መስከረም 16 ቀን የ2009 ዓ.ም. በበዓለ መስቀል ላይ በአደባባይ የተሰጠ መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ከአራቱ የከተማችን መዓዝን የመጣችሁ ሕዝበ ክርስቲያን፤ እንደዚሁም በሀገር ውስጥና በውጭ ሆናችሁ የበዓለ መስቀሉን ሥነ በዓል በመከታተል የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በመስቀሉ ተሰቅሎ ባፈሰሰው ደሙ ሰማያውያንና ምድራውያንን አስታርቆ ፍጹም ሰላምን ያጎናጸፈን ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ መስቀል በሰላም አደረሳችሁ።

‹‹ወለጽልእ ቀተሎ በመስቀሉ
ጥልንም በመስቀሉ ገደለው።››
(ኤፌ. 2፥16)

ቅዱስ መጽሐፍ በግልጽ እንደሚነግረን ዓለም እንደተፈጠረ ብዙም ሳይቆይ የጥል ግንብ እንደተገነባ ነው፤ የጠቡ መነሻ የሆነው መሠረታዊ ችግር ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ፣ ታማኝ ሆኖ አለመገኘት፣ ሕግን መጣስ፣ ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ የዲያብሎስን ምክር መቀበል ነው፤ (ዘፍ.2፡16-17፤ ዘፍ.3፡1-8)፡፡ ይህ አድራጎት የተፈጸመው በአባታችን አዳምና በእናታችን ሔዋን ሲሆን ድርጊቱ በፈጣሪና በፍጡራን፣ እንደዚሁም በፍጡራንና በፍጡራን መካከል ጽኑ የሆነ ጥል ፈጠረ፤ ከባድ የሆነ መርገምትና መለያየትም አስከተለ (ዘፍ. 3፥10-24)፡፡

ጥል ካለ ዘንድ መለያየቱም እየሰፋና እየከፋ መሄዱ የማይቀር ነውና ከአዳምና ከሔዋን የተገኘ የሰው ዘር በሙሉ እርስ በእርስ መጣላቱንና መለያየቱን በስፋት ቀጠለበት፣ በዚህም ሂደት የሰው ልጅ ሕይወት ጣዕም የለሽና መራራ ሆነች፣ ሁሉም በአምልኮ ባዕድና በድንቊርና ተዋጠ፤ ቀለም፣ እምነት፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ መልክዐ ምድር ከባቢያዊ ባህል፣ ሀብት፣ ሥልጣን፣ ዕውቀት የመሳሰሉ ሁሉ ሰውን እርስ በርሱ ለያይተው ለከፋ ጕዳት ዳረጉት፤ እነዚህ ሁሉ ኀጢአት ወልዳ ያሳደገቻቸው የአለመታዘዝ ውጤቶች እንጂ ከጥንተ ፍጥረት የተገኙ አይደሉም፡፡ የሰው ዘር በአጠቃላይ ከአዳም ውድቀት አንሥቶ እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ድረስ በዚህ የጨለማ ሕይወት ተውጦ ስለነበረ ቅዱስ መጽሐፍ “በጨለማና በሞት ጥላ የሚኖር ሕዝብ” ብሎ ይገልጸዋል፤ (ኢሳ. 9፡2)፡፡ ያ ዘመን የሰው ዘር በአጠቃላይ በሰማይም ሆነ በምድር፣ በነፍስም ሆነ በሥጋ ከባድ የሆነ የሞት ቅጣትን ያስተናገደበት ዘመን በመሆኑ ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኵነኔ ተብሎ ተገልጾአል፤ (ሮሜ 5፥12-19)፡፡ ይሁንና ምሕረት፣ ይቅርታ፣ ገደብ የለሽ ፍቅርና አዘኔታ ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር አምላክ አንድ ቀን ሰውን ከዚህ የሞት ቅጣት እንደሚታደገው ከመጀመሪያው አንሥቶ ተስፋውን ያሰማ ነበር፤ (ዘፍ. 3፥15፤ ዘፍ. 22፡፥6-18፣ ኢሳ. 53፥4-12፤ ዳን. 9፥24-27)፡፡

ከዘመን በኋላ እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት የባሕርይ ልጁ የሆነ ቀዳማዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድን ወደዚህ ዓለም ላከ፤ እሱም መጥቶ ሥጋችንን ተዋሐደ፤ የጥል ምክንያት የሆነውን ኀጢአትን ያጠፋ ዘንድ የኀጢአት መካካሻ ሆኖ በመስቀል ላይ መሥዋዕት ሆነ፤ በቀዳማዊ አዳም አለመታዘዝ የተበደለ እግዚአብሔር በዳግማዊ አዳም (በክርስቶስ) ድንቅ መታዘዝ ተካሰ፤ (ሮሜ 5፥19፤ 2ቆሮ. 5፥19፤ ዕብ. 5፥7-8)፡፡ በመሆኑም በዚህ መሥዋዕት ምክንያት እግዚአብሔር የዓለሙን ወይም የሰውን ኀጢአት ይቅር ብሎ የምሕረት በሩን ከፈተ፤ በሰውና በእግዚአብሔር የተገነባው ጥል ፈራርሶ በጥምቀትና በቅዱስ ቁርባን አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር የአባትና የልጅ የሆነ ግንኙነትን መመሥረት ተቻለ፤ (ኤፌ2፡13-16፤ ዮሐ.6፡56፤ ሮሜ.6፡3-4)፡፡ በቀለም፣ በዘር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት ወዘተ ተፈጥሮ የቆየውን የሰው ከሰው መለያየት ቀርቶ ሁሉም በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምኖ እንዲድን የሁሉም መዳኛ የሚሆን ስም ሰጠ፤ ‹‹ከሰማይ በታች ከዚህ ስም በቀር የምንድንበት ሌላ ስም የለምና›› ተብሎ እንደተጻፈው፤ (የሐዋ.ሥራ 4፥9-12)፡፡

ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ያህል ሥር ሰዶ የነበረው የጥል ግድግዳ በመስቀሉ ላይ በተፈጸመው የዕርቀ ሰላም መሥዋዕትነት ስለፈራረሰ ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት የሚከለክለን የለም፣ የኀጢአት ግንብ ቢኖርም እንኳ በንስሓ ይናዳል፤ ዛሬ በቀለም፣ በዘር፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በዕውቀት፣ በሀብት፣ በሥልጣን ወዘተ ከእግዚአብሔር ምሥጢረ ድኅነት የሚከለከል የለም፣ የሚጠየቀው አንድና አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ማመንና ቀጥሎም በሥነ ምግባር ተወስኖ መኖር ነው።

ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ጸንቶ የቆየው የጥል ግድግዳ የፈራረሰው በጌታችን በአምላካችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት ሲሆን፤ መሥዋዕትነቱም የተፈጸመው በመስቀል ላይ ነው፤ ለዚህም ነው ‹‹ጥልን በመስቀሉ ገደለ›› ተብሎ እየተነገረን ያለው፤ ሁላችንም እንደምናውቀው መግደል ማለት ማጥፋት፣ ህልውናን ማሳጣት ማለት እንደሆነ ለሁሉም ግልጽ ነው፤ከዚህ አንጻር ክርስቶስ በመስቀሉ ጥልን ገደለ ሲባል በፈጣሪና በፍጡራን መካከል የነበረውን የጥል ህልውና ጨርሶ አጠፋ ደመሰሰ ማለት እንደሆነ እናስተውላለን፤ ይሁንና በመስቀል የተፈጸመው ምሥጢር ጥልን ማጥፋት ብቻ አይደለም ዕርቅን፣ ሰላምን፣ አንድነትንና ነፃነትን በአጠቃላይ በመስቀል ላይ በተፈጸመው መሥዋዕትነት ተከናውኖአል፤ (ሮሜ 5፥10-11፣ 1ተሰ. 2፥13-15)፡፡ በመሆኑም መስቀልን ማሰብና ማክበር ሁለት ነገሮችን እንድናስታውስ ያስገድደናል፤ ይኸውም፡ (1) በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ያዳነን ክርስቶስንና የክርስቶስ ፍቅርን፣ (2) በመስቀል ላይ የተፈጸመው የድኅነታችን መሥዋዕትን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ስለሆነም መስቀሉን ማሰብ ማለት ክርስቶስንና የክርስቶስን የማዳን ምሥጢር ማሰብ ማለት እንደሆነ አንዘንጋ፤ መስቀል ሰላምን፣ አንድነትን፣ ነፃነትን ዕርቅን የሚሰብክና የሚያስተምር፣ ስለድኅነተ ሰብእ የሚመሰክር፣ የእግዚአብሔር የማዳን ዐርማ፣ የድልና የአሸናፊነት ምልክት ነው፤ ኀጢአትና ሞት ተሸንፈውበታልና (1ቆሮ. 15፥55-57)፡፡ ከዚህ አኳያ የክርስቶስ መስቀል ተራ ነገር ሳይሆን በስተጀርባው ነገረ ክርስቶስን ያዘለ በመሆኑ ክርስቶስንና የማዳን ተግባሩን እንደዚሁም የምንድንበትን መንገድ የሚያስተምረን ቅዱስ የሆነ ትእምርተ አድኅኖ ነው፡፡

በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ክፍለ ዘመናት የነበሩ አይሁዳውያንና ክርስቲያኖች የተጋጩበት ዐቢይ ነጥብ በዚህ መሠረታዊ ምክንያት ነው፤ ሁለቱም ክፍሎች ትእምርተ መስቀሉ ክርስቶስን በቀጥታ እየሰበከ እንደሆነ አልሳቱትም፤ በመሆኑም አይሁዳውያኑ ክርስቶስን መስበኩ እንዲያቆም ፈልገው መስቀልን በጒድጓድ ሲቀብሩት፣ ክርስቲያኖቹ ደግሞ መስቀሉ ከተቀበረበት ወጥቶ ክርስቶስን መስበክ አለበት በማለታቸው በመካከላቸው ቅራኔ ተፈጥሮአል፡፡ ይሁንና “የማታ ማታ እውነታ ይረታ” እንዲሉ፤ ምንም ቢሆን እውነት መርታቱ አይቀርምና መስቀሉ ከተቀበረበት ወጣ፤ እውነትም ረታ፤ እኛም ዛሬ በከፍተኛ ድምቀት የምናከብረው በዓል መስቀሉ ከተቀበረበት ጒድጓድ የወጣበትን ለማሰብ ብቻ ሳይሆን መስቀሉ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መድረክ አግኝቶ የክርስቶስን አዳኝነት ለዓለም ሕዝብ እንዲሰብክ፣ እንዲያስተምርና እንዲመሰክር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርም ጭምር ነው፡፡

ምስጋና ለኀያሉ አምላካችን ለእግዚአብሔር ይሁንና ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመናት ጥረት በዘመናችን እውን ሆኖ እነሆ መስቀለ ክርስቶስ ዓለምን በአጠቃላይ ለመስበክ የሚያስችል ምቹ መድረክ አግኝቶአል፡፡ ይኸውም በዓለ መስቀል በኢትዮጵያ ስም በተባበሩት የዓለም መንግሥታት ድርጅት መመዝገቡ ነው፤ በዚህም ለዚህ ታላቅ ዕድል ያበቃንን እግዚአብሔርን እጅግ አድርገን እናመሰግነዋለን፤ እንግዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀልን በዓል በከፍተኛ ሁኔታ የምታከብርበት ዋና ምክንያት የጥል ግድግዳን የሚያፈርስ፣ መለያየትን የሚንድ፣ በምትኩ ደግሞ ሰላምን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ መተማመንን፣ መቻቻልን፣ መተጋገዝን ፍጹምና ዘላቂ የሆነ ፍቅርን የሚያሰፍን በመሆኑ ነው፤ በተለይም ደግሞ ሰላምን በዋናነት ማግኘት የሚቻለው ከመስቀል አስተምህሮ በመሆኑ ነው፤ መስቀል ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› ብሎ ለገዳዮች ምሕረትንና ይቅርታን እየለመነ ፍጹም ፍቅርን ይሰብካል፤ መስቀል በንስሓ ለቀረበ በደለኛ ‹‹ዛሬውኑ ከኔ ጋር በገነት ትኖራለህ›› እያለ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ እንዲኖር ይጋብዛል፤ መስቀል ለሰው ድኅነት ሲባል ራስን አሳልፎ በመስጠት ፍጹም ድኅነትን ይሰብካል፤ ሌላም ለሰው ልጅ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ የሰላም ትምህርቶችን ያስተምራል፤ በትምህርቱም በነፍስና በሥጋ ያድናል፡፡

ዛሬ በሀገራችን አልፎ አልፎ የሚከሠተው የጥል መንፈስ ያለበት የሚመስል ክሥተት የመስቀሉ ስብከትና ትምህርት በቅጡ ካለማጤንና ካለማስተዋል የተነሣ እንደሆነ መገንዘብ አለብን፤ የመስቀልን ምልክት በአካሉ፣ በአንገቱ፣ በግንባሩና በልብሱ የተሸከመ ሰው ወንድሙን አይጠላም፣ መናናቅንም አያስተናግድም፣ መከፋፈልን፣ መለያየትን፣ መነታረክን፣ መጨቃጨቅንና ራስ ወዳድነትን የመሳሰሉ የዲያብሎስ የጥፋት ሠራዊት መስቀልን ባነገበ ክርስቲያን ዘንድ ቦታ የላቸውም፡፡ የመስቀሉ ትምህርት በእኛ አስተማሪነት የሰላም ምሥጢርነቱን በዓለሙ ሁሉ ለማዳረስ በምንሮጥበት በአሁኑ ጊዜ እኛው ራሳችን የመስቀል ትርጒም ሰላምና ፍቅር መሆኑን መረዳት አቅቶን በጥላቻ ዐይን የምንተያይ ከሆነ ስለመስቀል ማስተማር እንችላለን ብለን ሁላችንም በዓለም ሕዝብ ፊት ቃል የገባንበት የማስተማር ብቃታችን ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፤ መስቀል የገደለውን ጥል እንደገና ስበንና ጎትተን እንዳናመጣው ማሰብና መጠንቀቅ አለብን፡፡ ባለፉት ወራት በሀገራችን ውስጥ የተከሠቱ ግጭቶች ቤተ ክርስቲያናችንን ያሳዘኑና ያሳሰቡ መሆናቸውን ካሁን ቀደም ቤተ ክርስቲያናችን በየሚድያውና በየዐውደ ምሕረቱ በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷ አይዘነጋም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ሁሉም ኢትዮጵያውያን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከማእዷ ተቋዳሾች ናቸውና ሁሉም ኢትዮጵያውያን ልጆቿ እንደሆኑ በጽኑ የምታምንበት ጉዳይ ነው፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ነፃነትና እኩልነት አክብራ ከሦስት ሺሕ ዘመናት በላይ የሀገር አለኝታ ሆና የኖረችበት ምሥጢርም ይኸው ከእግዚአብሔር የተቀበለችው ሕዝብን አስማምታ የመጠበቅ አደራ በሚገባ መወጣት በመቻሏ እንደሆነ የሚካድ አይደለም፡፡

ስለሆነም የቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም ልጆችዋን በሰላምና በፍቅር ተንከባክባና አስማምታ ማገልገል ነውና የሀገራችን ሕዝቦች አንድነትና ነፃነት መከባበርና መተማመን፣ መቻቻልና መስማማት ተጠብቆ ይቀጥል ዘንድ እንደዚሁም የሀገራችን ሕዝቦች አንጸባራቂ ታሪክ ባህልና ትስስር በወቅታዊ ትኵሳት ፈተና ላይ እንዳይወድቅ ኢትዮጵያን ከልብ የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሰላማዊ፣ በወንድማዊና በሀገራዊ ፍቅር ችግሮችን በጋራ ውይይት እየፈታ በቆየው የወንድማማችነት መንፈስ ልማቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩሉን ያደርግ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታሳስባለች፡፡

በመጨረሻም፡ ሕዝባችን ከሰላምና ከፍቅር፣ ከመከባበርና ከመተማመን፣ ከወንድማማችነትና ከመፈቃቀር ጥቅም እንጂ ጕዳት እንደሌለ በጥልቀት የሚገነዘበው ነው፤ ኢትዮጵያ ሀገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታም ይህንን ሐቅ ያረጋገጠ ነው፤ በሰላምና በፍቅር ስንኖር ዐባይን የመሰለ ታላቅ ወንዝ መገደብ ችለናል፤ የሕዝቡ አንድነት ፍቅርና ሰላም እስከተጠበቀ ድረስ እንደአባቶቻችን ሌሎች ብዙ አስደናቂ የሆኑ የልማት ሥራዎችን ከመሥራት የሚገድበን እንደሌለ በሚገባ ተገንዝበናል፤ ስለሆነም የመስቀል መልእክትም፣ ትምህርትም ሰላምና ሰላም ብቻ ነውና የሀገራችን ሕዝቦች ከምንም በላይ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ረገድ የማያወላውል አቋም እንዲይዙ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

መስከረም 1 ቀን 2009 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ርእሰ ዐውደ ዓመት መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

ዘመናትና ዓመታት የማይቈጠሩለት እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከ2008 ዓ.ም.ዘመነ ዮሐንስ ወደ 2009 ዓ.ም. ዘመነ ማቴዎስ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ ፡፡

‹‹ወእስምያ ለዓመተ እግዚአብሔር ኅሪተ፤ የተመረጠችውንና የተወደደችውን የእግዚአብሔር ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል›› (ኢሳ.61፡2፤ ሉቃ.4፡19)፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው እንደ ሌላው ሁሉ ዓመትም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፤ ዓመት የጊዜ መለኪያ ነው፤ ጊዜም የሥራ መሣሪያ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓመታትን ለፍጡራኑ ሲሰጥ ለሥራ፣ ለኑሮ፣ ለምግብና ለጤና ወዘተ በሚያመች አኳኋን በተለያዩ ሐውዘ አየራት ከፋፍሎና አመቻችቶ መስጠቱ ዓለም በእርሱ መግቦት የሚመራ መሆኑን ይበልጥ ያጎላዋል፡፡ ከዚህም ጋር ጊዜያትን ለመለካት የሚያስችሉ መገብተ ብርሃን በጠፈረ ሰማይ ፈጥሮ ሰው በእነርሱ እየታገዘ ጊዜን በመለካት ለሥራውና ለኑሮው እንዲጠቀምባቸው አድርጎአል፡፡ ይህንንም በቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔርም ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ለምልክቶች፣ ለዘመናት፣ ለዕለታትና ለዓመታት መለያ ይሆኑ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ አለ›› በማለት በግልጽ አስቀምጦታል (ዘፍ. 1፥14)፡፡ ስለሆነም ሰው ቀንን በብርሃነ ፀሓይ፣ ወርን በብርሃነ ወርኅ፣ ወቅትን በብርሃነ ከዋክብት፣ ወዘተ. እየለካ ወቅቱን በመዋጀት ለእርሻ ተግባሩ ማለትም ለአዝርእቱ ለአትክልቱ፣ ለፍራፍሬው ምቹ ወቅት የትኛው እንደሆነ በመለየትና በማወቅ በግብርና ተግባር በሚገባ እንዲጠቀምባቸው አስችሎታል፡፡ በሌላም በኩል እግዚአብሔር ለአበው የሰጠው ተስፋ – ድኅነት ማለትም ዘመነ ሥጋዌ ወይም ዘመነ ክርስቶስ በዘመን ቀመር ስሌት አሠራር መቼ እንደሚሆን ቅዱሳን ነቢያት በኊልቈ ዓመታት ሲቈጥሩ፣ ሲከታተሉና ሲጠብቁ እንደነበሩ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በብዙ ቦታ ተጽፎአል።

በተለይም ነቢዩ ዳንኤል በደልና ኀጢአት የሚደመሰስበት ዘመነ ክርስቶስ ሊደርስ እርሱ ከነበረበት ዘመን አንሥቶ ሰባ ሱባዔ እንደቀረው በግልጽ ጽፎአል፤ በትንቢቱ መሠረትም ተፈጽሞአል፤ (ዳን. 9፥24-27)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህ ሱባዔ ሲፈጸም የሆነውን ነገር ሲገልጽ “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፤ ከሴትም ተወለደ ብሎአል” /ገላ. 4፡4/ ፡፡ ከዚህም አኳያ እግዚአብሔር ለማዳን ሥራ የመረጠው ወይም ለይቶ ያስቀመጠው ዓመት እንዳለ ከዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህም ዓመት ምርጥ የሆነ የእግዚአብሔር ዓመት ተብሎ ተገልጾአል፡፡ ቅዱሳን ነቢያት እግዚአብሔር በገለጸላቸው ምሥጢር መሠረት የተወደደው፣ የተመረጠውና ምሕረት እንደዝናም የሚዘንብበት የእግዚአብሔር ዓመት እርሱም ዘመነ ክርስቶስ እንደሚመጣ ብቻ ሳይሆን መቼ እንደሚመጣ ጭምር ዓመታቱን በትክክል እየቀመሩና እየቈጠሩ ሲናገሩና ሲያስተምሩ መኖራቸው የዘመናት ቊጥር በሃይማኖት ዘንድም የላቀ ተፈላጊነት እንዳለው ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔር የተናገረውን የማያስቀር ታማኝ አምላክ ነውና የተቈጠሩት ዓመታት በደረሱ ጊዜ፣ የዛሬ ሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመት ልጁን ወደዚህ ዓለም በመላክ ዓለሙን ከፍዳ ኀጢአት ታደገው፡፡ በመሆኑም በተጠቀሰው ዘመን ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ መሥዋዕት ሆኖ የዓለምን ዕዳ-ኀጢአት በመሸከም የሰው ልጅን በምሕረቱ ስለተቀበለው ከልደተ ክርስቶስ ወዲህ ያለው ዘመን ምሕረተ እግዚአብሔርን ለማሰብና ለማወጅ ሲባል ‹‹ዓመተ ምሕረት›› ወይም እንደ ነቢዩ እንደ ኢሳይያስ አገላለጽ “የተመረጠ የእግዚአብሔር ዓመት” ይባላል፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን በክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት ከመጀመሪያው ምእተ-ዓመት መጀመሪያ አንሥቶ ምሕረተ እግዚአብሔርን ገንዘብ ካደረጉ ሀገራት መካከል የመጀመሪያዎቹ ነንና ምሕረቱን ተቀብለን በዘመን አቈጣጠራችን ላይ ‹‹ዓመተ ምሕረት›› እያልን ምሕረተ እግዚአብሔርን ስናስታውስና ስናውጅ እንኖራለን፡፡

ዘመን የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሆነ ቀደም ብሎ ከላይ ተገልጾአል፤ የእግዚአብሔር ጸጋ እንደመሆኑም መጠን በጥንቃቄና በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፤ እግዚአብሔር ዘመናትን፣ ዓመታትንና ወራትን የሚሰጠን ለሃይማኖት ማጽኛ፣ ለሥነ ምግባር ማበልጸጊያ፣ ለንስሓ ማጎልበቻ፣ ለእድገት፣ ለብልጽግና፣ ለልማት፣ ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለአንድነትና ለስምምነት በአጠቃላይ የጎደለንን ለመሙላት ያጣነውን ለመተካት፣ የተስተካከለ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት እንዲኖረን ለማስቻል እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡

በመሆኑም ጊዜ ባለፈው አሮጌ ዘመን የጎደለብንን ሁሉ በአዲሱ ዘመን ለመሙላት እንድንችል በእግዚአብሔር የተሰጠን ልዩ ጸጋ ነውና በሥራ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ክፍለ ዘመናት ያመለጧት ብዙ ነገሮች እንዳሉ የሚታወቅ ነው፤ ይሁን እንጂ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ቀድሞ ያመለጧትን ነገሮች ለመሙላት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ መገኘቷና በዚህም ያመጣችው ለውጥ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ ይህም የእግዚአብሔር ጸጋ ነውና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ኢታስትት ጸጋሁ ዘላዕሌከ፤ በአንተ ያለውን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል” እንዳለው የተሰጠንን ጸጋ-ልማት በጥቃቅን ነገሮች ልናደናቅፈው አይገባም፡፡

አሁን ባለንበት ዘመን የተገነዘብነው ዐቢይ ቁም ነገር ቢኖር ሰላም የልማት ቊልፍ መሣሪያ መሆኑን ነው፤ በሀገራችን እየፈነጠቀ ያለው የእድገት ጮራ የሰላም ውጤት እንጂ የሌላ አይደለም፡፡ ከዓለም ተሞክሮ ልምድ ብንወስድም አሁን በከፍተኛ የእድገት ጣራ ላይ የሚገኙ ሀገራት የልማታቸው ምሥጢር የሰላምና የአንድነት መረጋገጥ እንደሆነ ማስተዋሉ አይከብድም፡፡ ስለሆነም ያለ ሰላም ልማትና እድገት ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለምና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለራሱ ልማት ሲል ለሰላም ጠበቃ መሆን አለበት፡፡ ባለፈው ዓመት ከዛሬ ሠላሳ አንድ ዓመታት በፊት ካጋጠመን ድርቅ ያልተናነሰ ከባድ ድርቅ ያጋጠመን ቢሆንም የሀገራችን ሕዝቦች ሰላማቸውንና አንድነታቸውን ጠብቀው ባስመዘገቡት እድገት ምክንያት ሀገራችን ችግሩን በራስዋ ዐቅም መቋቋም መቻሏ የሰላምና የአንድነት ጥቅም እንዲሁም እነርሱን ተከትሎ የተገኘው የእድገት ጣዕም ምን ያህል እንደሆነ የተገነዘብንበት ዓመት ሆኖ አልፎአል፡፡ስለሆነም አሁንም በተመረጠውና በተወደደው የእግዚአብሔር ዓመት ውስጥ ሆነን ዛሬ በምንጀምረው አዲስ ዓመት እግዚአብሔር ቸርነቱን አብዝቶልን የዝናሙ ስርጭትና የእህሉ ቡቃያ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ ተስፋ ሰጪ ሆኖ ስለሚታይ፣ ሕዝቡ በዚህ ተነቃቅቶ ሰላሙንና አንድነቱን በመጠበቅ የበለጠ ልማትና እድገት ለማስመዝገብ ጠንክሮ እንዲሠራ፣ እንደዚሁም ከድህነትና ከሰላም ዕጦት የበለጠ ሌላ ጠላት እንደሌለው ሕዝቡ ተገንዝቦ በአዲሱ ዓመት አለመግባባትን በውይይት፣ ድህነትን በልማት ለማሸነፍ በሁሉም አቅጣጫ እንዲረባረብ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ዘመኑ የሰላም፣ የአንድነትና የልማት ያድርግልን፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ፤ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

መስከረም 2 ቀን 2009 ዓ.ም ርእሰ ዐውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላ ሀገረቱ ጸሎት እንዲደረግ መመሪያ አስተላለፉ።

በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ተጠብቆ የቆየውን እና በየዓመቱ የሚከናወነውን የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር የዘንድሮ ዘመን መለወጫ በዓለ ቅዱስ ዮሐንስም መስከረም 2 ቀን 2009 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኀላፊዎች እና አጠቃላይ ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኀላፊዎችና ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች መዘምራንና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት በመንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት ሲከበር ቅዱስነታቸው በቃለ ምዕዳናቸው በዋናነት የሰላምን አስፈላጊነት በስፋት አትተው ሁሉም የሰላም ሐዋርያ ሆኖ በክርስቶስ መሾሙን አስረድተዋል፡፡ “ሰላም የምናመጣውም ሆነ የምናሳጣው እኛ ነን፤ ሰላም በእጃችን ሳለ እንደ ቀላል እንቈጥረዋለን ስናጣው ግን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንረዳለን፤ የሰላም ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላሙ ሰጥቶና፤ ይህ የክርስቶስ ሰላም በመላ ሀገራችን እንዲሁም በመላ ዓለማችን ጸንቶ እንዲኖር ሁላችንም የሰላም ሐዋርያት፣ የሰላም መምህራን፣ የሰላም መልእክተኞች በመሆን የሚጠበቅብንን መንፈሳዊ ኀላፊነት መወጣት አለብን” በማለት የሰላምን አስፈላጊነት በስፋት አትተው በየደረጃው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የሰላም ሐዋርያት ሆነው ሕዝቡን እንዲያገለግሉ አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡ በመቀጠልም ያለፈውን ዓመት የነበረውን የሀገራችን የድርቅ ችግር አስታውሰው እግዚአብሔር የልጆቹ ጸሎት የሚሰማና ለልጆቹ የሚራራ ርኅሩኅ አምላክ ስለሆነ ያንን ድርቅ አሳልፎ ሀገራችን በሐመልማል በረከት ጎብኝቷል በማለት ያለውን ወቅታዊ የሀገራችን የአየር ጸባይ ካስረዱ በኋላ ይህ አሁን የምናየው ልምላሜ ከፍሬ እንዲያደርስልን እና እኛ ከማናውቀው መቅሠፍት ሁሉ ሰውሮ የተባረከ ዘመን እንዲያደርግልን አሁንም ጸሎት ስለ ሰላም፣ ስለ አትክልቱ እና አዝርዕቱ፣ ስለ ሕዝባችን ፍቅር እና አንድነት፣ ስለ ዓለም ሰላም ሁሉ በማሰብ ዐውደ ዓመቱን በጸሎተ ምሕላ እንዲጀመር በማለት ለሁለተኛ ጊዜ የጸሎተ ምሕላ ሱባኤ እንዲያዝ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡