ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኀላፊ፣የአርሲ ሀገረ ስብከት እና የምሥራቅ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፣የሲዳማ ክልል፣ የጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ፤
በዚህ ሐዋርያዊ ጉባኤ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ እንድንወያይ በየጊዜው የሚሰበስበን እግዚአብሔር አምላካችን ከዚህ ዕለትና ሰዓት ስላደረሰን ምስጋና ለእርሱ እናቀርባለን፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ወደዚህ ዓመታዊ ዐቢይ ጉባኤ እንኳን ደና መጣችሁ።
“ዕቀብ ማፀንተከ ዘተወፈይከ ከመ ትስብክ ቃሎ ቀዊመከ
ቆመህ ቃሉን ትሰብክ ዘንድ የተቀበልከውን አደራ ጠብቅ”
1ኛ ጢሞ. 4፥14)፡፡
በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው በዓለም ያለው ኀላፊነት ሁሉ መንፈሳዊውም ሆነ ሥጋዊው ያለ አደራ የሚሰጥ አይደለምይልቁኑም ለቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ አደራ ከሁሉም የላቀ እንደሆነ አንስተውም ምክንያቱም ከሰው ሳይሆን በቀጥታ ከእግዚአብሔር የተሰጠ አደራ ከመሆኑም በተጨማሪ በሰማይም ሆነ በምድር ገደብ የለሽ ኀላፊነት በመሆኑ ነው ሌላው ተልእኮ የምድሩን ብቻ ሆኖ ከዚያም በጂኦግራፊ ወይም በመልክዐ ምድር ወይም በድንበር ወይም በሥጋዊና ዓለማዊ ጉዳዮች የተገደበ ነው የቅዱስ ሲኖዶስ ተልእኮ ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው በምድር ላይ ምንም ዐይነት ድንበርና ወሰን ስለሌለው ገደብ የለሽ ነው ምክንያቱም ራሱ አደራ ሰጪው አምላክ “ሑሩ ወመሀሩ ውስተ ኲሉ አጽናፈ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኲሉ ፍጥረት — ወደ ዓለም ዳርቻዎች ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” በማለት አዞናልና ነው ተልእኮው ይህ ከሆነ ዘንድ ኀላፊነቱም በዚህ ልክ ተሰጥቶናል ማለት ነው የቅዱስ ሲኖዶስ አደራ በመንፈስ ላይ ብቻ ያተኰረ ሳይሆን ምእመናንን በነፍሳቸውም ሆነ በሥጋቸው በምልአት መጠበቅን የሚመለከት ነው ማለትም ተልእኮአችን የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑት ምእመናን በምድርም ሆነ በሰማይ፣በሥጋም ሆነ በነፍስ ለጉዳት እንዳይጋለጡ መጠበቅ ነው ማለት ነው፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
ንዋይ ሩይ የተባለው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ በላከለት መልእክት የተሰጠንን አደራ እንዴት መወጣት እንዳለብን በሚገባ አስረድቶናል ይውም ተግቶ ቃሉን በመስበክ አደራችንን መጠበቅ እንዳለብን ነው ምክንያቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ከእግዚአብሔር ቃል የበለጠ የሰውን ኅሊና የሚረታና የሚያሳምን ሌላ ኀይል የለውምና ነው ቤተ ክርስቲያን በሁለት ሺሕ ዓመታት ተልእኮዋ የሕዝቡንና የአሕዛቡን ሕሊና ማርካ፣ መንፈሱን አርክታ ከጎኗ በማሰለፍ ለእግዚአብሔር ማቅረብ የቻለችው በዚህ ቅዱስና ኀያል ቃል ነው በመሆኑም እኛም ሆን የዘመኑ ትውልድ ከቃሉ የበለጠ ሌላ ኀይል እንደሌለ በውል ተገንዝበን፣ ለዚህም አጽንዖት ሰጥተን በትጋት መሥራት ግዴታችን ይሆናልቅዱስ ቃሉን በትጋትና በጥራት፣ በተመሥጦና በብቃት እያስተማርን መሆናችንና አለመሆናችንን የሚመሰክረው በምድሩ ላይ ያለው ተጨባጭ ውጤት እንደሆነም ማስተዋል ይገባናል ምእመናን እየበዙ በአገልግሎታችንና በትምህርታችንም እየተደሰቱ ከሆነ፣ እውነትም ቃሉን በትክክል አሥርጸናል ሠርተናልም ማለት ነው ተቃራኒው ከሆነ ግን ገና ይቀረናል ማለት ነውቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ጉባኤ ማየት መገምገምና ተጨባጭ የማስተካከል ሥራ መሥራት ያለበት በዚህ ዙሪያ ነው፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
መንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ ሥራ በአግባቡ ለማከናወን የሰላም መኖር እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ሰላም ከሌለ ሃይማኖታዊ አገልግሎትና አስተምህሮም መቆሙና መቋረጡ አይቀሬ ነው ሰላም ሲጠፋ አማንያንም ሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳት ላይ ይወድቃሉይህም በመሆኑ ዛሬ በሀገራችን በተከሠተው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱት ጉዳቶች በቤተ ክርስቲያናችን ሊከሠቱ ችለዋል፡፡ ይህ አሳዛኝ ክሥተት በሃይማኖት በወገንና በሀገር ላይ እያደረሰ ያለው ከባድ ጉዳት እንዲያበቃ ወደ እግዚአብሔር መጸለይና መማፀን ይኖርብናልነገሮች ሁሉ ከእግዚአብሔር በታች እንጂ በላይ ስላይደሉ መፍትሔው እሱ እንዲያመጣልን ወደ እርሱ አጥብቀን መጸለይ ይኖርብናል ከዚህም ጋር በጦርነቱ የተጐዱ ወገኖች ተደራራቢ ችግር እንዳያጋጥማቸው ሕዝቡን በማስተባበር ልንረዳቸውና ልንደርስላቸው ይገባል፡፡
በመጨረሻም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በተደነገገው መሠረት በጥቅምት ወር በየዓመቱ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን የሚካሄደው ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎት የተከፈተ መሆኑን በእግዚአብሔር ስም እናበሥራለን።
እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።