ሚያዝያ 27 ቀን እስከ 30 ቀን 2007 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቍጥር 164 ላይ በተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ ይካሄዳል፡፡ ከሁለቱ አንዱ ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን በዕለተ ረቡዕ የሚውለው የርክበ ካህናት ጉባኤ ነው፡፡

በመሆኑም የርክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሚያዝያ 27 ቀን ከሰዓት በኋላ በጸሎት ተከፍቶአል፡፡ በመቀጠልም ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባውን በጸሎትና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የመክፈቻ ንግግር ተጀምሮ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ ሰንብቶአል፤ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችንም አስተላልፎአል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለአራት ቀናት ያህል ባካሄደው ቀኖናዊ ጉባኤ፤ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚጠቅሙትን፤ ለልማትና ለሰላም የሚበጁትን፤ ከሀገር ውጭ ለሚገኙና በሀገር ውስጥ ላሉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁለንተናዊ ሕይወት መጠበቅ የሚያስችሉትን ርእሰ ጉዳዮች በማንሣት በስፋትና በጥልቀት አይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፎአል፡፡

1. ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በጉባኤው መክፈቻ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ሕይወት የቃኘ የሀገራችን እድገትንና የሰላም አስፈላጊነትን በስፋት የገለጸ በመሆኑ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡
2. ምልአተ ጉባኤው በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበውን ዓመታዊ የሥራ መግለጫ ሪፖርት አዳምጦ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡
3. ምንም ጥፋትና በደል ሳይኖርባቸው ክርስቲያኖች በመሆናቸው ብቻ በሊቢያ ሀገር አይ ኤስ በተባለ የአሸባሪዎች ቡድን በግፍና በሚዘገንን ሁኔታ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችንና የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በሟቾቹ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ተወያይቶ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ምልአተ ጉባኤው ያለውን ሁኔታ በጥልቀት ከተረዳ በኋላ ሟቾቹ የዘመኑ ሰማዕት እንዲባሉ ተስማምቶ ወስኗል፡፡
4. እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ የተሠዉት 30 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ልጆቻችን እና እንደ አውሮፓውያን አቈጣጠር የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በሊቢያ የተሠዉት 21 የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ክርስቲያኖች በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ሲኖዶስ የሰማዕትነት ክብር የተሰጣቸው ስለሆነ፣ የሁለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት ተብለው በአንድነት እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡
5. በልዩ ልዩ ምክንያት ከኢትዮጵያ ሀገራቸው ወጥተው በባዕድ ሀገር የሚገኙትንና ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከልና ለማቋቋም ቤተ ክርስቲያናችን መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት በመቀናጀት አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርግ፣ ይህን በተመለከተ ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያናችን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንም ርዳታ ሰጪዎችን በማስተባበር ኀላፊነቱን ወስዶ በንቃትና በትጋት አንዲሠራ ጉባኤው ወስኖአል፡፡
6. ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ አምስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኗን ቅዱስ ሲኖዶስ አውስቶ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን በጸሎት እንድትተጋ ጉባኤው መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
7. ኢትዮጵያ ሀገራችን ለብዙ ዘመናት ተጭኖአት ከቆየ የድህነት አረንቋ በተጨማሪ የእርስ በርስ ግጭት ጥሎባት ባለፈው ጠባሳ ክፉኛ የተጎዳች ብትሆንም በተገኘው ሰላም ምክንያት ባሳለፍናቸው ዓመታት እየታዩ ያሉ የልማትና የዕድገት፣ የእኩልነትና የአንድነት እመርታዎች የሰላምን ጠቃሚነት ከምንም ጊዜ በላይ መገንዘብ የተቻለበት ስለሆነ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም በላይ ሰላሙንና አንድነቱን አጽንቶ በመያዝ ሀገሩን ከአሸባሪዎችና ከጽንፈኞች ጥቃት ነቅቶ እንዲጠብቅ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፤
8. ሀገራችን ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና የካፒታል እጥረት እንደዚሁም በሀገር ውስጥ ሠርቶ የመበልጸግ ግንዛቤ ማነስ ካልሆነ በቀር በተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በማናቸውም መመዘኛ ከሌላው የተሻለች እንደሆነች የታወቀ ስለሆነ፤ ወጣቶች ልጆቻችን ወደሰው ሀገር እየኮበለሉ ራሳቸውን ለአደጋ ከሚያጋልጡ በሀገራቸው ሠርተው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ኅብረተሰቡም ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ በሰፊው እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ መልእክቱን አስተላልፏል፤
9. ለሀገራችንና ለሕዝቦቻችን ችግሮች ቍልፍ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ልማትን በማጠናከርና እድገትን በማረጋጋጥ ድህነትን ማስወገድ ስለሆነ ሕዝባችን ይህን ከልብ ተቀብሎ በየአቅጣጫው የተጀመሩትን የልማት ሥራዎች በመደገፍ ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች እኩል ለማሰለፍ የሚደረገውን ሀገራዊ ርብርቦሽ ለማሳካት በርትቶ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፤
10. በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በየቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ሁሉ የአረንጓዴ ልማትና የራስ አገዝ ልማት በማካሄድ ልማትን እንዲያፋጥኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፎአል፡፡
11. በውጭ ሀገር ከሚገኙ አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው የዕርቀ ሰላም ድርድር ለሀገራችን ልማትና ለሕዝባችን አንድነት የሚሰጠው ጥቅም የማይናቅ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያናችን በር ለሰላምና ለዕርቅ ክፍት መሆኑን ምልአተ ጉባኤው ገልጿል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተገለጹትና በሌሎችም መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቅቆአል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን ለሕዝባችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ምሕረቱንና ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን፤ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ አሜን፡፡

ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
ምሕረትና ይቅርታ፣ ትዕግሥትና ቸርነት የባሕርዩ የሆነ እግዚአብሔር አምላክ፣ ሰፊውን የወርኀ ጾም አገልግሎት በሰላም አስፈጽሞ ብርሃነ ትንሣኤውን በሰላም ስለአሳየን፣ እንደዚሁም ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና ዓመታዊ ከሆነ ከዚህ የርክበ ካህናት ጉባኤ በሰላም ስላደረሰን ክብርና ምስጋና ለእርሱ እናቀርባለን፡፡

‹‹ኀበ ሀለዉ ክልኤቱ ወሠለስቱ ጉቡኣን በስምየ አነ እሄሉ ማእከሌሆሙ ህየ — ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እገኛለሁ።›› (ማቴ. 18÷20)

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከዚህ በላይ በተጠቀሰው የጌታችን፣ የአምላካችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ቃል ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ጀማሪና ፈጻሚ ራሱ ጌታችን ቢሆንም ሥራው በአጠቃላይ በሰው ልጅ ድኅነት ላይ የሚከናወን ፍጹምና ምሉእ ተልእኮ በመሆኑ በአንድ ትውልድ ብቻ የሚያልቅ አይደለም፡፡

በመሆኑም ተልእኮው እስከ ዓለም መጨረሻ ለሚነሣው ትውልድ ሁሉ እንዲዳረስ፣ እርሱን ተከትለው የድኅነት አገልግሎት የሚሰጡ ሐዋርያት እንደሚያስፈልጉ ግልጽ ነበረ፡፡ ከዚህ አንጻር የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ የቅብብሎሽ ሥራ በመሆኑ እነሆ አባቶች ሲያልፉ በልጆች እየተተኩ ሥራው እኛ ዘንድ ደርሶአል፤ በዚህም ‹‹ወናሁ አነ እሄሉ ምስሌክሙ እስከ ኅልቀተ ዓለም፤ እነሆ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ›› (ማቴ. 28÷20) ብሎ የገባልን ቃል ኪዳን በተግባር እየተፈጸመልን አገልግሎታችን ከሀገር ውስጥ አልፎ መላውን ዓለም ባካለለ መልኩ እያካሄድን እንገኛለን፤ በዚህም እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በሁሉም የዓለም ክልል ፈላጊዋ እየበረከተ መምጣቱ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያናችን አማካኝነት ሊሠራ ያሰበው ሥራ እንዳለ የሚያመለክት ነው፤ ይህ ዕድል ለቤተ ክርስቲያናችን በጣም ትልቅ ስኬት የሚያስከትል በመሆኑ በሚገባ ልንሠራበትና ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

በመሆኑም በውጭ ሀገራት የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና አገልጋይ ካህናት እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ኦርቶዶክሳዊ ቀኖናን ከመጠበቅ ጋር በሙሉ ኀላፊነት፣ በአንድነትና በኅብረት ሆነው በውጭ ሀገር ያለው የቤተ ክርስቲያናችንን ተልእኮ በማስፋፋትና በማጠናከር ረገድ አብዝተው እንዲሠሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅብናል፡፡

ከሀገር ውጭ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት እየበረከቱ መምጣታቸው በአንድ በኩል የቤተ ክርስቲያናችን መጻኢ ዕድል ተስፋ ሰጭ እንደሆነ ሲያመለክት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ በአጠቃላይ በኦርቶዶክሱ ዓለም የሌለ ገለልተኛ ነን የሚል ስም በመጠቀም ከእናት ቤተ ክርስቲያን መኮብለል ሊታረም የሚገባ እንደሆነ ያመለክታል፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ካየነው “በሊቀ ጳጳስ ሥር ሆና የማትመራ ቤተ ክርስቲያን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ናት ለማለት ያስቸግራል፡፡” በመሆኑም ያለጥንቃቄም እንበለው ያለ ማወቅ በፈጠረው መነሾ የተጀመረው ስሕተት ጊዜ ሊሰጠው ስለማይገባ በዚህ ዙሪያ እንደካሁን ቀደሙ ጠንክረን በማስተማርና በማስረዳት ወደ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ጒያ ማሰባሰብ ይገባናል፤ ምእመናንም ይህንን ጊዜያዊ ስሕተት ለማስተካከል በሚደረገው ጥረት ተባባሪ እንዲሆኑ በዚህ አጋጣሚ ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ከሰበካ ጉባኤ መቋቋም በኋላ ያሳየችው እመርታ በተለይም በትላልቅ ከተሞች እየታየ ያለው፡-
• በኢኮኖሚ የመለወጥ ሁናቴ፣
• የትምህርት ቤቶች በብዛት መገንባት፣
• የጤና ተቅዋማትና የምግባረ ሠናይ ድርጅቶችን ማቋቋም እየተለመደ መምጣት
• ወጣቶች በየሰንበት ት/ቤቱ ስለሃይማኖታቸው በቂ ዕውቀት መቅሰማቸው፣
• የስብከተ ወንጌል ሥራ እየሰፋና እየተወደደ መምጣቱ እጅግ ተስፋ ሰጭ ሆኖ ይገኛል፡፡

እነዚህ ተስፋ ሰጭ ተግባራት ያላቸውን ክፍተት በመሙላትና በማስተካከል ዘመኑ በሚጠይቀው ጥበብና ብልሀት ከሠራንባቸው የዕጥፍ ዕጥፍ ዕድገትን ማምጣት እንደምንችል ሁኔታዎች ያሳያሉ፤ ስለሆነም ለበለጠ እድገት የተሻለ አሠራርና የጋራ ተነሣሽነትን አንግበን በመሥራት እድገታችንን በፍጥነት እውን ማድረግ ጊዜው የሚጠይቀን ኀላፊነት ነው፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው ጥንካሬና ድክመት ምን ጊዜም ቢሆን የማይለያዩ አንጻራዊ ነገሮች ናቸውና በቤተ ክርስቲያናችን አሠራር ውስጥም ጥንካሬ እንዳለ ሁሉ ድክመትም እንደማይጠፋ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በተለይም ካለፉት ዘመናት ጀምሮ እየተከሠተ ያለው የምእመናን ፍልሰት ወይም የበጎች መነጠቅና መኮብለል በመጀመሪያ ሊቀመጥ የሚገባ መሠረታዊ ችግር ሆኖ ይታያል፡፡

ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ከባድ ጥያቄ ሊያስነሣ የሚችል ጉዳይ መሆኑን ሁላችንም መገንዘብ አለብን፤ ስለሆነም ይህንን ችግር በወሳኝ መልኩ ለማስተካከል ጊዜ ሳይወስድ ይህ ቅዱስ ጉባኤ መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል፡፡

ሌላው በቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች እየተስተዋለ ያለው ችግር በስደትና በዝርወት የሚከሠት የሰብኣዊ መብት ጥሰትና የሃይማኖት ነፃነት እጦት፣ አልፎ ተርፎም ሕይወትን ማጣት ነው፤ ቤተ ክርቲያናችን በነዚህ ምክንያቶች የምታጣቸው ልጆች ቀላል ቊጥር ያላቸው አይደሉም፤ ልጆቻችን እንጀራ ፍለጋ ወደ ባዕድ ሀገር ሲሄዱ ስመ ክርስትና ከመለወጥ ጀምሮ ሃይማኖት እስከ መለወጥ የሚደርስ ተጽዕኖ ሁሉ እየገጠማቸው ብዙዎችን እያጣን ነው፤ ከዚህም ጋር በቅርቡ በሊቢያ እንደተከሠተው ያለ አረመኔያዊ ተግባር ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ እየተፈጸመባቸው ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ማባባሻ ሆኖ የሚገኘው ሀገራችን ከድህነት ወጥታ በኢኮኖሚ ሌሎች ሀገሮች ከደረሱበት ደረጃ ባለመድረሷ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም በሌላ ሀገር የሚገኘው ጥቅም በሀገር ውስጥ ቢገኝ ኖሮ ልጆቻችን ለስደት አይዳረጉም ነበር፤ ካልተሰደዱም ከላይ የተገለጸው ግፍና በደል በልጆቻችንና በቤተ ክርስቲያናችን አይደርስም ነበርና ነው፡፡

ስለሆነም አሁን በሀገራችንም ሆነ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በአሸባሪዎች እየተፈጸመብን ያለው ተግዳሮት በወሳኝ መልኩ ለመመከት በሀገራችን ያለውን የልማትና የእድገት መርሐ ግብር ከሕዝቡ ጎን ተሰልፎ በማፋጠን ድህነትን ታሪክ ማድረግ ለነገ የማይባል የቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ ሊሆን ይገባል፡፡ ሆኖም ለብዙ ዘመናት ሥር ሰዶ የቆየው ድህነት በአንድ ጀምበር ይጠፋል ተብሎ ስለማይገመት “ከመሞት መሰንበት” የሚለውን አባባል በመከተልና አሁን ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወጣት ልጆቻችን በሀገራቸው ሠርተው እንዲያድጉ ቤተ ክርስቲያናችን ያለማቋረጥ አዘውትራ ማስተማርና መምከር ይገባታል፤ እየመከረችም ትገኛለች፡፡

በመጨረሻም፤ ይህ ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በሚቀርቡ አጀንዳዎች መሠረት ለሰላም፤ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በመፈተሸና በመመርመር ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን በመወሰን ጉባኤውን እንዲያካሂድ በማሳሰብ የ2007 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ዛሬ መከፈቱን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ፣ ይቀድስ አሜን