ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሃያ ሰባት ዓመታት በስደት ይኖሩ የነበሩት የኢትዮጵያ አራተኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በዕርቀ ሰላም እና በአንድነት ወደ ሀገራቸው ገብተዋል፡፡

ስድስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው ቅዱስነታቸውን የተቀበሏቸው ሲሆን በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐውደ ምሕረት ለአቀባበሉ ለተሰበሰቡት ካህናትና ሕዝበ ክርስቲያን የሚከተለውን ታሪካዊና ሐዋርያዊ የአንድነትና የሰላም ቃለ በረከት አስተላልፈዋል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይሄልዉ አኀው ኅቡረ፡፡ (መዝ. 132፥1)

• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 4ኛ ፓትርያርክ፣
• ከሀገር ውስጥና ከውጭ አህጉር የመጣችሁ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
• የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዚህ ልዩ የሆነ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብረ በዓል ለማክበር በዚህ ዐውደ ምሕረት የተገኛችሁ እንግዶች በሙሉ።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም፤ ሶበ ይሄልዉ አኀው ኅቡረ — ወንድሞች በኅብረት ቢኖሩ፣ እነሆ መልካም ነው፤ እነሆም ያማረ ነው›› ሲል ጸልዮዋል፡፡ እኛም የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክታችንን የምናስተላልፈው በታላቅ መንፈሳዊ ደስታና ኅብረት ነው፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከብዙ ሺህ ዘመናት ጀምራ በፈጣሪዋ ታምና ነቅዕ በሌለው ሁናቴ በሃይማኖቷ ጸንታ፤ በነፃነቷ ኮርታና ታፍራ ለሥራዋም የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት መሆኑን አስተምራ፤ ጸሎቷንና ልመናዋን ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር›› ሲል ንጉሥ ዳዊት በመሰከረላት መሠረት ዕለት በዕለት እያስታኮተችና ወደ እግዚአብሔር እየጸለየች የምትኖር ስብሐተ እግዚአብሔር በየጊዜው የማይለይባት ሀገረ እግዚአብሔር ናት፡፡

ከላይ ከፍ ብሎ በመግቢያችን “ሶበ ይሄልዉ አኀው ኅቡረ — ወንድሞች በጋራ ቢኖሩ ቢተዳደሩ መልካም ነው” ሲል ነቢዩ በተነበየው ትንቢትና ባቀረበው ልመና መሠረት ታማኞቹ ለመሆን ለመረጠን ፈጣሪያችን የምንመልሰው ወሮታ ቢኖር የተቀበልነውን አምላካዊ አደራ እኛም ሠርተን ጠብቀን ተከታዮቻችንንም በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን፣ በሥርዐታችን፣ በባህላችንና በወጋችን መሠረት እንዲጸኑና እንዲሠሩ በመንፈሳዊ አገልግሎታቸውም በኩል ለቤተ ክርስቲያናችንና ለቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህን የመረዳዳትንና በአንድነት የመኖርን ሐሳብ እናስተምራቸዋለን ብለን በፍጹም ልባችን ተነሣሥተናል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 4ኛው የቤተ ክርስቲያናችን ፓትርያርክ!
ሁሉም እንደሚረዳው እኛም አሜሪካን አገር በነበርንበት ወቅት የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊና ሲኖዶሳዊው አንድነታችንን ወደቀደመው መሥመሩ ለመመለስ ብዙ ተጒዘን እንደነበር ቅዱስነትዎ ያውቀዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን የተፈጠረውን ልዩነትና የአንድነት መታጣት ችግሩ ከታየበት ጊዜ ጀምሮ በየቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤያት በጸሎት ያልታሰበበትና ያልተወሰነበት ጊዜ የለም፡፡ ሆኖም የሀገራችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን የአንድነት ህልውና በሚፈልጉ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ካህናት ተደጋጋሚ ሙከራ ሲደረግ መቆየቱ የሂደቱ ዋነኛ ታሪክ ነው፡፡

አሁንም ደግሞ ከሁሉ በበለጠ የኤ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ያደረጉት የማቀራረብና የማግባባት ሥራ ከ45 ዓመታት ወዲህ ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ባልታየ ሁናቴ የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት መንግሥታዊ ድጋፍ ታክሎበት ችግሩ በሚፈታበት ሥፍራ በአካል ጭምር ተገኝተው በሠሩት ሥራ የቤተ ክርስቲያናችን የአንድነት ታሪክ ዋና ባለሟል ያደረጋቸው ስለሆነ ቤተ ክርስቲያናችን በሠሩት መልካም ሥራ ስታመሰግናቸውና በጸሎትም ስታስባቸው ትኖራለች፡፡

ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበት ጊዜ አለው ተብሎ በመጻሕፍት እንደተጻፈው፤ ቅዱስነትዎና እኔ ዕድሜ ከጤና እግዚአብሔር አምላካችን ሰጥቶን ይህን ቀን ለማየት ስላበቃን ለእግዚአብሔር ልዩ ምስጋና ዘወትር እያቀረብን ወንድማማችነታችንንና መንፈሳዊ አባትነታችንን አጽንተን ከመኖር በስተቀር ሌላ ምን እንከፍለዋለን፡፡

በተለይም ቅዱስነትዎና እኔ የደረስንበት ይህ ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ሰላምና ፍቅር፣ የቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት መሆኑን ልጆቻችን የሀገራችን መሪዎች በአጽንዖት በአደባባይ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለም ለሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ሲመሰክሩና ሲናገሩ ከማየትና ከመስማት በላይ ምንስ የሚያስደስት የተቀደሰ ነገር ይኖራል፡፡

ሕዝበ እግዚአብሔር የሆነው ሕዝባችን ካልተረዳዳና ካልተመካከረ፣ በአንድ ሐሳብ ካልተጓዘ ጽኑ ፈተና ያገኘዋልና ለቤተ ክርሰቲያናችንና ለሕዝባችን እውነተኛ ጥቅም በዝግታ እየተመካከርንና፤ ሥራውን የበለጠ እያሻሻልን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንመራዋለን የሚል ጽኑ እምነት አለን፡፡

ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አንድነትና ፍቅር መሠረት የሆኑና በወንድማማቾች መካከል ያለውን የሐሳብና የአስተዳደር ልዩነት ታላቅ ፍቅር በተሞላበት የልጅነት መንፈስ አማካሪዎቻችን ሆነው ባላሰለሰ ጥረት ለዚህ ዕድል በማብቃታቸውና በመብቃታችን ኢትዮጵያ ዛሬም ለታሪክ የሚሠሩና የሚኖሩ የጀግኖች እናት መሆኗን ቀጣዩ ትውልድ በታሪክነት የሚጠቅሰውና የሚጽፈው ተግባር ይሆናል፡፡

ይህን የምንለው የቀደሙ አባቶቻችን ለቤተ ክርስቲያናችን ክብርና ልዕልና የለፉበትንና የደከሙበትን ጉዳይ የሚያሰናክል ሁናቴ ከ2 ዐሥርተ ዓመታት በላይ በአንዲቷ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በአስተዳደርና በሲኖዶሳዊው አመራራችን ውስጥ የቆየውን የልዩነት ታሪክ ‹‹ወንድሞች በአንድነት ሊኖሩ፣ በአንድነት ሊመሩና ሊሠሩ በመስማማት የካህናትን፣ የምእመናንንና የወጣቶችን ዕንባ የሚያብስ ውሳኔ መወሰናችን፤

በእኛ ዘመነ ክህነትና ፓትርያርክነት መታወጁ እኛን እግዚአብሔር አምላክ የበለጠ እድለኞች ያደረገን ሲሆን ለሰማዕያኑ ካህናት፣ ምእመናንና ወራዙት እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን ይህ መልካም ብሥራት ሲነገር በሕይወታቸው ያሉት በክብር ጐልምሰው ሲታዩ፤ በሞት የተለዩት አፅማቸው በወርቅ ቀለም ተጽፎ አብቦና አፍርቶ ትተዋቸው ለሄዱት ትውልዶች የታሪክ ውርስ ሆኖ ሲታወስ ይኖራል፡፡

በዚህ በዛሬው ቀን የቸርነት ባለቤት የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን በመገኘት የአንድ አባት የእግዚአብሔርና የአንዲት እናት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ልጆች ዳግመኛ በፍቅር ማሰሪያነት ታስረንና ተጣምረን እግዚአብሔርን ማመስገንና ቤተ ክርስቲያናችንን ማገልገል መጀመራችን በምድር ሠራዊትና በሰማይ መላእክት ጭምር ታላቅ ደስታ እንደሆነ እምነታችን የጸና ነው፤ እግዚአብሔርንም ዕጹብ ድንቅ ብለን ከማመስገን በላይ ምን እንላለን፡፡

አሁንም ደጋግመን የምንለው ለዚህ ዋና ዓላማ የእርስ በእርስ መመካከርን፣ መግባባትን፣ ፍቅርን፣ ይቅርታንና አንድነትን፣ የሚጠይቅ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያናችን ለምንመራቸውና ለምናገለግላቸው ሕዝበ ክርስቲያን ጉዳትና ጥቅሙን እያመዛዘን የምንመክርበት፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ላለችው ለቤተ ክርስቲያናችን የሰላምና የአንድነት አስተዳደር የምንናስቀጥልበት ቀን ላይ መሆናችን የቅዱስ ሲኖዶስ የወል የሰላምና የፍቅር ድል የተበሠረበት ዕለት ነው፡፡ የፍቅርና የሰላም የአንድነት ጠላት የሆነው ዲያቢሎስ በአደባባይ የተረታበት ዕለት መሆኑንም የምንናገረው በዚሁ ዕለት ነው፡፡

ከዚሁ ጋር የማይዘነጋው ጉዳይ ቢኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ቅዱስነትዎና እኔ በተለይ በእግዚአብሔር ተመርጠንና ተጠርተን በ3ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ በአንድ ዕለት ተቀብተን በኤጴስ ቆጶስነት መሰየማችን ነባሩ የመነሻ ታሪካችን ነው፡፡ በተቀበልነውም የመስቀል መሸከም አደራ ቤተ ክርስቲያናችንን ስናገለግል ቆይተን ለዚሁ ለታላቁ ክብር ላበቃን አምላክ በአንደበታችን ብቻ ማመስገን አይበቃንም፡፡ ለዘለቄታ ቀዋሚ፣ ለትወልድ ተሻጋሪ፣ ለሰው ሁሉ በፍቅር የሚደርስ እኛ ጀምረን መጨረሱን ለእግዚአብሔር የምንሰጥበት ታላቅ የአደራ መቀበያና መስጫ፤ እንዲሁም ፍቅረ እግዚአብሔር ከፍቅረ ቢጽ ጋር ተዋሕዶ የተከበረበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደራዊ ሥራ በማሻሻል፡፡ በካህናት፣ በምእመናንና በወጣቶቻችን መካከል የሠለጠነ አሠራር በመትከል ስለ ሀገራችንና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የምንደክም የሥራ ተከፋዮች እንሆናለን፡፡

ቅዱስ አባታችን!
በጤናና በሕይወት ጠብቆ ለዚህ ዕለት አድርሶ ወደ ቅድስት ሀገርዎ ኢትዮጵያ ለመግባት እንኳን አበቃዎ እያልኩ ንግግሬን “ኅሱ ሰላማ ለሀገር — ለሀገራችሁ ሰላምን እሹ” የሚለውን ለመፈጸም “ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይሄልዉ አኀው ኅቡረ” ለሚለው ዘይቤ ተገዥዎች ሆነን ቤተ ክርስቲያናችንንና ተከታዮቻችንን እየመራን ሐዋርያዊ ተልእኮአችንን እንደምንፈጽም ያለንን እምነት እንገልጻለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።