• Amharic  
  • English 
  • Home
  • Papal Messages
  • Biography
  • Patriarchs
  • Contact
  • Menu Menu

የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም የዐቢይ ጾምን መግባት በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

March 7, 2016

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በተለያዩ ክፍላተ ዓለም የምትገኙ የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፤

ምሕረቱ የበዛ መዓቱ የራቀ ቸርና ሰው ወዳጅ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ስምንት ዓመተ ምሕረት የጌታችን፣ የአምላካችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መዋዕለ ጾም ዐቢይ በሰላም አደረሳችሁ።

‹‹ወአንሰ መጻእኩ ከመ ይርከቡ ሕይወተ ወፈድፋደ ይርከቡ
እኔ የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲያገኙ መጣሁ።»
(ዮሐ. 10፥10)

ይህ ቃል የሕይወት አስገኚና ሰጪ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ዘላቂና ዘለዓለማዊ ሕይወት ሊሰጥ ሰው ሆኖ ወደሰዎች እንደመጣ ሲያመለክት የተናገረው ቃለ አድኅኖ ነው፡፡ ለፍጡራን ሁሉ ትልቁና የመጀመሪያው ጸጋ ሕይወት ነው፤ ሰውም ሆነ ሌሎች ፍጥረታት በዚህ ዓለም ሲወጡና ሲወርዱ የሚገኙት ሕይወትን ለመንከባከብ፣ ለመጠበቅና ለማስቀጠል ነው፤ ምክንያቱም ሕይወት ካለ በሕይወት መሣሪያነት ሁሉም ይገኛል፤ ሕይወት ከሌለ ግን ሁሉም የለምና ነው ፡፡ በመሆኑም ሕይወት በፍጡራን ዘንድ ተወዳዳሪና መተኪያ የሌላት ሀብት ናትና ሙሉ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግላት ይገባል፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋችንንና ነፍሳችንን በመዋሐድ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው ሆኖ በዓለም ላይ የተገለጠው ሕይወታችንን ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብና ለማዳን ነው፡፡ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ተገልጦ ይመላለስ በነበረበት ጊዜ ሕይወትን አጥተው በጒስቊልና የነበሩ የተለያዩ ሕሙማን ሕይወተ ሥጋን እንዲያገኙ አድርጎአል፤ ሕይወተ ነፍስን አጥተው የነበሩትም በሕያው ትምህርቱ ተስፋ ሕይወትን እንዲላበሱ አድርጎአል፤ ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ሙታን ሕይወታቸውን ተጎናጽፈው ከመቃብር እንዲነሡ አድርጎአል፤ በእነዚህ ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወት ራስ መሆኑን ከመግለጽ ጋር ለሰው ልጆች ሁሉ ሕይወትን ለመስጠት እንደመጣ በትምህርትም በተግባርም አሳይቶአል፡፡ ከዚህ አንጻር ሕይወት በፈጣሪም ሆነ በፍጡራን ምን ያህል ታላቅ ዋጋ እንዳላት ማስተዋሉ አይከብድም፡፡

የሕይወት አስፈላጊነት ብዙ የሚያነጋግር አይሆንም ነገር ግን ሕይወትን በመጠበቅና በመንከባከብ ዙሪያ ብዙ ነገሮችን ማየቱ ተገቢ ነው፤ ከሁሉ በፊት ማየት ያለብን የሰው ሕይወት ተፈጥሮ ነው፤ የሰው ሕይወት አስኳል የሆነች ነፍስ በሥራዋ ምክንያት ተቀጪ ወይም ተሸላሚ ትሆናለች እንጂ ህልውናዋ አይጠፋም፤ ህላዌ ነፍስ በዚህ ዓለምም ሆነ በላይኛው ዓለም የማያልፍና ቀጣይ ነው፤ ነገር ግን በቅጣት የምትኖሮው ህላዌ ነፍስ እንዳለመኖር ስለሚቈጠር በመንፈሳዊ ርእይ እንደሞተች ወይም እንደጠፋች ይቈጠራል፤ በመሆኑም ይህ ዐይነቱ መጥፎ ቅጣት በሰው ሕይወተ- ነፍስ እንዳይደርስ ነው ጌታችን ሕይወትን እንዲያገኙ መጣሁ ያለው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕይወተ – ነፍስ ሲባል እርሱ የሕይወትን ዋጋ ከፍሎ የሰው ሕይወተ ነፍስን በመሥዋዕትነቱ ከቅጣት የምትድንበትን ዕድል አመቻቸቶአል ነገር ግን በዚህ ጠባብ በር ገብቶ ለመዳን አሁንም በሰዎች በኩል ተጋድሎው መቀጠል የግድ ይላል፡፡ የተጋድሎ ጒዞ መነሻው እምነት ነው፤ መጓጓዣውም ሥነ ምግባር ነው፤ መዳረሻው ደግሞ ከቅጣት ነፃ የሆነች የዘለዓለም ይሕወትን መቀዳጀት ነው፡፡ በአርባ ወይም በሰማንያ ቀን ሀብተ ክርስትና፣ ስመ ወልድን ያገኙ አማንያን ክርስቲያኖች የጒዞው መነሻ አጠናቅቀዋል አሁን የሚገኙት በመካከለኛው መንገድ ሆኖ ሃይማኖትን በሥነ ምግባር በሚገልጹበት ጎዳና ላይ ናቸው፤ ይህ ጎዳና ጠበብ ያለ ስለሆነ ጥበብና ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ጒዞ ፈቃደ ሥጋ በእጅጉ ይዋጋል፤ እርሱ ካሸነፈ ሕይወት ለቅጣት ትዳረጋለች፤ ፈቃደ ነፍስ ካሸነፈ ደግሞ ሕይወት ከቅጣት ነፃ ትሆናለች ፡፡ ነገሩ እንደዚህ ከሆነ ፈቃደ ሥጋ እንዲሸነፍ፣ ፈቃደ ነፍስ እንዲያሸንፍ በዋናነት መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግል ጾም ነው ፡፡ የጾም መሠረታዊ ዐላማ የሥጋ ፍላጎት የሆነውን ሁሉ በመግታት ብሎም በማስወገድ ለነፍስ ፍላጎት ማደር፣ መታዘዝና መገዛት ነው፤ ይህም ማለት ለእግዚአብሔር መታዘዝ፣ መገዛትና አምልኮ ማቅረብን ያጠቃልላል፤

በሌላ አባባል ፈቃደ ነፍስን መፈጸም ማለት ፈቃደ እግዚአብሔርን መፈጸም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሰው በእግዚአብሔር አርኣያና አምሳል የተፈጠረ ነው ሲባል የሰው ፈቃደ ነፍስ በባሕርዩ ወደ ፈቃደ እግዚአብሔር ያደላ ነው ማለት ነው ፡፡ በመሆኑም ሰው ምንጊዜም ቢሆን ፈቃደ ሥጋውን እየገታ፣ ፈቃደ ነፍሱን እያስተናገደ መኖር እንደሚገባው ቢታወቅም በተለይም እኛን ክሶ ለማዳን ሲል ጌታችን የጾመውን ጾም መነሻ በማድረግ ይህን ጾመ ኢየሱስ በተለየ ሁኔታ እንጾመዋለን፤ በዚህም ፈቃደ ሥጋን በቊጥጥር ሥር አውለን ፈቃደ ነፍስን ዋና መሪና አለቃ በማድረግ በሁሉም ነገር እግዚአብሔርን እናመልካለን እናመሰግናለን ለእርሱም ብቻ እንታዘዛለን እንገዛለን በዚህም መንፈሳዊ መሣሪያ ነፍሳችንን ከቅጣት እንጠብቃለን፡፡ ፈቃደ ሥጋንና ፈቃደ ነፍስን ለይቶ ለማወቅ ብዙ ውጣ ውረድ አያስፈልግም፤ ምክንያቱም ኅሊናችን ለይቶ ያውቃቸዋልና ነው፤ ይህም ማለት ኅሊናችን የማይስማማበት ሁሉ ፈቃደ ሥጋ ነውና እርሱን መተው አለብን ማለት ነው፤ ኅሊናችን የሚስማማበት ግን ፈቃደ ነፍስ ነውና እርሱን ማድረግ አለብን እውነቱን መለየት በሚያቅተን ጊዜ ደግሞ መጻሕፍትን በማንበብና መምህራንን በመጠየቅ መረዳት እንችላለን ፡፡ ዋናውና ታላቁ ኀጢአት ኅሊናችን ያልተስማማ ሆኖ እያለ እርሱን በፈቃደ ሥጋ ተገፍተንና ተሸንፈን የምንፈጽመው በደል ነው፤ ይህ ዐይነቱ ባሕርይም በውስጣችን አለና እርሱን በጽናትና በመንፈሳዊ ብርታት ተዋግተን ማሸነፍ አለብን፣ ማለትም ለዚህ መንበርከክና መሸነፍ የለብንም ማለት ነው፡፡ብዙ ክርስቲያኖች ጾምን በተመለከተ ቶሎ ትዝ የሚላቸው የእንስሳት ተዋፅኦ የሆነውን አለመመገብ፣ እስከ ተወሰነ ሰዓት ቆይቶ መመገብ ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ እንዳለ ሆኖ ሌሎች ዐበይት የጾም ሠራዊትም እንዳሉ ማስተዋሉ ተገቢ ነው፡፡

ጾም ማለት ፊደላዊ ትርጒሙ መተው ማለት ነውና ምግብ ብቻ ሳይሆን ብዙ የምንተወው አለ፣ የምናደርገውም አለ፡፡ መተው ካለባቸው ነገሮች መካከል ተድላ ሥጋን፣ መጣላትን፣ መጨካከንን፣ ፍትሕ ማጒደልን፣ ሰው መበደልን፣ ምቀኝነትን፣ መናናቅን፣ መነታረክን፣ መጨቃጨቅን፣ ራስ ወዳድነትን፣ አልጠግብ ባይነትን፣ ለብቻ መብላትን፣ ሥራ ፈትነትን መካሰስን፣ የሌላው መሻትን፣ የመሳሰሉ ሁሉ መጾም አለባቸው ማለትም መተው አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል በጾም ወቅት መደረግ ያለባቸው መራራትን፣ መጸለይን፣ አብዝቶ መዋደድን፣ ተደጋግፎና ተባብሮ መኖርን፣ የተራበውን ማብላት፣ የተጠማውን ማጠጣት፣ የታረዘውን ማልበስ፣ ያዘነውን ማጽናናት፣ የታመመውን መጠየቅ፣ የታሰረውን መጎብኘት፣ እንግዳን ተቀብሎ ማስተናገድ፣ በሁሉም ነገር የሰላም ጠበቃ ሆኖ መገኘት፣ ፍትሕን መስጠት ለድሀና ለችግረኛ ቅድሚያ በመስጠት ማገዝ፣ የተገፋውን መርዳት ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መጠየቅና ያንኑ ማድረግ ወዘተ የመሳሰሉ መተግበርና በሥራ ማዋል ይገባል፡፡ በመሆኑም ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ መዋዕለ ጾም መንፈሳዊ ተግባራትን ከመፈጸም ጎን ለጎን እያንዳንዱ ዜጋ ለሀገሩ ልማት ጥቅምና ብልጽግና በአርቆ አስተዋይነት እንዲቆም፣ የሀገራችንና የሕዝቦቻችንን አንድነትና ወንድማማችነት ከሚፈታተን መጥፎ ድርጊት ሁሉ በመቈጠብ ወደልማትና ወደ እድገት ብቻ እንዲሰማራ፣ ጾሙም ጸሎቱም በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ኖሮት ለሀገራችንና ለሕዝቦቻችን የሕይወት ስኬት ሊያመጣልን የሚችለው በፍቅርና በስምምነት አንድ ላይ ስንጾም ስለሆነ፣ መላው የሀገራችን ሕዝቦች በያላችሁበት ሰላማችሁን፣ ወንድማማችነታችሁንና አንድነታችሁን በመጠበቅ፣ በድርቁ ምክንያት የተጎዱ ወገኖቻችንን በመርዳት የጾሙን ወራት እንድታሳልፉ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/e/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc3 https://eotcp.org/e/wp-content/uploads/logo-en.svg tc32016-03-07 13:01:182025-01-28 13:02:26የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም የዐቢይ ጾምን መግባት በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
  • የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው የዐቢይ ጾምን መግባት በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል
  • ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም የጾመ ነነዌ የሰላምና የጸሎት አዋጅ
  • በቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክና የተከናወኑና በታሪክ የሚዘከሩ ዐበይት ተግባራት፤

Archives

  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ጥር 11 ቀን 2008 ዓ.ም የበዓለ ጥምቀት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: ጥር 11 ቀን 2008 ዓ.ም የበዓለ ጥምቀት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ጥር 11 ቀን 2008 ዓ.ም የበዓለ ጥምቀት ቃለ ምዕዳንና... Link to: የካቲት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሁለት ቀናት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ Link to: የካቲት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሁለት ቀናት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ የካቲት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top