ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የዋጀ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለዓመታዊው የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

“ወይእዜኒ ረዐዩ ዘሀለዉ ኀቤክሙ መርዔቶ ለክርስቶስ፤ አሁንም በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ (1ኛ ጴጥ. 2፥6)፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ፣ ጠባቂ፣ መጋቢ፣ አስተናባሪና አስተዳዳሪ ነው፤ በሰማይና በምድር ያለው የሚታየውና የማይታየው ፍጥረት በአጠቃላይ በእግዚአብሔር ጥበቃና አስተዳደር ሥር ነው፤ ፍጡራን ከእሱ በተገኘ የአእምሮ ነፃነት በሚፈጽሙት ተግባር የራሳቸው ድርሻና ኀላፊነት እንዳላቸው ቢታወቅም ያለእርሱ ዕውቅና የሚደረግ እንደሌለ ግን ከቅዱስ መጽሐፍ እንማራለን፡፡ እንግዲህ እሱ የጠባቂዎች ጠባቂ ሆኖ ሳለ ከፍጡራን ወገን ደግሞ በልዩ ምርጫው እየሾመ መንጋውን ወይም ፍጥረቱን ያስጠብቃል፤ ይህ ከጥንት ጀምሮ የነበረ የእግዚአብሔር አሠራር እንደሆነ ቅዱስ ያሬድ ሲገልጽ “ኢኀደጋ ለምድር እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም እንበለ ካህናት ወዲያቆናት፤ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት አንሥቶ እስከ ዘላለሙድረስ ምድርን ያለካህናት እና ያለ ዲያቆናት አልተዋትም” በማለት ያረጋግጣል፡፡

ይህ የሚያመለክተን እግዚአብሔር ዓለምን ያለ ጠባቂ የተወበት ዘመን ካለመኖሩም ሌላ ጠባቂዎቹ ካህናትና ዲያቆናት መሆናቸውን ነው፤ ካህናት የሚለው ስያሜ የወል ስም ሆኖ ከቅዱስ ፓትርያርክ ጀምሮ ያለው ውሉደ ክህነት በሙሉ እንደሚያጠቃልል ይታወቃል፡፡ ከዚህ አኳያ ኰኵሐ ሃይማኖት ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን በተሰጠው የጥበቃ ኀላፊነት መሠረት እሱም በክህነት ለወለዳቸው ልጆቹ በፈንታው “መንጋውን ጠብቁ” እያለ ምእመናንን ሲያስጠብቅ እናያለን፡፡ ትልቁ የእግዚአብሔር ትእዛዝና የቤተ ክርስቲያን ተልእኮም ይህ የጥበቃ ተግባር ነው፡፡

እግዚአብሔር እኛ ካህናትን በኀላፊነት የሾመበት ዋና ዐላማ መንጋውን እንድንጠብቅለት ነው፤ ይህ መንጋ ተብሎ የተገለጸው ወገን የተለየ ሕዝብና ጐሳ ሳይሆን ትዝምደ ሰብእን ወይም የሰው ዘርን በሙሉ ነው፡፡ በራሱ እምቢተኝነት ከሚቀርበት በስተቀር የጌታችን ጥሪ ለትዝምደ ሰብእ በሙሉ እንደሆነ “ሑሩ ወስብኩ ወንጌለ ለኵሉ ፍጥረት ሂዱ፥ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” በማለት አሳውቆናል፡፡ እንዲህም ከሆነ ጠብቁ ተብለን የታዘዝነው ያመኑትን ወይም የተጠመቁትን ብቻ ሳይሆን ያላመኑትንም ያልተጠመቁትንም በአጠቃላይ እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡

ከዚህ አንጻር መንጋችንን ስንጠብቅ ያመኑትን በነፍሳቸውም በሥጋቸውም ምንም ዐይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው የተሟላ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ፣ ያላመኑትንም በፍቅር በማቅረብና ዘመድ ዘመድ በማለት፣ ውስጣዊና መንፈሳዊ ስሜታቸውን በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በማነቃቃትና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በማምጣት እንደሆነ ለሁላችን ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ይህን የጥበቃ ሥራ በአግባቡ ለማሳካት ትልቁ ትጥቃችን ቅዱስ ወንጌል እንደሆነ ምን ጊዜም መዘንጋት የለበትም፡፡ቃለ ቅዱስ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ለማዳረስ የተለያዩ ዘዴዎችንና አቀራረቦችን፣ ሥልጠናዎችንና አስተምህሮዎችን መጠቀምና በዚህም የባዘነውን በግ ወደ መንጋው የምንመለስበት ታሪካዊና ወቅታዊ ሥራ ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በየቀኑ የሚባክኑና በተኵላ የሚነጠቁ በጎች እጅግ እየተበራከቱ ነው፤ ዛሬ ሁሉም ነገር መልካም ነው ብለን የምንዘናጋበት ጊዜ ሳይሆን የጐደለውን ለመሙላት ቃል የምንገባበት፣ ያንኑም በተግባር ፈጽመን በጎቻችንን የምንሰበስብበት ጊዜ ነው፤ በዚህ አኳኋን በንቃትና በትጋት በኀላፊነትና በቊጭት ከሠራን ከባዘኑት በጎች መካከል ብዙዎቹን ወደ መንጋቸው መመለስ እንደምንችል፣ ያሉትም ባሉበት ጸንተው እንዲቀጥሉ ማድረግ እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

የጥበቃ ተግባራችን ከውጭ ኀይሎች ጣልቃ ገብነትና ከውስጥ ጥቅመኞች የተነሣ ተደጋጋሚ ዕንቅፋት በበዛበት በአሁኑ ጊዜ “በእንቅርት ላይ… ” እንደሚባለው በሀገራችን በተፈጠረው ያለመረጋጋት ክሥተት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ካህናትና ምእመናን ተገድለዋል፤ አሁንም ሥጋቱ እንዳለ፣ ከቀረበልን የአህጉረ ስብከት ሪፖርት ሰምተናል፤ በዐይናችንም አይተናል፤ ነባር የቤተ ክርስቲያናችን ይዞታዎች ሥልጣንን መከታ ባደረጉ ወገኖች እየተነጠቁ ነው፤ ምእመናን በሚደርስባቸው የማያባራ ተፅዕኖና አድልዎ ከቀያቸው እየተፈናቀሉና እየተሰደዱ ነው፡፡

ለመሆኑ እንዲህ ዐይነቱ ኢሰብኣዊ ድርጊት እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው? ይህ ድርጊት እንዲቆም እስከ ሞት ድረስ መሥዋዕት መሆን ከዚህ ጉባኤ አባላት ይጠበቃል፡፡ ይህ ጉባኤ የኀያሉ የእግዚአብሔር ጉባኤ ነው፤ ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ ብቻ ከሰባ ሚሊዮን ያላነሰ ሠራዊት ያለው ጉባኤ እንጂ ብቻውን አይደለም፤ ይህ ጉባኤ በሙሉ ዐቅሙ ሥራውን ከሠራና ድምፁን ካነሣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ሁሉ ሰሚው ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር እየደረሰብን ያለውን የማንታገሠው ግፍ መንግሥት እንዲያስተካክልልን ደጋግመን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ እኛም በጸሎት አምላካችንን ከመማፀን ጋር ሁሌም በተጎጂው ሕዝባችን መካከል እየተገኘን በልዩ ልዩ ግፍ ልባቸው የተሰበረውን የልጆቻችን ኀዘን መቅረፍ ይኖርብናል፡፡ ችግራቸውንም መጋራት ይጠበቅብናል፤ የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንደገና መገንባት አለብን፤ መንግሥትም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የሃይማኖት ክብር ነጻነትና እኩልነትን በሚሸረሽሩ የታችኛው መዋቅር ባለሥልጣናት ላይ የማያዳግም የእርምት ማስተካከያ እንዲያደርግ ጥብቅ ክትትል ማድረግ አለብን፡፡

የመንጋ ጥበቃችን ሥራ እየተሰነካከለ የሚገኘው ከውጭ ሆነው በገንዘብ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ እርስ በርሳችንን በመከፋፈል በሚተነኩሱን ኀይሎች ብቻ አይደለም፤ በውስጣችን ያለው ሕግ ያልጠበቀ አሠራርም የምእመናንን ልቡና እያቈሰለ የሚገኝ ሌላው የጥበቃችን ዕንቅፋት ነው፤በመሠረቱ ይህንን ችግር ከሥር መሠረቱ ነቅለን በማፅዳት ማስተካከል ካልቻልን ችግራችን በወሳኝ መልኩ ሊቀረፍ አይችልም፡፡

በመሆኑም ቀደም ሲል የተጠኑትን የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ችግር መፍትሔና የመሪ ዕቅድ ጥናቶች ይህ ዐቢይ ጉባኤ በወሰነው መሠረት ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በአስቸኳይ ይተገብር ዘንድ ጠበቅ ያለ መመሪያ ሊያስተላልፍ ይገባል፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ በብልሹ አስተዳደር አዙሪት የሚታመስ የቤተ ክርስቲያን አሠራር ሊኖር አይገባም፤ በዚህ ዓመት አሠራራችንን ሁሉ አስተካክለን ወደ መንጋ ጥበቃና ወደ ልማት ሥራችን በፍጥነት መሸጋገር አለብን፡፡

በመጨረሻም፡- የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን ዙሪያ መለስ ጥቃት ለመመከትና ለመከላከል ብሎም ለማስቆም አንድ የጥቃት መከላከል ግብረ ኀይል እንደዚሁም በየአካባቢው የሚሰነዘሩትን ጥቃቶች፣ ወከባዎች፣ ተጽዕኖዎችና አድላዊ አሠራሮችን እየተከታተለ ትክክለኛ ኢንፎርሜሽንን የሚያቀርብ የኮሙኒኬሽን ግብረ ኀይል በአሁኑ ጉባኤያችን አቋቁመን ቤተ ክርስቲያናችንንና መንጋችንን ከመከራ እንድንታደግ የሀገራችንን ሰላምና የሕዝባችንን አንድነትም በጽኑ እንድናስጠብቅ አባታዊ መልእክታችንን እያስተላለፍን፣ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መከፈቱን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!