ከጥቅምት 11 ቀን እስከ 18 ቀን 2014 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቍጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልአተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዐተ ጸሎት ከፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሄድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
1. የ2014 ዓ.ም. የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ መልእክት አሁን በሀገራችን እየታየ ባለው ጦርነት እና የእርስ በርስ ግጭት ላይ ያተከረ ሲሆን፡-

• ጦርነቱ በወንድማማቾች መካከል እየተደረገ ያለና ኀዘኑን የከፋ ያደረገው መሆኑ፣
• በዚሁ ጦርነትና ግጭት በርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ለሞት ለስደትና ለረኃብ መዳረጋቸው፣
• በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ሀገራዊ ልማት ላይ እያደረሰ ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ይህ ጦርነትና ግጭት ተወግዶ በሀገሪቱ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ከሁሉም በላይ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ይቅርታ ምሕረት መጠየቅ አስፈላጊ በመሆኑ ጉባኤው ይህንኑ መልእክት ተቀብሎ በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል፡፡

2. በሀገራችን በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሰላም ዕጦትና ጦርነት ወደፊትም ሊያስከትል የሚችለው ችግር ከፍተኛ መሆኑ ስለታመነበት በተቻለ ዐቅም ዜጎች ሁሉ ለሀገራዊው አንድነትና ሰላም መገኘት ዘብ እንዲቆሙ የየበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

3. በዚሁ ሀገራዊ የሰላም ዕጦት እየተደረገ ያለውን ጦርነት ምክንያት አድርገው ከሀገር ውጭ የሚገኙ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትና ካህናት ሀገራዊ ሰላም ላይ ጥላ በሚያጠላ ሀገራዊና ሕዝባዊ አንድነትን በሚያፈርስ መልኩ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ከቤተ ክርስቲያንና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ነን ከሚሉ በፍጹም የማይጠበቅ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ በመሆኑም በአውስትራልያ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ሁነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እየፈጸሙ ካለው ሀገራዊና ሕዝባዊ አንድነት ከሚያደፈርስ ተግባራቸው እንዲቈጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ እያሳሰበ አሁንም ወደ ሰላሙና አንድነቱ እንዲመለሱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ይህንንም የሰላም ተልእኮ የሚያስፈጽም በውጭው ዓለም የሚገኙ ብፁዓን አባቶች የሚመሩት የጋራ የሰላም ልኡክ እንዲቋቋም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

4. በሀገራችን በኢትዮጵያ በተከሠተው ጦርነት ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉና በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግር ለደረሰባቸው ወገኖቻችን እርዳታ እንዲሆን ብር 50,000,000 (ኃምሳ ሚሊየን ብር) በቤተ ክርስቲያናችን ስም ችግሩ ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

5. የሀገራችንን ቀጣይ የእድገት ደረጃ በእጅጉ ከፍ ያደርጋል የሕዝቦችን አኗኗር በመቀየር ከድህነት ያወጣል በሚል ታስቦበት ከዓመታት በፊት ግንባታው የተጀመረው የሕዳሴ ግድብ እየተጠናቀቀ ያለበት ምዕራፍ ላይ መድረሱና 2ኛ ሙሌት መከናወኑ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ትልቅ የድል ምዕራፍ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ አድንቋል፡፡ በቀጣይም ለመጨረሻው የድል ምዕራፍ ለመድረስ መላው ኢትዮጵያውያን በጒልበት በገንዘባቸውም በሐሳብም ጭምር ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳስቧል፡፡

6. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ መንፈሳውያን ኮሌጆችን አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ ጋር ለማመጣጠንና ተጨማሪ ኮሌጆች በማስፈለጉ በደቡብ ክልል የሚገኙ ሁለት ካህናት ማሠልናዎች ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲያድጉ አስፈላጊውም በጀት እንዲመደብላቸው ጉባኤው ወስኗል፡፡

7. ለመንበረ ፓትርያርክና ለየአህጉረ ስብከት የሚያገለግል የ2014 ዓ.ም. ዓመታዊ በጀት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተደልድሎ በቀረበው መሠረት ዝርዝሩን ተመልክቶ በጀቱ እንዲጸድቅ በማድረግ በሥራ ላይ እንዲውል ጉባኤው ወስኗል፡፡

8. የ4ዐኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ መግለጫ ላይ የተነጋገረው ጉባኤ በመግለጫው ላይ በመወያየት አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማድረግ እና በማጽደቅ የ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ መመሪያ እንዲሆን ጉባኤው ወስኗል፡፡

9. በሀገራችን በኢትዮጵያ የተደረገው 6ኛ ሀገራዊ ምርጫ ነፃና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መከናወኑና በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመመረጣቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተሰማውን ደስታ እየገለጸ፤ ቀጣዩ ሀገራዊ ሥራቸውም ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም የተሳካ የአመራር ዘመን እንዲሆንላቸው በሥራቸውም እግዚአብሔር አብሮአቸው እንዲሆን ቤተ ክርስቲያን ትጸልያለች፡፡

በአጠቃላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በጉባኤ በሰነበተባቸው ቀናት ስለ አብነት ት/ቤቶች እና ስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ስለ ሰንበት ት/ቤቶች መጠናከር ስለ ሀገራዊ ሰላምና አንድነት ሰፊ ምክክርና ውይይት ያደረገ ከመሆኑም በላይ በሀገራችን በተከሠተው የሰላም ዕጦት የደረሰው ጦርነት ረኃብና የጤና ማጣት አብቅቶ ሰላም እንዲሰፍን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰባት ቀናት ጸሎት ያደረገ ሲሆን በቀጣይም መላው ካህናትና ምእመናን ስለ ሀገራችን ሰላምና አንድነት እንዲጸልዩ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ አሳስቧል፡፡

በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ ለ8 ቀናት ሲያከናውን የቆየውን የጥቅምቱ 2014 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ዛሬ ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በጸሎት ዘግቷል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለሀገራችን ሰላሙን
ለመላው ሕዝባችን አንድነቱን ይስጥልን፤ አሜን፡፡

ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኀላፊ፣የአርሲ ሀገረ ስብከት እና የምሥራቅ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፣የሲዳማ ክልል፣ የጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ፤

በዚህ ሐዋርያዊ ጉባኤ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ እንድንወያይ በየጊዜው የሚሰበስበን እግዚአብሔር አምላካችን ከዚህ ዕለትና ሰዓት ስላደረሰን ምስጋና ለእርሱ እናቀርባለን፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ወደዚህ ዓመታዊ ዐቢይ ጉባኤ እንኳን ደና መጣችሁ።

“ዕቀብ ማፀንተከ ዘተወፈይከ ከመ ትስብክ ቃሎ ቀዊመከ
ቆመህ ቃሉን ትሰብክ ዘንድ የተቀበልከውን አደራ ጠብቅ”
1ኛ ጢሞ. 4፥14)፡፡
በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው በዓለም ያለው ኀላፊነት ሁሉ መንፈሳዊውም ሆነ ሥጋዊው ያለ አደራ የሚሰጥ አይደለምይልቁኑም ለቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ አደራ ከሁሉም የላቀ እንደሆነ አንስተውም ምክንያቱም ከሰው ሳይሆን በቀጥታ ከእግዚአብሔር የተሰጠ አደራ ከመሆኑም በተጨማሪ በሰማይም ሆነ በምድር ገደብ የለሽ ኀላፊነት በመሆኑ ነው ሌላው ተልእኮ የምድሩን ብቻ ሆኖ ከዚያም በጂኦግራፊ ወይም በመልክዐ ምድር ወይም በድንበር ወይም በሥጋዊና ዓለማዊ ጉዳዮች የተገደበ ነው የቅዱስ ሲኖዶስ ተልእኮ ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው በምድር ላይ ምንም ዐይነት ድንበርና ወሰን ስለሌለው ገደብ የለሽ ነው ምክንያቱም ራሱ አደራ ሰጪው አምላክ “ሑሩ ወመሀሩ ውስተ ኲሉ አጽናፈ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኲሉ ፍጥረት — ወደ ዓለም ዳርቻዎች ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” በማለት አዞናልና ነው ተልእኮው ይህ ከሆነ ዘንድ ኀላፊነቱም በዚህ ልክ ተሰጥቶናል ማለት ነው የቅዱስ ሲኖዶስ አደራ በመንፈስ ላይ ብቻ ያተኰረ ሳይሆን ምእመናንን በነፍሳቸውም ሆነ በሥጋቸው በምልአት መጠበቅን የሚመለከት ነው ማለትም ተልእኮአችን የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑት ምእመናን በምድርም ሆነ በሰማይ፣በሥጋም ሆነ በነፍስ ለጉዳት እንዳይጋለጡ መጠበቅ ነው ማለት ነው፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
ንዋይ ሩይ የተባለው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ በላከለት መልእክት የተሰጠንን አደራ እንዴት መወጣት እንዳለብን በሚገባ አስረድቶናል ይውም ተግቶ ቃሉን በመስበክ አደራችንን መጠበቅ እንዳለብን ነው ምክንያቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ከእግዚአብሔር ቃል የበለጠ የሰውን ኅሊና የሚረታና የሚያሳምን ሌላ ኀይል የለውምና ነው ቤተ ክርስቲያን በሁለት ሺሕ ዓመታት ተልእኮዋ የሕዝቡንና የአሕዛቡን ሕሊና ማርካ፣ መንፈሱን አርክታ ከጎኗ በማሰለፍ ለእግዚአብሔር ማቅረብ የቻለችው በዚህ ቅዱስና ኀያል ቃል ነው በመሆኑም እኛም ሆን የዘመኑ ትውልድ ከቃሉ የበለጠ ሌላ ኀይል እንደሌለ በውል ተገንዝበን፣ ለዚህም አጽንዖት ሰጥተን በትጋት መሥራት ግዴታችን ይሆናልቅዱስ ቃሉን በትጋትና በጥራት፣ በተመሥጦና በብቃት እያስተማርን መሆናችንና አለመሆናችንን የሚመሰክረው በምድሩ ላይ ያለው ተጨባጭ ውጤት እንደሆነም ማስተዋል ይገባናል ምእመናን እየበዙ በአገልግሎታችንና በትምህርታችንም እየተደሰቱ ከሆነ፣ እውነትም ቃሉን በትክክል አሥርጸናል ሠርተናልም ማለት ነው ተቃራኒው ከሆነ ግን ገና ይቀረናል ማለት ነውቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ጉባኤ ማየት መገምገምና ተጨባጭ የማስተካከል ሥራ መሥራት ያለበት በዚህ ዙሪያ ነው፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
መንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ ሥራ በአግባቡ ለማከናወን የሰላም መኖር እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ሰላም ከሌለ ሃይማኖታዊ አገልግሎትና አስተምህሮም መቆሙና መቋረጡ አይቀሬ ነው ሰላም ሲጠፋ አማንያንም ሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳት ላይ ይወድቃሉይህም በመሆኑ ዛሬ በሀገራችን በተከሠተው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱት ጉዳቶች በቤተ ክርስቲያናችን ሊከሠቱ ችለዋል፡፡ ይህ አሳዛኝ ክሥተት በሃይማኖት በወገንና በሀገር ላይ እያደረሰ ያለው ከባድ ጉዳት እንዲያበቃ ወደ እግዚአብሔር መጸለይና መማፀን ይኖርብናልነገሮች ሁሉ ከእግዚአብሔር በታች እንጂ በላይ ስላይደሉ መፍትሔው እሱ እንዲያመጣልን ወደ እርሱ አጥብቀን መጸለይ ይኖርብናል ከዚህም ጋር በጦርነቱ የተጐዱ ወገኖች ተደራራቢ ችግር እንዳያጋጥማቸው ሕዝቡን በማስተባበር ልንረዳቸውና ልንደርስላቸው ይገባል፡፡
በመጨረሻም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በተደነገገው መሠረት በጥቅምት ወር በየዓመቱ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን የሚካሄደው ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎት የተከፈተ መሆኑን በእግዚአብሔር ስም እናበሥራለን።

እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።

ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም 40ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኀላፊ፣ የአርሲ ሀገረ ስብከት እና የምሥራቅ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፣ የሲዳማ ክልል፣ የጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኀላፊዎች፣
ከሀገር ውስጥና ከውጭ አህጉር የመጣችሁ የየሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች፣
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየክፍሉ ኀላፊዎች፣
የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣
ከሁሉም አህጉረ ስብከት የመጣችሁ ተወካዮች በአጠቃላይ፤ የተበታተኑትን የሚሰበስብ፣ የተራራቁትን የሚያቀራርብ እግዚአብሔር አምላካችን ከልዩ ልዩ አጽናፈ ዓለም የመጣችሁትንና ከዚህ ከቅርብ የቆየነውን በአንድነት አሰባስቦ ስላገናኘን ክብርና ምስጋና ለአምላካችን እናቀርባለን።

“ወአናቅጸ ሲኦል ኢይኄይልዋ ወኢያንቀለቅልዋ፤
የሲኦል በሮች አይበረቱባትም፤ አያናዋውጧትምም።”
(ማቴ. 16፥18)

ይህን አረፍተ ነገር ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኀይልና ጽናት አስመልክቶ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን ትምህርት ነው፤ አረፍተ ነገሩ እንደሚያመለክተው ቤተ ክርስቲያን ፈተና የሚያበዙባት ፈታኞች እንደማይለዩዋት ነው፤ ፈተናውን የሚያመጡባት አካላት በስም ባይጠሩም በተግባራቸው የሲኦል በሮች ተብለው ስለ ተጠቀሱ ሞትና መቃብር እንደዚሁም የእነሱ ዘበኞች የሆኑ ሠራዊተ አጋንንት እንደሆኑ መረዳቱ አያዳግትም፤ ጌታችን የቤተ ክርስቲያን ፈታኞች እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በሙሉ ዐቅማቸው ቤተ ክርስቲያንን ቢታገሏትም ሊያሸንፏት ግን አይችሉም ማለቱ በራእየ ዮሐንስ እንደተገለጸው መቃብር በትንሣኤ ዘጉባኤ፣ ሠራዊተ አጋንንት ደግሞ በደመ በግዑ በመጨረሻ የሚሸነፉና ከነካቴው የሚወገዱ መሆናቸውን ለመግለጽ እንደሆነ እናስተውላለን፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትነ ክቡራን የጉባኤው ታዳሚዎች
ሊቀ ኖሎት በሆነው በአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተቋቋመውና የተሰበሰበው ይህ ዓለም ዐቀፍ ጉባኤ፣ የሲኦል በሮች የማያናውጧትን ቤተ ክርስቲያን ለመጠበቅ እንደሆነ ሁላችንም የምንገነዘበው ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ሺሕ ዘመናት ያህል በመከራ እየተፈተነች እስካሁን ድረስ ከዕለት ወደ ዕለት እየሰፋችና ሁሉንም እያዳረሰች የመጓዟ ምሥጢር መድኀኒታችን ከላይ የገባላትን ቃል ኪዳን ሊቀለብስ የሚችል ኀይል በሰማይም ይሁን በምድር የሌለ በመሆኑ እንደሆነ አንዘነጋውም፤ ይሁን እንጂ ዋናውና ላዕላዊው ጠባቂ እሱ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እኛም የጥበቃው ተሳታፊዎች አድርጎ ሹሞናልና አደራ ጭምር ያለበት የጥበቃ ተልእኮና ኀላፊነት አለብን፡፡ በዚህም “አማልክት አንትሙ ወደቂቀ ልዑል ኲልክሙ፤ እናንተ አማልክት ናችሁ፤ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ” ብሎ ያናገረው የጸጋ አምላክነት በእኛ ላይ እንዴት ተፈጻሚ እንደሆነ ማጤኑ ተገቢ ነው፤ ከዚህ አንጻር በአሁኑ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ፈተና በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?በየአካባቢው የሚገኙ ኖሎትስ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ያደረጉት ጥረት ምን ይመስላል? ለወደፊቱስ የቤተ ክርስቲያንን ፈተና ለማቅለል ምን ማድረግ ይገባል? የሚሉትን መሪ ሐሳቦች በማንሣት ይህ ጉባኤ የማየት ኀላፊነት አለበት፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ክቡራን የጉባኤው ታዳሚዎች፣
ቤተ ክርስቲያን በአየር የተንሳፈፈች ነገር ሳትሆን በማኅበረ አማንያን ልቡና ውስጥ ተጠልላ የምትገኝ መንፈሳዊት መንግሥተ እግዚአብሔር ናት፤ ይህም ባሕርይዋ ከአማንያን ህልውና ጋር ያቀራኛታል፤ አማንያንም ያለ ሀገር ህልውና ስለሌላቸው ቤተ ክርስቲያን በተከታዮቿ አማካኝነት ከሀገር ሰላም ጋር ትተሳሰራለች፣ ይህ ብቻም አይደለም፤ የዓለሙን ሰላምና ፍቅር አስተማሪ፣ ሰባኪና ተምሳሌት በመሆን የሰው ልጆችን ሁሉ የመጠበቅ ኀላፊነትም አለባት፤ ይህንም ስታደርግ እንደ እናትም እንደ መምህርም እንደ ሽማግሌም ማእከላዊት ሆኖ ሥራዋን በለብዎ ማከናወን እንዳለባት ይታወቃል፡፡ ይሁንና ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ጊዜ በፈተና ተከባ፣ ልጆችዋም እርስ በርስ እየተጣሉ እንደሚገኙ ዓለም ሁሉ የሚያውቀው ነው፤ እነዚህ ወገኖቻችን ቤተ ክርስቲያን ልጆቼ ብላ የተቀበለቻቸው፣ በልጅነት ያከበረቻቸውና ለእግዚአብሔር መንግሥት ዕጩ ያደረገቻቸው፣ ያም ባይሆን በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠሩ ክቡራን ሰዎች ናቸው፤ ቤተ ክርስቲያን በዚህም በዚያም ያሉ ሁሉ ልጆቿ ናቸውና ስለነሱ ይገዳታል፤ ይሰማታል፣ ያሳስባታልም፤ በመሆኑም ብትችል መክራና አስተምራ፣ ገሥጻና ተቈጥታ፣ ካልሆነም ልባዊ የሆነ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር በማቅረብ ከእርስ በርስ ጠብ ተላቅቀው በአንድነት፣ በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ በጸሎትና በምሕላ ፈጣሪን መማፀን አለባት፤ ይህን ስናደርግ የኖላዊነት ኀላፊነታችንን በአግባቡ እየተወጣን ነው ማለት እንችላለን፤ በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያስተላልፈው ቀኖናዊ መልእክት ገዳማቱ አድባራቱና አብያተ ክርስቲያናቱ በጸሎትና በምሕላ ተጠምደው ስለ ሕዝብ ስለ ምእመናንና ስለሀገር ደኅንነት አጥብቀው ፈጣሪን እንዲማፀኑ በዚህ ጉባኤ ፊት አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም አርባኛው ዓለም ዐቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ተከፍቶ በፈቃደ እግዚአብሔር የተጀመረ መሆኑን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር የተባረከ የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።