ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ/ም፡ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

“ዘሰ አምነኒ በቅድመ ሰብእ አነኒ አአምኖ በቅድመ አቡየ ዘበሰማያት
በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ።”
(ማቴ. 10፥32)

ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ መሥዋዕትነት አብሯት የኖረ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በልዩ ልዩ ዘመናት ልጆቿ በግፍ ተገድለው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በናግራን፣ በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በዮዲት ጉዲት፣ በዐሥራ አምስኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ አሕመድ፣ በዐሥራ ዘጠነኛውና ሃያኛው ክፍለ ዘመን በውጭ ወራሪ ኀይሎች በርካታ የሰማዕትነት ታሪኮች አልፈዋል፡፡

ይሁን እንጂ በሁሉም ዘመን የተነሡባት አሳዳጆችና ገዳዮች ከነታሪካቸው ሲጠፉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአምላኳ ጥበቃና በልጆቿ ጽናት ሰማዕታቷን አክብራ ለሰው ልጅ መንፈሳዊ ሀብትን እያደለች አሁንም አለች ወደፊትም ትኖራለች፡፡ ዛሬ እነዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች በጠባቡ በር ተጒዘው ሰማዕትነት ተቀብለው ወደ መንግሥተ ሰማያት የገቡ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የክርስትና እምነት ጽኑ ምስክሮች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም ለእነዚህ ልጆቻችን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት የሚገባውን የሰማዕትነት ቀኖና ሥነ ሥርዐት በቅርቡ በማከናወን ለመላው ዓለም ያሳውቃል፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ቤተ ሰቦች የሆናችሁ ክርስቲያኖች ሁሉ በዚህ አረመኔያዊ ወንጀል ሳትደናገጡ አሸባሪነትን በአንድነት ሆናችሁ በማውገዝና በመከላከል የተጀመረውን ተቃውሞ ትርጒም ባለውና አፋጣኝ በሆነ መንገድ ልንፈጽመው እንደሚገባ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!
ለአሸባሪነት ሃይማኖት የለውም፣ በዕውቀትና በበሳል አእምሮ የሚከናወን ተግባርም አይደለም፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎችም የተረጋጋ ሥነ ልቡና ያላቸው ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ብሶት ያለባቸው ሰዎች እንደሚያደርጉት ያለ የነፃነት ትግልም አይደለም፡፡ ነገር ግን በፍጹም ራስ ወዳድነትና ጭካኔ ላይ የተመሠረተ አስነዋሪ ወንጀል ነው፡፡ የአይ ኤስ አሸባሪዎች የፈጸሙት ወንጀል የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ አስተሳሰብን የማይወክልና የሰውን ልጅ ተፈጥሮኣዊ ባሕርይ የጣሰ ተግባር ነው፡፡

ይህንን አስነዋሪ ግፍ ክርስቲያኖችና የሌላ እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ ሊያወግዘውና ሊጸየፈው የሚገባ ተግባር ነው፡፡እነዚህ ሰዎች የፈጸሙት ተግባር በራሳቸው ላይ ቢፈጸምና በጤናማ ሥነ ልቡና ቢያዩት ኖሮ በወጣቶቻችን ላይ በፈጸሙት ተግባር ልክ እንኳ ቢከፈላቸው እንደማይበቃ አድርገው በራሳቸው ላይ ይፈርዱ ነበር፡፡

ዛሬ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ለሚመስሉት ወገኖቹ ሕይወት፣ ደኅንነት፣ ምቾትና ሰላም ደፋ ቀና በሚልበት ዓለም ከሰው የተፈጠሩ የማይመስሉ አረመኔዎች ክቡር የሆነ የሰውን ልጅ ነፍስ ኢሰብኣዊ በሆነ መንገድ ሲቀጥፉ መታየት ምን የሚሉት እምነት ነው? ይህን አስነዋሪና ከሰው ተራ የሚያወጣቸውን ተግባርስ የወጣቶቹ ወላጆች ሳይቀሩ ዓለም ሁሉ በሚመለከተው ሚዲያ ማሳየትስ ምን የሚሉት ጭካኔ ነው? የሰውን ልጅ የቀድሞ ታሪክ አጥፍቶ አዲስ የግፍና የኢሰብኣዊነት ታሪክ ለመሥራት መጣጣርስ ምን የሚሉት አስተሳሰብ ነው?

ስለዚህ አይ ኤስን ጨምሮ በሰብኣዊ ፍጡር ሉዓላዊ ክብር ላይ የተቃጣ የአሸባሪነት ወንጀል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከምድራችን ሊወገድ የሚገባው እኩይ ግብር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ራሳቸውን አይ ኤስ ብለው የሚጠሩት አሸባሪዎች ከዕውቀትና ከሃይማኖት የወጡ፣ የልማትና የሰው ልጅ ሰላማዊ ሕይወት ሥጋቶች የሆኑ ቡድኖች በመሆናቸው ዓለም በአንድነት ተባብሮ ሊያስቆማቸው ይገባል፣ ምናልባት ቡድኑን በገንዘብና በልዩ ልዩ መንገድ ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦችና ተቋማት ካሉም የጥፋት ተባባሪ ከመሆን ሊታቀቡ ይገባል፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ለፈጸሙት ወንጀል በነፍሳቸውና በኅሊናቸው ከሚመጣባቸው ዘለዓለማዊ ፍርድ ይድኑ ዘንድ ንስሓ እንዲገቡ ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
ቀደም ሲል እንደገለጽነው በመንፈሳዊ ሕይወት ከምናገኘው ዋጋ ሁሉ የሰማዕትነት ዋጋ ተወዳዳሪ የለውም፣ በፍትሕ መንፈሳዊ ‹‹ወሰማዕታትሰ እሉ እሙንቱ ዘይቤ ክርስቶስ በእንቲኣሆሙ ዘሰ አምነኒ በቅድመ ሰብእ አነኒ አአምኖ በቅድመ አቡየ ዘበሰማያት፣ ወለእመ ተሳተፍክምዎሙ በጊዜ ኀዘናቲሆሙ ይከውን ለክሙ ስምዕ በእንተ ጻሕቀ ኅሊናክሙ –ሰማዕታት ማለት እኔን በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ ብሎ ክርስቶስ ስለእነርሱ የተናገረላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን በመከራቸው ጊዜ ብትመስሏው ስለቊርጥ ሓሳባችሁ ሰማዕትነት ይቈጠርላችኋል» የተባለላቸው ናቸው።

“ሰማዕታት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፣ መልካም እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ የሰጡ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡” (1ኛ ጴጥ. 4፥19)፤ ሰማዕታት ኀላፊ ጠፊ የሆነውን የዚህን ዓለም ጣዕም ትተው ስለእግዚአብሔር መንግሥት እና ፍቅር ታማኝ ሆነው በስለትና በእሳት ፊት በጽናት የቆሙ የእምነት አርበኞች ናቸው፤ ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው ታማኞች ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ደማቅ ምስክሮች ናቸው።

ሰማዕታት በቅዱሳት መጻሕፍት “ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ፤” (ማቴ 10፥28) የሚለውን ቃል ተቀብለው ምርጫቸው እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ ያሳዩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ሰማዕታት የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው በተባለው መሠረት የመንግሥተ ሰማያትን የክብር አክሊል በጥበብ ጀምረው በደማቸው ምስክርነት የተቀዳጁ ናቸው፡፡

ክብራቸውም አቡቀለምሲስ ዮሐንስ በራእዩ ምዕ 20 ቁጥር 4 “ዙፋኖችንም አየሁ፤ በእርሱ ላይ ለተቀመጡትም ዳኝነት ተሰጣቸው፣ ስለኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች … አየሁ” ብሎ እንደተናገረው በእግዚአብሔር መንግሥት የማያልፍ አክሊልና የፍርድ ዙፋን የተዘጋጀላቸው ናቸው፡፡

ስለዚህ የእነዚህ ወጣቶች ልጆቻችን ቤተሰቦች የሰማዕታት ቤተ ሰቦች በመሆናችሁ ልትጽናኑ ይገባል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በደሙ የመሠረታት ወልደ እግዚአብሔር የልጆቿን ነፍስ በክብር እንዲቀበል ትጸልያለች፡፡ ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን የልጆቻንን ነፍስ በክብር ያሳርፍልን፣ ለመላው ዓለም ሰላምንና መረጋጋትን ለቤተ ክርስቲያንና ለሰማዕታቱ ቤተ ሰቦች መጽናናትና ብርታትን ይስጥልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚብሔር እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ አይኤስ በተባለው አሸባሪ ቡድን በግፍ ስለተገደሉት ኢትዮጵያውያን በመስቀል አደባባይ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን አስተላልፈዋል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ/ም ራሱን አይ ኤስ በማለት የሚጠራው ሰብኣዊ ርኅራኄ የሌለው አሸባሪ ቡድን በወገኖቻችን ላይ ያደረሰውን አሠቃቂ የወንጀል ድርጊት ከሰማንበት ቀንና ሰዓት ጀምሮ በአምላካችን ዘንድ የወገኖቻችን ደም በከንቱ እንዳይቀር ልብን በሚሰብር ኀዘን በጸሎት በማሰብ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ በሰብኣዊ ፍጡር ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ድርጊት አሳሳቢና ፍጹም ጭካኔ የተመላው በመሆኑ ከኀዘናችንና ሰማዕታቱን በጸሎት ከማሰብ በተጨማሪ ወጣቶቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች መሆናቸውን ስለተረዳን ስለጌታችን ስምና ስለቀናች ሃይማኖት፣ ስለ እግዚአብሔርም ፍቅር ዐላውያን በቅጣት የሚያሠቃዩትን ክርስቲያናዊ ቸል አትበሉ ተብሎ በዲድስቅልያ በተደነገገው ቀኖና መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በተደጋጋሚ ልዩ ልዩ መግለጫዎች በማውጣት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልታደርግ የሚገባትን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ሥርዐት በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡

በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው የሁሉም ሃይማኖቶች ተልእኮ ሰውን ማዳን እንጂ ሰውን መግደል እንዳይደለ ቢታመንም ንጹሓን ዜጎችን በሃይማኖት ምክንያት በአሠቃቂ ግድያ የመግደል ወንጀል በዓለማችን መታየት ከጀመረ ሰነባብቶአል፡፡ ኢትዮያውያን ወገኖቻችንም በተለያየ ጊዜና በተለያየ አካባቢ የዚህ ዐይነቱ ግድያ ሰለባ መሆናቸው አልቀረም፡፡ ከዚህ አንጻር በዚህ ሰሙን በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች በሆኑት ልጆቻችን ላይ የተፈጸመው አሠቃቂ ግድያ ከምንም ጊዜ በላይ ቤተ ክርስቲያናችንን፣ ሀገራችንንና ሕዝባችንን ያሳዘነና ያሳሰበ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡

የተፈጸመው አሠቃቂ ድርጊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የዓለም ሃይማኖቶች ላይ የተቃጣ የወንጀል ተግባር መሆኑን በማመን መላው የሀገራችን ሕዝቦችና የሃይማኖት ተቅዋማት እንደዚሁም መላው የዓለም መንግሥታት ይህን ድርጊት በጽኑ መቃወምና ማውገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም የተፈጸመውን ድርጊት ፈጽሞ ታወግዛለች ከመንግሥትና ከሕዝብ ጋር ተሰልፋም የሚጠበቅባትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ታረጋግጣለች፡፡

ቀደም ሲል በመግለጫችን እንደተነገረው የአሸባሪዎች የጥፋት ዕልቂት ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ጾታንና አካባቢን ሳይለይ በአጠቃላይ በሰው ዘር ላይ የዘመተ የጥፋት ተልእኮ ስለሆነ ሁሉም የሃይማኖት መሪዎችና የፀረ ሽብር ተቅዋማት ለዓለማችን ሰላም መረጋገጥና ለሰው ልጆች በሕይወት የመኖር መብት መከበር ተባብረው እንዲሠሩ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ትጠይቃለች፤

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ዐቀፍ ማኅበረ ሰብና ከየሀገሩ መንግሥታት ጋር በመሆን የሚያካሂደውን የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል የዜጎቻችን ሕይወት በአሸባሪዎች እንዳይቀጠፍ ከእስከ አሁኑ በበለጠ እንዲንቀሳቀስ፤ ሕዝቡም ከአሁን በፊት በበጎ ታሪካችን እንደሚታወቀው በሃይማኖትና በሌላው ሁሉ ሳንለያይ ጠብቀን ያቆየነውን በአንድነት፣ በፍቅርና በመቻቻል የመኖር ዕሴት አሁንም አጥብቀን በመያዝ የጋራ ጠላት የሆነውን ግብረ ሽብር በመመከት ራሱንና ሀገሩን ከአሸባሪዎች ነቅቶ እንዲጠብቅ ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች፤

የሟዋች ቤተሰቦች የሆናችሁ ወገኖቻችን ሁሉ በዚህ ግፍ የተሞላበት ጭካኔ የተገደሉት ልጆቻችን በዚህ ዓለም የመኖር ተስፋቸው ባጭሩ ቢቀጭም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተገፉ መንግሥተ ሰማያትን ይናጠቋታል ማለትም ይወርሱአታል ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት እግዚብሔር ዕንባቸውን አብሶ በመንግሥቱ የሚቀበላቸው መሆኑን ዐውቃችሁ፣ ቤተ ክርስቲያንም ለሰማዕታቱ የአንድ ሳምንት የጸሎተ ፍትሐት ያወጀች መሆኑንና ሰማዕታቱን በሚገባቸው ክብር ለማክበር የሚገባትን ሥርዐት የምታከናውን መሆኑን ተረድታችሁ ልትጽናኑ ይገባችኋል፡፡

ከዚሁ ጋር ለማሳሰብ የምንወደው ጉዳይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ከመውጣት፣ አስተማማኝ የሕይወትና የንብረት ዋስትና ወደሌለበት ሀገር ከመሄድ ተቈጥቦ በሀገሩ ሠርቶ ኑሮውን እንዲመራ ቤተ ክርስቲያን የምትመክር መሆኑን እናስገነዝባለን፤

ክቡራንና ክቡራት፡ የተወደዳችሁ የሀገራችን ሕዝቦች
ሞትን ለመጀመሪያ ጊዜ የቀመሰው አቤል የተገደለው በወንድሙ በቃየል እጅ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ግን በዐመፅና በክፋት ተመልቶ ወንድሙን አቤልን የገደለ ቃየልን ከነጥፋቱ እንዲሠወር አልፈቀደም፡፡ ይልቁንም ገዳዩን “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? አቤል ምን አደረገህ?” የወንድምህ የአቤል የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮሃልና ብሎ ጠይቆታል፡፡ (ዘፍ 4፥10)

ስለዚህ ዛሬም በግፍና በጭካኔ የተመሉ አሸባሪዎች ከፈጣሪን ጥያቄና ፍርድ ፈጽመው እንደማያመልጡ እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ፈጣሪ የወንድሙን ደም ያፈሰሰውን ቃየልን የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ፣ በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ በማለት በቃየል ላይ ፈርዷልና ነው፡፡ ይህ አምላካዊ ፍርድ ዛሬም ወንድሞቻቸው የሚሆኑ የንጹሓን ወጣቶችን ሕይወት ያለርኀራኄ የቀጠፉ አሸባሪዎች ከዚህ ሰማያዊና ምድራዊ ፍርድ እንደማያመልጡ እምነታችን የጸና ነው፡፡ ስለዚህ እኛም በዛሬው ዕለት በወገኖቻችን የደረሰውን አሠቃቂ ወንጀል ልባችንን ስለነካው አቤል ወዴት አለ ብሎ የተገደለውን እንደፈለገው ፈጣሪ ወንድሞቻችን ወዴት አሉ ብለነን ሁላችንም ከመኖሪያ ቤታችን ከሥራችን ወጥተን ይህንን አሠቃቂ የወንጀል ድርጊት ለመቃወምና ለማውገዝ ወደ አደባባይ መውጣታችን ሰውን በሚወድ በፈጣሪ ፊት የሚያስመሰግን ነው፡፡

ክቡራንና ክቡራት፥ የተወደዳችሁ የሀገራችን ሕዝቦች
ይህ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን አሠቃቂ የወንጀል ድርጊት ከሰው ልጅ ተፈጥሮኣዊ ተግባር የወጣ ደረቅ ወንጀል ስለሆነ፣ ልንቃወምና ልንመክት የምንችለው በጥልቀትና በተረጋጋ መንፈስ በመሆን በመላው ዓለም ካሉ ከፀረ ሽብረ ግብረ ኀይላት ጋር በመተባበር ስለሆነ በትዕግሥትና በጥበብ የሰው ልጅ ሉዓላዊ ክብር እንዳይጣስ በነፃነት ሊኖርባት በተሰጠችው ምድር የሕይወት ዋስትና እንዲኖረው ለማስቻል ሁሉም ነቅቶና ተግቶ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚብሔር እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ በሰማዕትነት ስለተሠዉ ኢትዮጵያውያን የቅዱስነታቸው መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ግፉዓን ይትማሠጥዋ ለመንግሥተ ሰማያት በሃይማኖታቸው ምክንያት ግፍ የሚደርስባቸው መንግሥተ ሰማያትን ይናጠቋታል፡፡ (ማቴ. 11፣12)

በሰሜን አፍሪካ ሊቢያ ውስጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀልን በተመለከተ ከኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በድጋሚ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ፡፡ ራሱን አይ ኤስ እያለ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰሜን አፍራካ በሊቢያ ውስጥ በሜዲትራንያን ባሕር አካባቢ በንጹሓን የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ላይ ግፍ በተሞላበት አሠቃቂ ሁኔታ ግድያ እንደፈጸመ ታውቆአል፡፡ በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው የሁሉም ሃይማኖቶች ተልእኮ ሰውን ማዳን እንጂ ሰውን መግደል እንዳይደለ ይታመናል፡፡

ይሁን እንጂ በማንኛውም ሃይማኖት ተቀባይነት የሌለው ንጹሓን ዜጎችን በሃይማኖት ምክንያት በአሠቃቂ ግድያ የመግደል ወንጀል በዓለማችን መታየት ከጀመረ ሰነባብቶአል፡፡ ኢትዮያውያን ወገኖቻችንም በተለያየ ጊዜና በተለያየ አካባቢ የዚህ ዐይነቱ ግድያ ሰለባ መሆናቸውን አልቀረም፡፡ ከዚህ አንጻር በዚህ ሰሙን በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች በሆኑት ልጆቻችን ላይ የተፈጸመው አሠቃቂ ግድያ ከምንም ጊዜ በላይ ቤተ ክርስቲያናችንን ያሳዘነና ያሳሰበ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡

በመሆኑም የኢትዮያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተፈጸመው ድርጊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የዓለም ሃይማኖቶች ላይ የተቃጣ የወንጀል ተግባር መሆኑን በማመን መላው የሀገራችን ሕዝቦችና የሃይማኖት ተቅዋማት እንደዚሁም መላው የዓለም መንግሥታትና ማኅበረ ሰብ ይህንን ድርጊት በጽኑ ከመቃወምና ከማውገዝ በተጨማሪ ትርጒም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ፈጣንና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያፈላልግ እየጠየቀ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቶአል፡፡

1. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተከታይ ልጆችዋ ላይ በአይ ኤስ አሸባሪዎች የተፈጸመው አሠቃቂ ግድያ ደረቅ የወንጀል ተግባር በመሆኑ በጽኑ ታወግዛለች፤

2. በሁሉም እንደሚታወቀውና በተግባርም እንደታየው የአሸባሪዎች የጥፋት ዕልቂት ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ጾታንና አካባቢን ሳይለይ በአጠቃላይ በሰው ዘር ላይ የዘመተ የጥፋት ተልእኮ ስለሆነ የዓለም መንግሥታትና በአጠቃላይ የዓለም ማኅበረ ሰብ፣ እንደዚሁም ሁሉ የሃይማኖት መሪዎችና የፀረ ሽብር ተቅዋማት ለዓለማችን የሰላም መረጋገጥና ለሰው ልጆች በሕይወት የመኖር መብት መከበር ተባብረው እንዲሠሩ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ትጠይቃለች፤

3. የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ዐቀፍ ማኅበረ ሰብና ከየሀገሩ መንግሥታት ጋር በመሆን የሚያካሂደውን የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል የዜጎች ሕይወት በአሸባሪዎች እንዳይቀጠፍ ከእስከ አሁኑ በበለጠ እንዲንቀሳቀስ ቤተ ክርስቲያናችን ትጠይቃለች፤ በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ከመንግሥትና ከሕዝብ ጎን ተሰልፋ የሚጠበቅባትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆንዋን ታረጋግጣለች፣

4. የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሃይማኖትና በሌላው ሁሉ ሳንለያይ ከጥንት ጀምሮ ጠብቀን ያቆየነውን በኅብረት፣ በአንድነት፣ በፍቅርና በመቻቻል የመኖር ጸጋ አሁንም አጥብቀን በመያዝ የጋራ ጠላት የሆነውን ግብረ ሽብር የመመከት ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እናሳስባለን፡፡

5. የመዋች ቤተ ሰቦች የሆናችሁ ወገኖቻችን ሁሉ በዚህ ግፍ የተሞላበት ጭካኔ የተገደሉት ልጆቻችን በዚህ ዓለም የመኖር መብታቸው ባጭሩ ቢቀጭም ጌታችን የተገፉ መንግሥተ ሰማያትን ይናጠቋታል ማለትም ይወርሱአታል ባለው አምላካዊ ቃል እግዚብሔር ዕንባቸውን አብሶ በመንግሥቱ የሚቀበላቸው መሆኑን ዐውቃችሁ፣ እንደዚሁም ልጆቻችን «ወኩን መሃይምነ እስከ ለሞት ወእሁበከ አክሊለ ሕይወት – እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፤ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሀለሁ፤» (ራእ. 210) ያለውን የሐዋርያው ቃል ጠብቀው ሃይማኖታችንን አንክድም በማለት የሃይማኖት ሰማዕትነትን የተቀበሉ የሃይማኖት መስተጋድላን ስለሆኑ የጀግና እናት አታለቅስም እንደተባለው የልጆቻችሁ ሰማዕትነት በእግዚአብሔር መንግሥት ታላቅ ዋጋ ስላላቸው በዚህ ከኀዘናችሁ እንድትጽናኑ ቤተ ክርስቲያን ታሳስባለች፡፡

6. ቅዱስ ሲኖዶስ በሃይማኖታቸው ምክንያት ለተሠዉ ክርስቲያኖች ሊሰጥ የሚገባውን የሰማዕትነት ክብር በቀኖናው መሠረት መፈጸም ይቻል ዘንድ በአይ ኤስ አሸባሪ ቡድን በግፍ የተገደሉት ልጆቻችን ቤተ ሰብ የሆናችሁ ሁሉ የመዋቾቹን ስመ ክርስትና፣ ፎቶና ሙሉ አድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በተቻለ መጠን በፍጥነት እንድታቀርቡ ቤተ ክርስቲያን ታሳስባለች፡፡

7. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ከመውጣት፣ አስተማማኝ የሕይወትና የንብረት ዋስትና ወደሌለበት ሀገር ከመሄድ ተቈጥቦ በሀገሩ ውስጥ ሠርቶ ኑሮውን እንዲመራ ቤተ ክርስቲያን በአጽንዖት ትመክራለች፤

8. ቅዱስ ሲኖዶስ በየትኛውም አካባቢ የሚገኙትን ወገኖቻችንና የቤተ ክርስቲያን ልጆቻችን ከመሰል ጥቃት ለመታደግ እንዲቻል ከመንግሥት ጋር በቅርበት የሚሠራ ዐቢይ ኮሚቴ በአስቸኳይ የሚያቋቁም መሆኑን ይገልጻል፤

9. ከነገ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለ7 ቀናት ያህል በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በግፍ ለተገደሉት ወገኖች ጸሎተ ፍትሐት፣ ለሀገራችንና በአጠቃላይ ለዓለሙ ሁሉ ሰላም መጠበቅ፣ ለሰው ልጆች በሕይወት የመኖር መብት መከበር ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡

ወስብሐት ለእግዚብሔር እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሊቢያ ሀገር በንጹሓን ወገኖች ላይ ስለተፈጸመው አሠቃቂ ግድያ ስለማውገዝ በቅዱስነታቸው የተሰጠ የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ/ም ከእኩለ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም ያሉ የዜና ማሰራጫዎች በሰሜን አፍሪካ በሊቢያ የሜዲትራንያን ባሕር ዳርቻ አካባቢ አይኤስ በተባለ አሸባሪ ቡድን በንጹሓን ወገኖች አሠቃቂ ግድያ እንደተፈጸመባቸው ዘግበዋል፡፡

ዘገባው ከምኑም ከምኑ የሌሉበት ንጹሓን ክርስቲያን ወጣቶች በታጠቁና ፍጹም ሰብኣዊነት በሌላቸው አሸባሪዎች ሲገደሉ የሚያሳየው ምስልም በመላው ዓለም እየታየ ይገኛል፡፡ አሠቃቂው ግድያ ስለተፈጸመባቸው ንጹሓን ወጣቶች ዜግነትና ማንነት ግልጽና አስተማማኝ የሆነ መረጃ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በበርካታ የዓለም ዜና ማሰራጫዎች ሲነገር እንደሚሰማው የዚህ የግፍ ወንጀል ሰለባዎች ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች መሆናቸውን የዜና ማሰራጫዎቹ አክለው እየገለጹ ነው፡፡

የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፈጣሪ የተሰጠች የማንኛውም የሰው ልጅ ሕይወት ኀላፊነት በማይሰማቸውና በእነርሱ ላይ ሊደረግ በማይፈቅዱ ምንም ዐይነት ሰብኣዊ ርኅራኄ በሌላቸው እንድትቀጠፍ ስለማትፈቅድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን አሠቃቂ ድርጊት በጽኑ ትቃወማለች፣ አጥብቃም ታወግዘዋለች፡፡

ስለዚህ የዚህ ግፍ ሰለባ የሆኑት ወገኖቻችን ማንነት ተረድተን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት መሠረት አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑና መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ተገንዝበው ሁኔታውን በትዕግሥት እንዲጠብቁ፤ እንደዚሁም የተፈጸመው የጭካኔ ተግባር የማንኛውም ሃይማኖት ተቋምና እምነት የማይወክል የአሸባሪዎች ተግባር መሆኑን ተገንዝበው ኢትዮጵያውያን የሆኑ ሁሉ እንደቀድሞው በአንድነት በማውገዝ የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች ኪሳራ እንጂ ምንም ዐይነት ትርፍ የማያገኙ መሆናቸውን በተግባር እንዲያሳዩዋቸው እናሳስባለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፡፡ አሜን።

ሚያዝያ 4 ቀን የ2007 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤ በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤በሞትና በመቃብር ላይ ሥልጣን ያለው ኀያሉና አሸናፊው ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ ፡፡

‹‹ወበከመ በእንተ አዳም ኵልነ ንመውት ከማሁ በክርስቶስ ኵልነ ነሐዩ፤ ሁላችን በአዳም እንደምንሞት እንደዚሁም ሁላችን በክርስቶስ ሕያዋን እንሆናለን›› (1ቆሮ. 15÷22)፡፡

እዚህ ላይ በተገለጸው ቃለ እግዚአብሔር መሠረት የሰዎች መጻኢና የመጨረሻ ዕድል ከሁለት አዳማዊ ውርስ ጋር የተያያዘ ሆኖ ይገኛል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ በግልጽ እንደተጻፈው ሰው ሁሉ ከቀዳማዊ አዳም በሥጋ ተወልዶአል፤ የእርሱ የሆነውንም ሁሉ ወርሶአል፤ ይህም ማለት በሥጋው በኩል የግብረ ኀጢአት ዝንባሌን፣ ሞተ ሥጋን፣ ወሪደ መቃብርን፣ በመቃብር ውስጥ መበስበስንና መፍረስን ሲወርስ በነፍሱ በኩል ደግሞ ከእግዚአብሔር መለየትን፣ በኀጢአት ተሸንፎ የዲያብሎስ ሎሌ መሆንን፣ በኀጢአቱ ምክንያት ለኵነኔ ሲኦል ተጋላጭ መሆንን እና የመሳሰሉትን ሁሉ ወርሶአል ማለት ነው፡፡ ጠቅለል አድርገን ስናየው ቀዳማዊ አዳም በሥጋና በነፍስ ከባድ ውድቀትን ለልጆቹ አውርሶአል ማለት ነው፡፡ ከቀዳማዊ አዳም የውድቀት ዘመን ጀምሮ እስከ ስቅለተ ክርስቶስ በነበረው ረጅም ዘመን የሰው ዘር በአጠቃላይ ከቀዳማዊ አዳም ባገኘው ውርስ ምክንያት በሥጋው ርደተ መቃብርን፣ በነፍሱ ርደተ ሲኦልን ተፈርዶበት በድርብ መከራ ሲማቅቅ ኖሮአል፡፡ ያ ዘመን ከመከራው ብዛት የተነሣ ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኵነኔ ፣ ዓመተ መርገም ተብሎ ተሰይሞአል፡፡ ይሁን እንጂ ለምሕረቱና ለይቅርታው ወሰን የሌለው እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ውድቀት በትንሣኤ ለመቀልበስ ሲል የባሕርይ ልጁ የሆነ እግዚአብሔር ወልድን ወደዚህ ዓለም ላከ፡፡

እርሱም የኛን ሥጋ ተዋሕዶ ሰው ሆነ፤ በመካከላችን ተገኝቶም ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከመቃብር ወደ ትንሣኤ የሚወስደውን መንገድ በቅዱስ ወንጌሉ አስተማረን (ዮሐ. 5÷24)። የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ የአብ ልጅ ቢሆንም በሥጋው የሰው ልጅ ነውና ዳግማዊ አዳም ተብሎ ይጠራል (1ቆሮ. 15÷45-48)፡፡ በመሆኑም ዳግማዊ አዳም የተባለው ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በበኩሉ ቀዳማዊ አዳም ለልጆቹ ላወረሰው ውርስ ተቃራኒ የሆነውን ለሰው ዘር ሁሉ አውርሶአል፤ ይኸውም፡ በኀጢአት ዝንባሌ ፈንታ ጽድቀ መንፈስን፣ በሞት ፈንታ ዘለዓለማዊ ሕይወትን፣ በርደተ መቃብር ፈንታ ትንሣኤን፤ በርደተ ሲኦል ፈንታ ዕርገትን፣ በመለያየት ፈንታ ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት መኖርንና የመሳሰሉትን ለልጆቹ አውርሶአል፡፡ ይህ ሁሉ በክርስቶስ ቤዛነት ምክንያት ለሰው ልጅ በመሰጠቱ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ያለው ዘመን ዓመተ ሥጋዌ፣ መዋዕለ ንስሓ፣ ዓመተ ምሕረት ተብሎ ይጠራል፡፡ ይሁንና ሰው ሁሉ ከቀዳማዊ አዳም በሥጋ ዘር በመወለዱ የእርሱ የሆነውን ሁሉ እንደወረሰ፣ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ የዳግማዊ አዳም የሆነውን ሁሉ ለመውረስ ከዳግማዊ አዳም በመንፈስ መወለድ የግድ ያስፈልገዋል፡፡ ሰው በእምነት ተፀንሶ በጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ ሲወለድ የዳግማዊ አዳም ልጅ ይሆንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ይወርሳል፤ ከዚህ ዳግም ልደት በመንፈስ የተወለዱ ሰዎች ሁሉ የቀዳማዊ አዳም ውርስ አይነካቸውም (ሮሜ 8÷1)፡፡ የዳግማዊ አዳም ውርስ በዳግም ምጽአተ ክርስቶስ እውን ለማድረግ ቀጠሮ ተይዞለታል፤ ያን ጊዜ በመቃብር ያሉ ሙታን ሁሉ በቅፅበት ሲነሡና በሕይወት ያሉትም በአንድ ጊዜ በቅጽበት ሲለወጡ የዳግማዊ አዳም ውርስ በግልጽ ይታያል፡፡

በዚህ ጊዜ የሚሞተውና የሚበሰብሰው አካላችን የማይሞተውንና የማይበሰብሰውን ሲጎናጸፍ ሞትና መቃብር ይሸነፋሉ፤ ህልውናቸውም ያከትማል (1ቆሮ. 15÷52-57)፤ በዚያን ጊዜ ከቀዳማዊ አዳም በመጣ የኀጢአት ውርስ ምክንያት የሞቱ ሁሉ ከዳግማዊ አዳም በተገኘ የጽድቅ ውርስ ምክንያት ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ (1ቆሮ. 15÷49)፤ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶና ሞትን ድል አድርጎ የተነሣበትን በዓለ ፋሲካ ዛሬ በታላቅ ድምቀትና በደስታ ማክበራችን ‹‹ሞቴንና ትንሣኤዬን አስቡ›› (1ቆሮ. 11÷26) ያለውን ቃሉን ከመፈጸም ባሻገር የኛንም ትንሣኤ በእርሱ ትንሣኤ እያየን በሃይማኖትና በማይናወጽ ተስፋ ጸንተን እንድንኖር ለማድረግ ነው፡፡ በእርግጥም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤዛነቱ ካቀዳጀን ጸጋ አንዱና ዋነኛው እኛን ለትንሣኤና ለዘለዓለማዊ ሕይወት ማብቃቱ ነው፡፡ ከጌታችን ትንሣኤ የምንገነዘበው ዐቢይ ነገር እርሱ በመቃብር ውስጥ ሙስና መቃብር ማለትም መበስበስና መፍረስ ሳይነካው ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት ወደሰማያዊ ክብሩ እንዳረገ፣ እኛም ከእርሱ በወረስነው የጽድቅ ውርስ መሠረት እንደእርሱ ከመቃብር ተነሥተንና የዘለዓለምን ሕይወት ተቀዳጅተን ወደሰማያዊ መንግሥቱ የምናርግ መሆናችንን ነው፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ የትንሣኤያችን ማሳያ መስተዋትና የዘለዓለማዊው ሕይወታችን ማረጋገጫ ነውና (1ተሰ.4÷13-18)፡፡ ይሁን እንጂ የትንሣኤያችን ጒዞ የሚጀምረው ዛሬ በሕይወተ ሥጋ እያለን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ገበሬ በመኸር ወራት ጥሩ ምርትን ለማፈስ ልፋቱን በግንቦትና በሰኔ እንደሚጀምር፣ ያን ካላደረገ ደግሞ የሚያገኘው ምርት እንደማይኖር ሁሉ፣ እኛም የትንሣኤያችን ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ጒዞ ዛሬ በዚህ ዓለም ሳለን ካልጀመርነው በዳግም ምጽአት የምናገኘው ነገር አይኖርም (ማቴ 25÷ 1-13)፡፡

ሁላችንም እንደምንገነዘበው አምላካችን እግዚአብሔር ሠርቶ የሚያሠራ አምላክ እንጂ መክሊቱን ቀብሮ በስንፍና የሚኖረውን የሚወድ አምላክ አይደለም (ማቴ. 25÷24-30)፤ አምላካችን ከባሕርይ አምላክነት በስተቀር ሁሉን በሁሉ የሚያሳትፍ አምላክ እንደሆነ ምን ጊዜም አንርሳ፤ “ቅዱስ ተብሎ ቅዱሳን እንድንባል፣ ጻድቅ ተብሎ ጻድቃን እንድንባል፣ ክቡር ሆኖ ክቡራን እንድንሆን፣ ሕያው ሆኖ ሕያዋን እንድንሆን ፈቅዶልናል” (1ጴጥ. 1÷16)፡፡ በመሆኑም እርሱ የመልካም ሥራ ሁሉ ባለቤት እንደሆነ እኛም የመልካም ሥራ ባለቤቶች በመሆን ትንሣኤያችንን ከዚህ እንድንጀምር ተሳትፎውን ማለትም እርሱን መምሰልን ከእኛ ይፈልጋል (ማቴ. 5÷48)። ዛሬ ዓለማችን በፀጥታ ዕጦት እየታመሰች የምትገኘው ከሥነ ምግባር ጉድለት የተነሣ እንደሆነ ሁሉም ሊያውቀውና ሊገነዘበው ይገባል፡፡ በልዩ ልዩ የዓለማችን ሀገራት ውስጥ የሚገኙ የትምህርት ተቅዋማት የሥነ ምግባር ትምህርትን እያስተማሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ዓለማችን በመልካም ሥነ ምግባር ከመበልጸግ ይልቅ በዘቀጠና ለአእምሮ በሚዘገንን ነውረ ኀጢአት ክፉኛ እየተናጠች ትገኛለች፡፡ ይህ ሁሉ የሥነ ምግባር ውድቀት ሊመጣ የቻለው በየትምህርት ቤቱ የሚሰጠው የሥነ ምግባር ትምህርት በፈሪሀ እግዚአብሔር ያልተቃኘ ከመሆኑ የተነሣ እንደሆነ ሊሠመርበት ይገባል (መዝ. 110÷10፤ 1ቆሮ. 1÷20-21)፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን በእግዚአብሔር ፊት ልዩ ተቀባይነት ያላት ሀገር እንደሆነች ቅዱስ መጽሐፍ ሊመሰክርላት የቻለው በተቀደሰው ባህሏና በመልካም ሥነ ምግባሯ፣ በጸናው ሃይማኖቷና በእውነተኛው ትውፊቷ እንጂ በሌላ በምንም እንዳልሆነ በአጽንዖት መገንዘብ ያሻል፡፡ (መዝ. 71፡9፤ 67፡31) በሀገራችን ከምናስታውሰው ነባሩና ሃይማኖታዊ ባህላችን አንዱ ለብቻ መመገብ እንደነውር የሚወሰድ መሆኑን ነው፡፡ ይህ መልካም ሥነ ምግባራችንና ቅዱስ ባህላችን ዛሬም ተጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ የሁላችንም ኀላፊነት ነው፡፡ የትንሣኤያችንን ጒዞ ዛሬ እንጀምር ስንል የተራበውን ማጒረስ፣ የተጠማውን ማጠጣት፣ የታረዘውን ማልበስ፣ ያዘነውን ማጽናናት፣ የታመመውን መጠየቅና መርዳት፣ ስደተኛውን ማስተናገድ፣ የታሰረውን መጠየቅ፣ የሥራ ጊዜን በአልባሌ ቦታ አለማጥፋት፣ ለሰላም፣ ለሀገር ልማትና ለእድገት በአንድነት መሰለፍ፣ ሁሉንም ነገር በፍቅርና በስምምነት ብቻ መፍታት የመሳሰሉትን ሁሉ የሕይወታችን መርሆዎች አድርገን በተግባር እናውላቸው ማለታችን ነው፤ ይህንን የምናደርግ ከሆነ እውነትም የትንሣኤን ጒዞ በትክክል ጀምረናል ማለት ነው፡፡

በመጨረሻም፡ ሁላችሁም ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን በተቀደሰው እምነት ጸንታችሁ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔርን መሠረት ያደረገ ሥነ ምግባር አንግባችሁ፣ የሀገራችንን ሰላም በጽኑ እንድትጠብቁ፣ ልማቷንና እድገቷን እንድታፋጥኑ፣ አንድነታችሁንና እኩልነታችሁን አጥብቃችሁ እንድትይዙ፣ በዓለ ፋሲካውንም የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስና የተጠሙትን በማጠጣት፣ በሰላምና በፍቅር እንድታከብሩ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ አሜን፡፡

የካቲት 9 ቀን የ2007 ዓ.ም የዐቢይ ጾም መግቢያ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በመላ ዓለም የምትገኙ፣ በሃይማኖት ጸንታችሁ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን እንዲፈጽምላችሁ በናፍቆት የምትጠባበቁ፣ የእግዚአብሔር ልጆች ምእመናንና ምእመናት፤

ኀጢአትን በምግባረ ጽድቅ ለምንደመስስበት፣ ዲያብሎስን በእግዚአብሔር ቃል ድል ለምናደርግበት ለታላቁ ጾማችን ለጾመ ኢየሱስ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“እስመ አኮ ክመ በኅብስት ባሕቲቱ ዘየሐዩ ሰብእ አላ በኵሉ ቃል ዘይወጽእ እምአፉሁ ለእግዚአብሔር፤ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም።” (ማቴ. 4÷4)

ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በሠላሳ ዓመቱ በእደ ዮሐንስ፣ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፣ ሳይውል ሳያድር ወዲያውኑ ወደ ምድረ በዳ ሄዶ ጾምን መጾም ጀመረ፡፡ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሲጾም ከአራዊት በቀር ከእርሱ ጋር ማንም አልነበረም፤ መዋዕለ ጾሙን ከፈጸመ በኋላ ዲያብሎስ አዳምን ባሳተበት መብል እርሱንም ለማሳሳት ከጀለ፤ ሆኖም ጌታችን ‹‹ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም›› በማለት የማሳሳቻ ግንቡን ናደበት፤ ቀጥሎም ዲያብሎስ ‹‹መላእክቱን ስላንተ ያዝልሃል፣ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል›› ብሎ መጽሐፉን በትዕቢት መንፈስ በመጥቀስ ጌታችን ከመቅደሱ አናት ራሱን እንዲወረውር በስሑት ጥቅሱ ወተወተ፤ ይሁንና አሁንም ጌታችን ‹‹አምላክህን እግዚአብሔርን አትፈታተነው›› ተብሎ ተጽፎአል በማለት በድጋሚ የጥፋት መረቡን በጠሰበት፡፡ (መዝ. 90÷11፤ ዘዳ. 6÷16)

ዲያብሎስ ለሦስተኛ ጊዜ የዓለምን ክብርና ብልጽግና በማሳየት ጌታችንን ለእኔ ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ ብሎ በፍቅረ ንዋይ አማካኝነት በአምልኮ ባዕድ ሊያጠምደው ሞከረ፤ ያን ጊዜ ጌታችን ሂድ፣ አንተ ሰይጣን ‹‹ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ›› (ዘዳ. 6÷13) ተብሎ ተጽፎአል ብሎ ዲያብሎስን ተስፋ ቈርጦና ተሸንፎ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር አንዳች ነገር ሲሹ ከእህልና ከውኃ ተከልክለው፣ በጾም ተወስነው፣ ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን ሲለምኑ ተቀባይነትን ያገኙ እንደነበረ በቅዱስ መጽሐፍ በብዙ ቦታ ተጽፎአል፤ በዚህም ነቢዩ ዳንኤልና ዕዝራ፣ እንደዚሁም ሙሴና ኤልያስ፣ አስቴርና ወንድሟ መርዶክዮስ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው ፤ ከሀገር አንጻር ደግሞ የነነዌ ከተማን ብንመለከት ስለጾም ጠቃሚነት በቂ ትምህርት እናገኛለን። (አስ. 4፥1-4፣ ዮና. 3፥1-10)

አበው ነቢያት በጾምና በጸሎት ሆነው ያቀረቡትን ተማሕፅኖና ልመና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ የሚሹትን እንዳገኙ ቅዱሳት መጻሕፍት መስክረዋል፡፡ ጌታችን፣ አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የተጓደለውን ለማሟላት፣ የረቀቀውን ለማጕላትና የተዛባውን ለማስተካከል የመጣ እንደመሆኑ መጠን “ኦሪትንና ነቢያትን ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም” በማለት አስተምሮአል፤ (ማቴ 5÷17)፤ በመሆኑም ሙሴና ኤልያስ እንዳደረጉት እርሱም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በመጾም ሰይጣንን ድል አድርጎአል፤ ከድርጊቱ ሂደት እንደምንገነዘበው ሰይጣን ሰውን ለመጣል የሚጠቀምባቸው ዋና ዋና መሣሪያዎች መብል፣ ትዕቢትና ፍቅረ ንዋይ መሆናቸውን በዚህ እናስተውላለን ፤ ዲያብሎስ እናታችን ሔዋንን በዛፉ ፍሬ እንድትጎመጅ፤ እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ በሚለው ቅስቀሳ ሁሉን በእጇ እንድትጨብጥ በሚያስመስል የሐሰት ምክር እንድትወድቅ አድርጎአል (ዘፍ. 3÷4-8)። ዲያብሎስ ጌታችንን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተገልጾ በአዳማዊ ቁመና ሲመለከተው በቀዳማዊ አዳም የተጠቀመውን ስልት ተጠቅሞ ዳግማዊ አዳምን ለመጣል ብዙ ተጠብቦአል፤ ይሁን እንጂ ‹‹ተልባ መስሎሽ ሰናፍጭ ትቀምሽ›› እንደሚባለው በቀዳማዊ አዳም ያስለመደው ዘዴ ዳግማዊ አዳም በተባለ በጌታችን ላይ ሊሠራለት አልቻለም ፡፡

ጌታችን ዲያብሎስን ድል የነሣው በሦስት ነገሮች እንደሆነ እናያለን ይኸውም፡- አንደኛ፡ በጾም፣ በጸሎትና በእግዚአብሔር ቃል ነው (ሉቃ. 4፡1-13) ጌታችን በዲያብሎስ በኩል ይቀርቡ የነበሩ ፈተናዎች በሙሉ ያከሸፋቸው የእግዚአብሔር ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ነው፤ ዲያብሎስም በዚያው ልዋጋ ብሎ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስን ተጠቅሞአል ይሁንና ጥቅሶቹ በተቀመጠላቸው እውነተኛ ትርጒምና መንፈሳዊ ይዘት ሳይሆን ለራሱ ክፉ ዐላማ በሚያመች አኳኋን ለትዕቢትና ለፍቅረ ንዋይ ስለተጠቀመባቸው ሚዛን ሊደፉለት አልቻሉምና በመጨረሻ ሽንፈቱን ሊከናነብ ግድ ሆኖበታል ፡፡

ጾም ዲያብሎስንና አሳሳች መሣሪያዎቹን ሰባብረን የምንጥልበት መንፈሳዊና ኀያል መሣሪያችን ነው፤ በጾምና በጸሎት አጋንንት ይሸነፋሉ፣ በጾምና በጸሎት ኀጢአት ይደመሰሳል፣ በጾምና በጸሎት መልካም የሆነ የሥራ ዕቅድ ይሠምራል፤ በጾምና በጸሎት ነፍስ ከስለ ኀጢአት ትፈወሳለች፤ በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ይቻላል፤ በአጠቃላይ ጾምና ጸሎት የሥጋ ፍላጎትን በቊጥጥር ሥር በማዋል ነፍስ ኀያልና አሸናፊ ሆና የበላይነትን እንድትቀዳጅ ያደርጋሉ፡፡

እንግዲህ ጾምን እንድንጾም የምንገደድባቸው ዐበይት ምክንያቶች እነዚህ ሲሆኑ ብዙ ተከታይ ሠራዊት እንዳላቸውም መዘንጋት የለብንም በጾም ወቅት፡ እጆቻችን ለጸሎት፣ ድሆችን ለመርዳትና ለልማታዊ ሥራ የሚዘረጉ፤ አንደበታችን ሃይማኖትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን የሚሰብክ፣ ጆሮአችን ቃለ እግዚአብሔርን፣ መልካሙንና ሐቁን ነገር ብቻ የሚሰማ፣ ዐይናችንም ወደጽድቅ ሥራ ብቻ አነጣጥሮ የሚመለከት፤ እግሮቻችንም ወደ ቤተ እግዚአብሔርና ወደልማታዊ ተግባር የሚገሠግሡ መሆን አለባቸው፣ በዚህ መንፈስና ግንዛቤ ጾሙን ከጾምን ዲያብሎስን ማሸነፋችን፣ እግዚአብሔርንም መምሰላችን የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡

በመጨረሻም፡ የጾም ወራት ከምንም ጊዜ የበለጠ ሥራ የሚሠራበት እንጂ እጅና እግር አጣጥፈው የሚውሉበት ባለመሆኑ መንፈሳዊውንና ልማታዊውን ሥራችንን አቀናጅተን በመሥራት ሀገራችንን በአረንጓዴ ልማት ያጌጠች፣ ውብ፣ ለኑሮ ምቹና የተፈጥሮ ጸጋዋ የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ የሚደረገው የአፈርና የውኃ ጥበቃ ሥራ፣ በወርኀ ጾሙም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምድርን ውብና ለም አድርጎ በፈጠረ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡ ወርኀ ጾሙን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው እንዲያደርሰን የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ አሜን