንዲዳብርና እንዲሰፍን የአመራር መርሕ በስፋትና በጥልቀት እየተሰጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ ለሚተላለፈው መመሪያና የሰላም መልእክት ትኵረት ባለመስጠት የሀገርና የወገን ፍቅር ስሜት የተለየው የጭካኔ ሥራን መሥራት ከኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚጠበቅ ተግባር ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ይህ መወገዝ ያለበት የዐመፅ ተግባር አብረው በኖሩ ወንድማማቾች መካከል የፈጠረው ግጭት፤ አለመግባባትና መቃቃር በዚህ ሳቢያ እየተካሄደ ያለው መጠፋፋት እየሰፋና እያደገ ወደሌላ ከመሸጋገሩ በፊት ከወዲሁ ታስቦበት ተፋጥኖ ይገታ ዘንድ የባለ ድርሻ አካላት ሁሉ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም የተፈጠረው ችግር ተወግዶ የተሟላ ሰላምና መረጋጋት እውን እስከሚሆን ድረስ የመፍትሔው አካል በመሆን የሚቻላትን ሁሉ በመፈጸምና በማስፈጸም ያለባትን ሀገራዊ ግዴታና ኀላፊነት በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅባታል፡፡ የሀገሪቱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሰላምና መረጋጋት በሚጎዳ መንገድ የሚሄዱ ግለሰቦች ሁሉ እንዲስተካከሉ ከእግዚአብሔር ሕግ አኳያ ምክርና ትምህርት በመለገስና በማስተላለፍ ዓላማዋና ዐይነተኛው ተግባርዋ እንደሆነም ማስገንዘብ ይኖርባታል፡፡ ስለዚህ ሰላምና መረጋጋት የሚመነጨው ከቤተ ሰብና ኅብረተ ሰብ ስለሆነ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲመክሩ፣ እንዲገሥጹ እንዲያስተምሩ ያስፈልጋል፡፡

ኅብረተሰቡም በዘር በሃይማኖትና በጎሣ ሳይለያይ በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢ እየተሰማና እየታየ ካለው መጥፎ እንቅስቃሴ ራሱን እንዲገታ እንዲቈጣጠር፤ ካህናትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም የመልካም ሥነ ምግባር መሠረት በሆነችው ሀገራችን ላይ ችግሩ በተከሠተበት አካባቢ እየተገኙ ትምህርተ ወንጌል እየሰጡ የማረጋጋት፣ የማጽናናትና የማስታረቅ ሥራን እንዲሠሩ፡፡ ይህን አላስፈላጊ ግጭት ከሕዝባችንና ከሀገራችን እግዚአብሔር እንዲያርቅልን ጾመ ፍልሰታ ለማርያምን ምክንያት በማድግ ሙሉ ሱባኤውን በሁሉም ገዳማትና አድባራት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ፤ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጅጅጋ፣ በጎዴ ከተማና በሌሎችም ከተሞች በደረሰው አሠቃቂ ግድያና ዘረፋ ምክንያት በየመጠለያው በረኃብ፣ በጽምና በዕርዛት ለሚሠቃዩ ካህናትና ምእመናን መንግሥት ተፋጥኖ እንዲደርስላቸውና የነፍስ አድን ሥራ እንዲሠራ በአጽንዖት እናሳስባለን፡፡

ለሞቱት ወገኖቻችንም በመላ ገዳማትና አድባራት ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ፤ በችግሩ ዙሪያ የሚገኙ የክልልና የዞን መስተዳድር አካላትም የገላጋይ ያለህ የሚል ሮሮ እስከሚሰማ ድረስ ሳይጠብቁ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ድንጋጌ በማክበርና በማስከበር ከመንግሥትና ከሕዝብ የተረከቡትን ኀላፊነት በብቃት እንዲወጡ በቤተ ክርስቲያናችን ስም አደራ እያለን ይህን መልእክት እናስተላልፋለን፡፡ ኅልፈተ ሕይወት ያጋጠማቸው ወገኖቻችንን እግዚአብሔር በመንግሥቱ እንዲቀበልልን ያዘኑትን እንዲያረጋጋልን፤ የተጎዱትን በምሕረቱ እንዲጎበኝልን፤ ዘላቂ ሰላምም እንዲሰጠን እንጸልያለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡