በ35ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ ጉባኤ ጥቅምት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤ ክቡራን የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኀላፊዎች፣ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ከሚገኙ አህጉረ ስብከት የመጣችሁ ሥራ አስኪያጆችና ተወካዮች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ተወካዮች፣ በአጠቃላይ በዚህ ዓመታዊና ዓለም አቀፋዊ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የተገኛችሁ ተሳታፊዎች በሙሉ፤

የምሕረት አባትና የሰላም ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን ለዚህ ዓመታዊ የቤተ ክርስቲያናችን ዐቢይ ጉባኤ ስላደረሰን በቅድሚያ ክብርና ምስጋና ለእርሱ እናቀርባለን፡፡ እናንተንም እንኳን አደረሳችሁ እንኳንም በደኅና መጣችሁ እንላለን፡፡

“እንዘ አልብነ ኵሉ ብነ
አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የኛ ነው፤”
(2ቆሮ. 6፥10)፡፡

የሃይማኖት ጉዞ ሁሉ የመንፈስ ጒዞ ነውና በመንፈስ ጀምሮ በመንፈስ የሚጠናቀቅ እንጂ እንደገና ተመልሶ ወደ ግዙፉና ዓለማዊው ነገር የሚዘፈቅ አይደለም፤ እንደዚህ የሚሞከር ከሆነም ዐላማውን ስቶ ይወድቃል እንጂ ውጤታማ መሆን ፈጽሞ አይችልም፡፡

የሃይማኖት ሥራ በዋነኛነት የሚከናወነው በካህናት እንደሆነ ለሁሉም ግልጽ ነው፤ ካህናትም በትምህርተ ሃይማኖት ጸንተው፣ በኀይለ መንፈስ ቅዱስ ጎልብተው ዓለምንና በውስጡ ያለውን እየተዋጉ በማሸነፍ በድል አድራጊነት ወደፊት እንዲገሠግሡ እንጂ እንደገና በፍትወታት እኩያት ተሸንፈው ወደ ዓለማዊው አስተሳሰብና አኗኗር እንዲቀላቀሉ አልተፈቀደም፤ ካህናት የቆሙበት ስፍራና የተሸከሙት ኀላፊነት መለኮታዊ መንፈሳዊና ዘላለማዊ ነውና፤ ይሁን እንጂ ካህናት የመንፈስ ተቃራኒ የሆነውን አካለ ሥጋ የለበሱ በመሆናቸው ለሥጋዊ ኑሮአቸው የሚያስፈልግ ሁሉ በምእመናን እንዲሟላላቸው በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን በእግዚአብሔር ታዞአል፡፡

ካህናት እንደ ሐዲስ ኪዳኑ ሁሉ በብሉይ ኪዳንም በደብተራ ኦሪትና በዙርያው በነበረው የግብረ ክህነት አገልግሎት ሌት ተቀን ፅሙድ እንደ በሬ ቅኑት እንደ ገበሬ ሆነው በትጋት መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ያከናውኑ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ይሁንና ለኑሮአቸው የሚያስፈልገውን በተመለከተ የተፈቀደላቸው ቢኖር የዓለም የሆነውን ርስተ መሬት ሳይሆን ርስታቸው ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ያረጋግጣል ፤ ይህንንም አስመልክቶ ቅዱስ መጽሐፍ እንደዚህ ይላል “እግዚአብሔር አሮንን አለው፡- በምድራቸው ርስት በመካከላቸውም ድርሻ አይሆንልህም፤ በእስራኤል ልጆች መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ”፤ (ዘኍ. 18፥20)፡፡ ይህም ማለት የካህናት ሥጋዊ ኑሮ በርስተ መሬት ላይ ሳይሆን በሃይማኖተ ምእመናን ላይ በተመሠረተ ቃለ እግዚአብሔር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በሌላ አባባል፡- እግዚአብሔር ለካህናት የፈቀደው ርስት መሬታዊ ሳይሆን ዐሥራቱ፣ ቀዳምያቱና በኵራቱ ከምእመናን በነቂስ እየተከፈለ ለካህናት መተዳደሪያ ይሆን ዘንድ ለቤተ እግዚአብሔር እንዲሰጥ አድርጎአል ማለት ነው፤ (ዘፀ. 13፥2፣ ዘኍ. 18፥20-24፣ ዘሌ. 23፥9-14)፡፡ በዘመነ ሐዲስም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያንኑ የኦሪቱን ዐስበ ካህን በማጽናት “ይደልዎ ዓስቡ ለዘይትቀነይ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” ብሎአል (ማቴ.10፥10)፡፡

ከጥንት ጀምሮ ካህናተ እግዚአብሔር ይህ ነው ተብሎ የሚነገርና ግዙፍ የሆነ ምድራዊ ሀብት እንደሌላቸው ከላይ በተገለጸው ቃለ እግዚአብሔር ዋቢነት ማወቅ ይቻላል፤ ይሁን እንጂ ካህናት ኀላፊና ጠፊ የሆነው ምድራዊ ሀብት አይኑራቸው እንጂ የማያልፍና ተቈጥሮ የማያልቅ መለኮታዊ ሀብት በምድር ሳይቀር እንዳላቸው በቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮም ሆነ በተግባር ታይቶአል ፡፡ ከዚህም የተነሣ ነው “ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው” ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ የተነገረው፤ነገሩም እውነት ነው ፤አንድ ካህን ብዙ ገንዘብ ወይም ሌላ ሀብት ላይኖረው ይችላል ፤ ነገር ግን በብዙ የሚቀጠሩ ምእመናን አሉት፡፡

ከዚህ አኳያ ካህን ምንም የሌለው ቢመስልም አያያዙን ካወቀበት ብዙ ሀብት ያለው ነው ብንል ፍጹም እውነት እንጂ ሽንገላ ሊሆን አይችልም፤ ሁላችንም ከምር ማወቅና መቀበል ያለ ብን ዐቢይ ጉዳይ ሀብት ማለት የገንዘብና የእንስሳት ብዛት ወይም የመሬት ይዞታ ስፋት ሳይሆን የሰው ብዛት መሆኑን ነው ፤ምክንያቱም የሰው ሀብት ካለ ሌላው ሁሉ ከሰው ዘንድ ይገኛልና ነው፤ ለእኛም ለካህናት ትልቁና ቋሚው ሀብታችን የሰው ሀብት ነውና አንዳች የሀብት ወረት የሌለን ስንሆን እንደ እግዚአብሔር ቃል ብዙ የሰው ሀብት አለን፡፡

ከዚህ አንጻር የቤተ ክርስቲያን ቀዋሚ ሀብቶች ምእመናን በመሆናቸው በየጊዜው ብዙ ችግሮች ሲያጋጥሙአት በምእመናን ድጋፍ ሁሉንም ስትወጣው ቆይታለች ፤የሩቁን ትተን ከዛሬ አርባ ዓመታት በፊት የሆነውን እንኳ ብንመለከት የነበራት የመሬት ሀብት ሁሉ በጊዜው በነበረው መንግሥት ሲወረስ የማይነጥፉና ቀዋሚ ሀብቶች ሆነው የደረሱላት ምእመናን ብቻ ነበሩ፡፡ በወቅቱ የቤተ ክርስቲያን ቀዋሚና የማይነጥፍ ሀብት ምእመናን ብቻ መሆናቸውን የተረዱት ቀደምት ቅዱሳን አበው በተለይም ሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ምእመናንን በቃለ ዐዋዲ አደራጅተው ተገቢውን አስተዋፅኦ እንዲከፍሉ በማድረጋቸው በአሁኑ ጊዜ ከሞላ ጎደል ቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮዋ በአግባቡ እንድትወጣ፣ የካህናት ኑሮም እንዲሻሻል ለማድረግ ተችሎአል፡፡

ይሁን እንጂ ጌታችን “ማእረሩ ብዙኅ ውእቱ ወገባሩሰ ኅዳጥ ውእቱ፤ አዝመራው ወይም መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኛው ግን ጥቂት ነው” (ማቴ 9፡37) እንዳለው ዛሬም አዝመራው ብዙ ሆኖ ሳለ ሠራተኛው ጥቂት በመሆኑ ቀላል የማይባል ክፍተት ይስተዋላል፤ ይህም ማለት የሰው ኀይል እጥረት ባይኖር እንኳ ከአስተሳሰብና አሠራር ክፍተት የተነሣ አዝመራው በሚገባ ሳይያዝና ሳይጠበቅ እየቀረ ሌሎች ወፎች እየለቃቀሙት እንደሆነ በግልጽ ይታያል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ከኃምሳ ሚሊየን ያላነሱ ምእመናን ያሏት ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በመቶ ሚሊዮን ሳይሆን በቢሊየኖች የሚቈጠር የገንዘብ ሀብት አሰባስባ ትላልቅ መንፈሳዊ ተቅዋማትን ትገነባ ነበር፤ በዚህም ሀብትዋ ተጠቅማ አረጋውያንንና አሳዳጊ አልባ ሕፃናትን፣ በየማእከሉ ሰብስባ በሚገባ ትረዳ ነበር፣ የትምህርትና የጤና ተቅማዋት የመሳሰሉትን ማኅበራዊና መንፈሳዊ ተቅዋማትንም በብዛት ከፍታ ለሕዝቡ ችግር መቃለል ፈጥኖ ደራሽ መሆን ትችል ነበር፡፡

ዛሬም ጊዜው እየነጋ እንጂ እየመሸ አይደለምና አሁንም ከሁሉ በፊት ሀብታችን ያለበትን አካባቢ በውል ማወቅ ይኖርብናል ሀብታችን ያለው በምእመናን ልቡና ውስጥ ነው፡፡ እሱን በእግዚአብሔር ቃል አለስልሰን፤ በሥነ ምግባር ኰትኵተን ለመልካም ፍሬና ለጥሩ ምርት ማብቃት አለብን፤ ከአያያዝና ከትምህርት ጒድለት አንድ ምእመን ከበረታችን በተወሰደ ቍጥር ሀብታችን እየቀነሰ መሆኑን በውል እንገንዘብ ፤ምእመናን እስከ በዙና እስከተጠበቁ ድረስ ካህናት ሀብታሞች ነን ፤ ምእመናን እየቀነሱ በሄዱ ቊጥር ግን መደኽየታችን የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ካህናት ሁሌም መጨነቅ ያለብን ስለ ሀብት ድልብ ሳይሆን ስለምእመናን ድልብ ነው፤ ምእመናን ካሉ ሀብቱ አለና፤ ከኃምሳ ሚሊዮን በላይ ምእመናን ካሉንና በእነርሱ ላይ ተገቢ ጥበቃና አገልግሎት ካበረከትን የሚጎድልብን አንዳች ነገር አይኖርም፤ የሰበካ ጉባኤ ዐቢይ ተልእኮም ይኸው ነው፤ እስካሁን በሚታየው ተጨባጭ እውነታ የሰበካ ጉባኤ ዐላማ እኛ ካህናት ሀብታሞች መሆናችንን ያረጋገጠ ወንጌላዊ መሣሪያ እንደ ሆነ ከቶውኑ ልንዘነጋ አይገባም፡፡

ሰበካ ጉባኤ ትልቅና አስተማማኝ የሀብት ምንጭ እንደሆነ ተረጋግጦ ባለበት ሁኔታ እድገቱ አዝጋሚ ሆኖ መታየቱ ችግሩ የእኛ እንጂ የመሠረተ ዐላማው አለመሆኑን በሚገባ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ዛሬም፣ ነገም፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ ላቀ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የእድገት ደረጃ ለማሸጋገር ብቸኛውና ዋነኛው ቊልፍ ሰበካ ጉባኤ መሆኑን ሁላችንም ልናሠምርበት ይገባል፤ ስለሆነም እኛ ካህናት ሌት ተቀን በመሥራት፤ ምእመናንን እንደ እግዚአብሔር ቃል በመጠበቅና በመንከባከብ እንደዚሁም የሚጠበቅብንን መልካም ሥነ ምግባር ሁሉ ለምእመናን በማሳየት የቤተ ክርስቲያናችንን እድገትና ሉዓላዊ ክብር እስከ መጨረሻው ማስከበር ይጠበቅብናል፤

የካህናት መደበኛ ሥራ ምእመናንን ከማንኛውም ጒዳት መጠበቅ እንደሆነ የማይካድ ነው፤ የምእመናን ጥበቃም የተሟላ እንዲሆን በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ከዚያም አልፎ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተሟላ ሰላም መኖር የግድ ይላል፤ የመጀመሪያው ጥበቃም ማተኰር ያለበት በሰላም መረጋገጥ ላይ ነው፤ ምክንያቱም ሰላም ከሌለ ምእመናን የሚጠመቁበትና የሚቈርቡበት ቤተ ክርስቲያንም አደጋ ላይ ይወድቃል፤ በሰላም ወጥቶ ቤተ ክርስቲያን ደርሶና ከእግዚአብሔር ጋር ተገናኝቶ መመለስም ይቆማል፤ በዚህ ሁሉ ሃይማኖቱ ራሱ አደጋ ላይ ይወድቃል፤ ባለፉት ወራት በሀገራችን የተከሠተው የሰላም መደፍረስ አደጋ ያሳየን ነገር ቢኖር ይኸው የምእመናን ጒዳት ነው፡፡ በተለይም ዘርንና ሃይማኖትን ለይቶ የሀገርን አንድነት ለመናድ የሚደረገው ሙከራ ጎጅነቱ ወደር የማይገኝለት ነው፡፡ የኦሮሞ የኢሬቻ በዓል ላይ የደረሰው የሰው ዕልቂትም በኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ ቊስል አሳልፎ አልፏል፡፡ በዚህም ምክንያት ምእመናን ከተጎዱ ቤተ ክርስቲያን በቀጥታ ትጎዳለች፤ የሀገር ሰላም ከደፈረሰ ጒዞው ሁሉ ወደፊት መሆኑ ቀርቶ የኋልዮሽ ይሆናል፡፡ ታዲያ የኛ መምህርነትና አባትነት ለዚህ ጊዜ ያልሆነ ለመቼ ሊሆን ነው? እኛ አስተምረነው፣ መክረነው ታረቅ ብለነው የማይሰማን ሰው በዚህች ሀገር ይኖራል ብለን አናስብም፡፡

ስለሆነም ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ያሉ የቤተ ክርስቲያናችን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መምህራን ሊቃውንትና ካህናት በሙሉ የነበረን የሰላም ሀብት ልማታችንና እድገታችን በማይዋጥላቸው ባዕዳንና በሌሎች አካላት ሳይነጠቅ በነበረው ዐይነት ተጠብቆ እንዲቀጥል ለማድረግ ዙርያ መለስ ርብርብ ማድረግ ይገባናል፡፡ ሕዝባችን ሰላምን፣ እድገትን፣ አንድነትን፣ ልማትን፣ እኩልነትን፣ ፍትሓዊነትን፣ መልካም አስተዳደርን ብቻ እንደሚፈልግ እየነገረን ነው፡፡ ሕዝቡ ይህ ጥያቄ እንዲመለስለትና እውን እንዲሆንለት በመንግሥትና በሕዝቡ መካከል አገናኝ ድልድይ ሆነን መሥራት ይኖርብናል፤ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው አደራና ተልእኮም ይኸው ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በእሬቻ በዓልና በሌሎችም አካባቢዎች በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችን ሁሉ እግዚአብሔር በመንግሥቱ እንዲቀበልልን፣ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጥልን፣ወደፊትም ሕዝባችንን ከመሰል አደጋ እንዲጠብቅልን፣ ጸሎታችንን ወደ እግዚአብሔር እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም፡ ይህ ዐቢይ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን ዐበይት ጉዳዮችና በሀገራዊ ሰላም መጠበቅ ዙሪያ በሰፊው ተወያይቶ የበኩሉን ለማድረግ ቃል በመግባት ስብሰባውን እንዲያጠናቅቅ እያሳሰብን ሠላሳ አምስተኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ በዛሬው ዕለት መከፈቱን እናበሥራለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡