መስከረም 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

ፍጥረታትን ሁሉ በጸጋው ፈጥሮ የሚመግብና የሚመራ መሐሪውና ይቅር ባዩ አምላካችን እግዚአብሔር ያለፈውን ዓመት በሰላም አስፈጽሞ ለአዲሱ የምሕረት ዓመት ስላደረሰን ፍጹም ክብር አምልኮትና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፤ እንደዚሁም ለሁለት ሺሕ ዐሥር ዓመተ ምሕረት በዓለ መስቀል እንኳን በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!

“ወይመጽእ መዋዕለ ሣህል እምቅድመ ገጹ ለእግዚአብሔር
ከእግዚአብሔር ዘንድ የይቅርታ ዘመን ይመጣል፤”
(የሐዋ.ሥራ 3፥19)

ይቅርታ ከእግዚአብሔር የሚመነጭና ለዓለም ሁሉ ባለመቋረጥ የሚፈስ፣ ቀዋሚ የምሕረት ጅረት ነው፤ ሰማይ ከነግሡ ምድር ከነልብሱ በህልውና ጸንቶ ሊኖር የቻለውና የሚችለው በእግዚአብሔር ይቅርታ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ፍጥረት በበደለ ቊጥር ሳይቈጣ እግዚአብሔር በምሕረትና በይቅርታ ሁሉንም እያለፈ ፍጥረቱን ይመግባል፣ ይመራል፣ ያስተዳድራል፣ ይንከባከባል፤ የእግዚአብሔር ይቅርታ ሁሌ የማያቋርጥ ትልቅ ጸጋ ቢሆንም በመስቀል ላይ የገለጸው ይቅርታ ከሁሉም የላቀ ነው፡፡ ምክንያቱም በመስቀል ላይ የተፈጸመው ይቅርታ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘለዓለማዊ በመሆኑ፣ እንዲሁ በነፃ የተሰጠ ሳይሆን መለኮት በተዋሐደው ደሙ የተገኘ በመሆኑ፣ በከፊል ሳይሆን ሰማያውያንንና ምድራውያንን ሁሉ በአንድነት ያጥለቀለቀ በመሆኑና ለወደፊትም የኀጢአት ሁሉ ማስተስረያ አድርጎ ያቆመው የይቅርታ ሕግ በመሆኑ በመስቀሉ ላይ የሆነው ይቅርታ ከይቅርታ ሁሉ ይበልጣል፡፡

በመስቀል ላይ የተፈጸመው የዕርቅና የይቅርታ ጸጋ ፊተኞቹንና ኋለኞቹን ሁሉ ያካተተ በመሆኑ ድንበር የለሽ ይቅርታ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ የእግዚአብሔር ይቅርታ ምድርን መላ፤ ሰማያትም በእግዚአብሔር ቃል ጸኑ፤ ኀይላቸውም ሁሉ ከአፉ እስትንፋስ የተገኘ ነው ብሎ የሚያስተምረን ይህንን ለመግለጽ ነው፡፡ (መዝ. 32፥6)

ቅዱስ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ሁለተኛ የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊኮስ፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳትና ሜትሮፖሊታኖች፤
ክቡራንና ክቡራት የበዓሉ ተሳታፊዎች፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሌላው ክፍለ ዓለም በተሻለና በደመቀ ሁኔታ በዓለ መስቀልን የምታከብርበት ምክንያት እግዚአብሔር ለፍጡራኑ ከሠራው ሥራ ሁሉ ይልቅ በመስቀሉ የሠራው እጅግ የላቀና ሰውን ከሞተ ነፍስ የታደገ በመሆኑ ነው፡፡ ነገረ መስቀሉ ሁሉንም በእኩልነት ተቀብሎ ያስማማና አንድ ያደረገ፣ ሰላምንና ፍቅርን ያሰፈነ፣ በአምልኮተ ጣዖትና በብልሹ ሥነ ምግባር፣ በተሳሳተ እምነትና አስተሳሰብ ተበላሽቶ የነበረውን ዓለም ፍጹም ሰላማዊ ርትዓዊና ትሩፋዊ በሆነ ትምህርቱ ያጣፈጠ ነው፡፡

በዓለም ውስጥ የኢትዮጵያ ምእመናንን ያህል የመስቀልን ጣዕም የተገነዘበ የለም በሚያስብል ሁኔታ፣ ትእምርተ መስቀሉ በልብሳችን፣ በአካላችን፣ በቤታችን፣ በሥራ ዕቃዎቻችን፣ በጌጦቻችን፣ በዕለት ተዕለት ሥራችንና እንቅስቃሴአችን ሁሉ ሊኖር የቻለው፣ የቀደሙት ኢትዮጵያውያን አበው የመስቀሉን ጣዕም በነፍስ ወከፍ ኢትዮጵያዊ ኅሊና በሚገባ እንዲሠርጽ የሚያስችል ሥራ በመሥራታቸው እንደሆነ የማይካድ ነው፤ ለዚህም ማስረጃችን ጥዑም ለጒርዔየ ነገረ መስቀልከ የመስቀልህ ነገር ለጒረሮዬ ጣፋጭ ነው ብሎ ኢትዮጵያዊው ነባቤ መለኮት ቅዱስ ያሬድ ያስተማረው ትምህርት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ትክክለኛውን መስቀል ከተቀበረበት ቦታ ከጎልጎታ በዛሬው ዕለት በተከሠተው ተኣምር ምክንያት እንዲወጣ ካደረገ በኋላ በሂደት ወደ ኢትዮጵያ ሀገራችን እንዲገባ ማድረጉ የኢትዮጵያውያንን ፍቅረ መስቀል አይቶ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ በመሆኑም ኢትዮጵያን ከባዕድ ወራሪ፣ ከባዕድ አምልኮና ባህል የተጠበቀ፣ የነፃነት፣ የሃይማኖት፣ የአንድነት ኀይል የሆነ፣ በሥነ ምግባር የበለጸገ፣ ኵሩና ጨዋ የሆነ ፣ ለማንም ይሁን ለማን ያልተበገረ ሕዝብ በዚህች ምድር በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዲኖር ያደረገ፣ በሀገሪቱ መሐል ዙፋኑን ዘርግቶ የተቀመጠው የመስቀሉ ኀይል እንደሆነ ማንም ኢትዮጵያዊ ያውቃል፤ ዛሬ በዚህች ሰዓት በዚህ አደባባይ በተግባር እየገለጽነው ያለ ዐቢይ ትዕይንትም ይኸው ሐቅ ነው፡፡

ይህ ታላቅና በእግዚአብሔር በረከት የተመላ ሕዝብ በታቦተ ሕጉና በመስቀሉ ፊት ቆሞ ፈጣሪውን ሲለምን ያልተደረገለትና የማይደረግለት ኀይለ እግዚአብሔር የለም፡፡ በመሆኑም በየዓመቱ እንዲህ ባለ ሰልፍና ትዕይንት የምናከብረው የመስቀል በዓል ታማኙና ዘለዓለማዊው፣ ሁሉን ማድረግ የሚችል፣ የኀያላን ሁሉ ኀያል የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ይህንን ቅዱስ ሀገርና ሕዝብ ከሚታየውና ከማይታየው ፈተና እንዲጠብቅልን በጸሎትና በምስጋና በአንድነት ሆነን ለመማፀን ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በመንፈሳዊ ኀይል በኩል የደከመችበት ጊዜ ፈጽሞ ባይኖርም በኢኮኖሚ ዐቅሟ ግን ወደኋላ የቀረችበት ጊዜ ቀላል እንዳልሆነ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር እስከ ዳር በቊርጠኝነትና በሀገር ወዳድነት ተንቀሳቅሶ ባስመዘገበው ልማትና እድገት ስማችን እንደገና እንደጥንቱ እየገነነ እንደመጣ ሁላችንም እያየን ነው፡፡ ዛሬ የሀገራችን ልማትና እድገት በየአቅጣጫው ተፋፍሞአል፣ ዛሬ በሂደት የሚገኘው የልማትና የእድገት ግስጋሤያችን የኢትዮጵያ ከፍታ እውን ሆኖ ቀድሞ የነበረው ገናና ስማችንና ሥልጣኔአችን እስኪረጋገጥ ድረስ አጠናክረን መቀጠል አለብን፡፡ ከዚህ አንጻር የዘንድሮውን በዓለ መስቀል የምናከብረው ይህ የነፍስ ወከፍ ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ሕልም የሆነው ራእይ እውን እንዲሆን በመጸለይ ነው ፡፡

ቅዱስ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ሁለተኛ የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊኮስ፣
ብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳትና ሜትሮፖሊታኖስ፣ክቡራን ክቡራት

የዘንድሮ የመስቀል በዓላችን ልዩ የሚያደርገው የሶስተኛ ሺሕ ወይም ሚሊኒየም ዐሥረኛ ዓመት የልማትና የእድገት ጒዞአችን በምናስብበት ወቅት፣ እንደዚሁም እጅግ በጣም ውድ እኅት የሆነችው የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊኮስ ቅዱስ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ሁለተኛ በተገኙበት እየተከበረ ያለ መሆኑ ነው፡፡ የቅዱስነታቸው ጒብኝት የመልካም ገጽታችን፣ የታላቅነታችን፣ የልማታችንና የሰላማችን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሰላማችንንና አንድነታችንን ጠብቀን እስከተጓዝን ድረስ ፈላጊያችን አክባሪያችንና ወዳጃችን ብዙ ይሆናል፡፡ ሰላማችንን፣ አንድነታችንንና ወንድማማችነታችንን እንደ ዐይን ብሌን ጠብቀን ወደልማትና ሥራ ስንሰለፍ ብርቱዎች ነን፤ ስለዚህ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዳጅ ሰላምን መጠበቅ፣ ከበሽታ መራቅ፣ ልማትን ማፋጠን፣ እድገትን ማረጋገጥ ሊሆን ይገባል፡፡

በመጨረሻም፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመሉ በአጽንዖት ለማስተላለፍ የምንፈልገው ዐቢይ መልእክት ሕዝባችን ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔርን ድምፅ እርሱም “ ሰላም ለእናንተ ይሁን” የሚለውን ድምፅ ዘወትር እንዲሰማ ነው፤ ይህ ድምፅ የእድገቱና የድኅነቱ ዋስትና ነውና ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ድምፁን ያለማመንታት ሰምቶና ተቀብሎ፣ ከበሽታ አምጪ ተግባራትና ከሁከት ርቆ “የአትዮጵያን ከፍታ” በቀጣዮቹ ዓመታት እንዲያረጋግጥ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የመስቀል በዓል ያድርግልን፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም. የዘመን መለወጫ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

የዘመናትና የፍጥረታት ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ ሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት ወደ ዘመነ ማርቆስ ሁለት ሺሕ ዐሥር ዓመተ ምሕረት በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“አንሶስዉ እንዘ ብክሙ ብርሃን
ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን ተመላለሱ።”
(ዮሐ. 12፥35)

የብርሃን ጸጋ ለሰው ልጆች ወይም በአጠቃላይ ለፍጥረታት ሁሉ ከተሰጡ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ትልቁ ነው፤ ብርሃን የሥራ መሣሪያ ነው፣ ብርሃን የመልካም ነገር ሁሉ ተምሳሌት ነው፤ እግዚአብሔር ራሱ በባሕርዩ ብርሃን ከመሆኑም ሌላ በእርሱ ዘንድ የማይጠፋ ብርሃን እንዳለ በቅዱስ መጽሐፍ ተገልጾአል፤ የሰው ልጅ ከወዲያ ወዲህ፣ ከወዲህ ወዲያ ተንቀሳቅሶ፣ ነግዶ፣ አርሶ፣ ሠርቶ፣ ተምሮና አስተምሮ ለኑሮው የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማግኘት ብርሃን የግድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ጋር ሙሉ ጤና፣ ቀና የሆነ አእምሮ፣ ሰላምና ፍቅር ለሰው ልጅ ብልጽግና ወሳኝ ቦታ አላቸው፤ እነዚህ በሰው ልጅ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት ላይ ያላቸው ጸጋ እጅግ የላቀ በመሆኑ በቅዱስ መጽሐፍ አገላለጽ ብርሃን እየተባሉ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደዚሁም ዕድሜና መልካም ዘመን በተመሳሳይ አገላለጽ ብርሃን ተብሎ ይመሠጠራል፤ ምክንያቱም ብርሃን በሌለበት ሁኔታ ምንም ሥራ መሥራት እንደማይቻል ሰላማዊ ዘመን ከሌለም ልማትና እድገት ማስመዝገብ አይቻልምና ነው፤ በመሆኑም ዕድሜና ዘመንም ሌላው ታላቁ የእግዚአብሔር ብርሃን ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን ተመላለሱ” ሲል የዕድሜና የጊዜ ብርሃንነትን ማመልከቱ እንደሆነ ዐውደ ምንባቡ በግልጽ ያሳያል፤ ምክንያቱም እርሱ በዚህ ዓለም በመምህርነት የተገለጸበት ዘመን ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ በነበረበት ጊዜ የተናገረው ከመሆኑ ጋር ባላችው አጭር የትምህርት ዕድሜ ወይም ዘመን ሰዎች በእርሱ ብርሃንነት እንዲያምኑ የቀሰቀሰበትና ያስተማረበት ትምህርት ነው፡፡ በእርግጥም ላስተዋለውና በሥራ ለተጠቀመበት፣ ጊዜ ታላቁ ብርሃን ነው፤ ጊዜ ሲቀና ነገሩ ሁሉ ብርሃን ይሆናል፤ ጊዜው ከጨለመ ደግሞ ዙሪያው ሁሉ ጨለማ ይሆናል፤ ዕድሜያችን ወይም ዘመናችን በሕይወታችን ውስጥ ለልማትም ሆነ ለጥፋት ለጽድቅም ሆነ ለኀጢአት፣ ለትንሣኤም ሆነ ለውድቀት መሣሪያነቱ የታወቀ ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም የሚሠራውና የሚከናወነው በጊዜው ነውና፡፡ በዘመናት ውስጥ ብርሃናውያን የሆኑ ዓመታት እንደነበሩ ሁሉ ጽልመታውያን የሆኑ ዓመታትም በሀገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም እንደነበሩ እናውቃለን፡፡ እነዚህ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮች በየፊናቸው ለሰው ልጆች ያተረፉት ስጦታም በስማቸው ልክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ዘመናትን ብርሃናውያን ወይም ጽልመታውያን እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የሰው ልጅ ሚና ትልቅ እንደሆነ የማይካድ ነው፡፡

የሰው ልጅ የማስተዋልና የመቻቻል፣ የመታገሥና የመወያየት፣ የፍቅርና የስምምነት፣ የሰላምና የአንድነት ጠቃሚነትን ዘንግቶ፣ በስሜትና በወቅታዊ ትኲሳት፣ እንደዚሁም የእግዚአብሔርን የሰላም ድምፅ አልሰማ ብሎ በራስ ወዳድነትና በስግብግብነት ተሸንፎ ወደ ትርምስ ሲገባ ዘመኑ ጽልመታዊ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በሰው ችኩልና ደካማ አስተሳሰብ የተጨናነቀ ጽልመታዊ ዘመን ከውድመትና ከጥፋት በቀር አንዳችም ትርፍ እንደሌለው ከሀገራችን ተሞክሮ የበለጠ መምህር አይኖርም፡፡ በሌላ በኩል ሰዎች ከእርስ በርስ ግጭት ተላቅቀው ሰላምንና ፍቅርን፣ አንድነትንና እኩልነትን፣ መቻቻልንና መስማማትን፣ መወያየትንና መቀራረብን፣ ወንድማማችነትንና መከባበርን ያረጋገጠ፣ ትዕግሥትና አስተዋይነት የማይለየው የእግዚአብሔርን ድምፅ በመከተልና አእምሮን በማስፋት መኖር ሲጀመሩ ዘመኑ ብርሃናዊ እንደሚሆን፣ ልማቱና እድገቱም እንደሚፈጥንና እንደሚረጋገጥ አሁንም በሀገራችን ወቅታዊ ተሞክሮ ተረድተነዋል፤ ይህ ሁሉ እውነታ የሚያሳየው የዘመን ብርሃንነትና ጽልመትነት የሚወሰነው፣ እኛ ሰዎች በምናውጠነጥነው አስተሳሰብና በምናደርገው እንቅስቃሴ እንደሆነ ማስተዋል ተገቢ ነው፤ ለዚህም ነው ኀላፊነቱም ተመልሶ ወደ እኛ የሚመጣው፡፡

ጌታችንም ምርጫውንና ውሳኔውን ለእኛ ትቶ ብርሃን ስላላችሁ በብርሃን ተመላለሱ በማለት ገለጻውንና ትምህርቱን ብቻ መናገሩ ከዚህ የተነሣ እንደሆነ ማስተዋል ይገባል፡፡ ከእነዚህ ከሁለቱ የሚሻለንን መምረጥና መከተል የእኛ ፈንታ ነው፤ ምርጫችን ሰላምና አንድነት ከሆነ ዘመኑ ብርሃን ነው፤ ተቃራኒው ከሆነ ደግሞ የኋልዮሽ ጒዞ ይሆናል፤ ስለሆነም ምርጫችን ሰላምና አንድነት እንዲሆን ሁላችንም ተስማምተን መወሰን አለብን፡፡ ማንም ሰው ብርሃንና ጨለማ ጎን ለጎን ቀርበውለት የትኛውን ትመርጣለህ የሚል ጥያቄ ቢቀርብለት ያለማመንታት ብርሃኑን እንደሚመርጥ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ችግሩ ሰዎች ይህንን ግልጽና ጠቃሚ ምርጫ ተቀብለው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ብዙ የሚያታልሉና በድብብቆሽ የሚመላለሱ አካላት በመካከሉ ይገቡና ጨለማውን ብርሃን፣ ብርሃኑንም ጨለማ አስመስለው ሰውን ወደገደል መክተታቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ብርሃናዊና መልካም የሆነ ምርጫችንን ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደርጉታል፤ እኛ ሰዎች አእምሮአችንን በሚገባ መጠቀም ያለብን እዚህ ላይ ነው፤ ማለትም እኛው ራሳችን የሚጠቅመንና የማይጠቅመንን የመለየት ዐቅም ስላለን ዓቅማችንን ተጠቅመን ለዘላቂ ጥቅማችንና ለትክክለኛ ምርጫችን መወገን ይኖርብናል ማለት ነው፡፡

ሰዎች የሆን ሁላችን ባለ አእምሮዎች ሆነን ተፈጥረናል፤ አእምሮ ከእግዚብሔር ጋር የሚያመሳስለን ስለሆነ ከሀብት ሁሉ የበለጠ ሀብት ነው፤ ይህንን አእምሮአችንን ካዳመጥነውና ከተከተልነው ሐቁን አይስትም፤ አመዛዝኖ፣ ገምግሞ ለክቶ፣ ጠቃሚውን ነገር ከልባችን ውስጥ ቊጭ ያደርግልናል፤ ነገር ግን ትዕግሥትን፣ ማገናዘብን፣ ቆም ብሎ ማሰላሰልን፣ ምክንያታዊ መሆንን፣ ማመዛዘንን፣ ፈሪሀ እግዚአብሔርና ፈቃደ እግዚአብሔር መከተልን ይፈልጋልና እነዚህን እንደ ግብአት አድርገን ልናቀርብለት ይገባል፤ ይህንን መጠቀም ስንችል የዘመናችንና የዕድሜያችን ብርሃን ዋስትና ይኖረዋል፤ ጨለማም አያሸንፈውም፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤

ለዐሥር ዓመታት ያህል የተጓዝንበት የሦስተኛው ሺሕ ወይም ሚሊኒየም ዐቢይ ዘመን ለኢትየጵያ ሀገራችን ብርሃናዊ ዘመን የፈነጠቀበት ወቅት ነው፤ ምክንያቱም በዚህ ዘመን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያልተነካ ሀብታችን እርሱም የዐባይ ወንዝ ሀብታችንን ለመቋደስ የሚያስችል ግዙፍ የልማት ሥራ ተጀምሮ ወደ መጠናቀቅ እየተቃረበ ያለበት እጅግ ብርሃናዊ ዘመን በመሆኑ ነው፡፡ በሠለጠነው የምዕራቡ ዓለም ካልሆነ በቀር በአፍሪከ ምድር ለዚያውም በድርቅ፣ በረኃብና በጦርነት ትታወቅ በነበረችው ኢትዮጵያ ይሆናሉ ተብለው የማይታሰቡ እጅግ ግዙፍ የሆኑና የሕዝባችንን መሠረታዊ የእድገት ለውጥ የሚያረጋግጡ የኮንስትራክሽንና የኢንዱስትሪ፣ የትምህርትና የጤና ተቅዋማት በፍጥነት እየገሠገሡ መገኘት በዚህ ብርሃናዊ ዘመን የዕለት ተዕለት ትእይንት እንደሆኑ በዐይን እየታየ ነው፤ ይህ ጸጋ እንዲሁ ያለ መሥዋዕትነት የተገኘ ሳይሆን እኛ ኢትዮጵያውያን ከሁሉ በላይ ሰላምንና ልማትን መርጠን በአንድነት ወደ ብርሃናዊ አስተሳሰብ ስለገባን ነው፡፡ እግዚአብሔርም በብርሃን ተመላለሱ ያለው ይህንን ለማመልከት ነውና በዚህ ምክንያት ትክክለኛ ምርጫችንን እርሱ ስለባረከልን የልማትና የእድገት ተምሳሌት መሆን እንደቻልን አንሥተውም፡፡ ዛሬም ወደማንወደውና ወደማንመርጠው ጨለማ ሊከቱን የሚሹ እንደ ኤች አይ ቪ ኤድስና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንደዚሁም በሕዝባችን መካከል መለያየትና መቃቃር ሊያስከትሉ የሚችሉ አፍራሽ ድርጊቶች ብቅ ብቅ በማለት እየተፈታተኑን እንደሆኑ መዘንጋት የለበትም፤ እነዚህ ሁሉ በተግባር ያየናቸው የሕዝባችን ቀንደኛ ፀርና የጨለማ አበጋዞች፣ የልማታችንና የሰላማችን ዕንቅፋቶች ናቸውና ሕዝቡ በተለመደው ሃይማኖታዊና አርቆ ማሰብ ኀይሉ እንዲመክታቸው በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም፡ የዛሬ ዐሥር ዓመት “ታላቅ ነበርን ታላቅም እንሆናለን” በማለት ለሦስተኛው ሺሕ ወይም ሚሊኒየም ዐቢይ ክፍለ ዘመን የገባነውን ቃል በማደስ በአዲሱ ዓመት ካለፈው ዓመት በበለጠ ጠንክረን በመሥራት ልማታችንንና እድገታችንን በፍጥነት በማሳደግ፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታን ባለን የተሞክሮ አሠራር በመመከት፣ እንደዚሁም ሕገ ወጥ ዝውውርን፣ ሀገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ድርጊትን በማክሸፍ፣ በሃይማኖትና በሰላም መርሕ በመመራት አዲሱን ዘመን ብርሃናዊ እንድናደርገው አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

አዲሱ ዘመን የሰላም የፍቅርና የብልጽግና ያድርግልን፤ እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡