ታኅሣሥ 29 ቀን 2013 ዓ.ም የልደት በዓልን መግባት አስመልክተው ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት ሁሉ፤
ከጥንት ጀምሮ የነገረንን ተስፋውን ለመፈጸም በዚህ ዓለም የተወለደው የተስፋ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ።

“ወናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ወትሰምዮ ስሞ አማኑኤል ዘበትርጓሜሁ እግዚአብሔር ምስሌነ፣ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች፤ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ማለት ነው” (ኢሳ. 7፥14፤ ማቴ. 1፥23)

የምሕረት አባት እግዚአብሔር አምላካችን በእውነተኛ ዳኝነቱ በኀጢአት ላይ መፍረዱ የማይቀር ቢሆንም ከዚህ ጎን ለጎን ይቅርባይነቱ አይለይም፡፡ በመሆኑም ሰው በበደሉ ምክንያት ቢፈረድበትም የሚድንበትንም ተስፋ ወዲያውኑ ተነግሮታል፤ ሰውም ያንን ተስፋ እንደሚፈጸምለት በማመን ለዘመናት ሲጠባበቅ ኖሮአል፣ ከዚህ አኳያ የተሰጠው ተስፋ በተለያየ ጊዜ፣ በተለያየ አገላለጽ፣ በተለያዩ ቅዱሳን ነቢያት በየጊዜው ተደጋግሞ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ከነዚህም መካከል ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ይገኝበታል፣ ነቢዩ ስለዚህ ተስፋ ሲናገር “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች፤ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው” በማለት ተስፋውን በትንቢቱ አጒልቶ ተናግሮአል፡፡ ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስም ይህ ተስፋ የተነገረው ለእመቤታችን እናትነት፣ ለጌታችን ልጅነት እንደዚሁም ድኅነትን ለሚሻ ለሰው ልጅ ሁሉ እንደሆነ በወንጌሉ አስረድቶናል፤ በተስፋው መሠረት የሚወለደው ልጅም አማኑኤል የሚል ስም እንዳለውና ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጦአል፣ ምሥጢሩ ከሕፃኑ መወለድ በፊት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መለያየት እንደነበረ፣ ሕፃኑ አማኑኤል ሲወለድ ግን እግዚአብሔርና ሰው መለያየታቸው ቀርቶ በከዊን አንድ እንደሆኑ ያስረዳናል፤ እንደዚህ ባለ ሁኔታ፣ በትንቢት ሲነገር የቆየው የእግዚአብሔርና የሰው ምሥጢረ ተዋሕዶ በዕለተ ፅንስ በማሕፀነ ማርያም እውን ሆነ፤ ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ “አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰውም አምላክ ሆነ” ከዘጠኝ ወር በኋላም በዛሬው ዕለት ታኅሣስ ፳፱ ቀን በቤተ ልሔም ከተማ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሰውን ሥጋ ለብሶ ወይም ተዋሕዶ መታየቱ ሰውን እንደታረቀው እና እንዳቀረበው፣ የአካሉ አካል እስከ ማድረግ ድረስ ደርሶም እንደወደደው በግልጽ ታወቀ፡፡ በመሆኑም ይህንን የአምላክና የሰው በከዊን መዋሐድ ያዩ ሰማያውያን ሠራዊት በከፍተኛ አድናቆትና በሐሤት “በሰማያት ለእግዚአብሔር ክብር ይገባል፤ በምድርም ለሰው ልጅ ሰላም ይገባል፤ ምክንያቱም ሰውን በእጅጉ ወዶታልና” በሚል ሰማያዊ አዲስ መዝሙር ቤተ ልሔምን አሸበረቋት፡፡ በቤተ ልሔም የነበሩ እረኞችም የምስጋናውና የክብሩ ተሳታፊዎች ነበሩ፣ ስለዚህ በዓለ ልደተ ክርስቶስ የከዊን ተዋሕዶው በአምላክና በሰው መካከል፣ የአንድነቱ ጥምረት በመላእክትና በሰዎች መካከል የተከናወነበት ታላቅ ቀን በመሆኑ በሰው ልጅ የድኅነት ጒዞ ዋናው መሠረት የተጣለበት ቀን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” የተባለው ትንቢትም በዚህ ቀን በትክክል መፈጸሙን እንገነዘባለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

ልደተ ክርስቶስ የተለያዩት የተገናኙበት፣ የተራራቁት የተቀራረቡበት፣ ሰማያውያንና ምድራውያን ስለ እግዚአብሔር ክብርና ስለ ሰላም በኅብረት የዘመሩበት ታላቅ በዓል ነው፣ ስለ እግዚአብሔር ክብርና ስለሰላም አስፈላጊነት በተመለከተ ከልደተ ክርስቶስ የበለጠ አስተማሪና ትምህርት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፣ ስለአንድነት ጠቀሜታም ከልደተ ክርስቶስ የተሻለ አስተምህሮ ይኖራል ተብሎ አይታመንም፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑም ሆነ ሌላው ማኅበረሰብ ለሰማያዊም ሆነ ለምድራዊ ኑሮአችን፣ ለነፍሳችንም ሆነ ለሥጋዊ ሕይወታችን የሚበጀን ምንድን ነው? ብሎ የሚጠይቅ ካለ መልሱ ከልደተ ክርስቶስ ይገኛል፤ መልሱ ከሁሉ በፊት ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ነው፣ መልሱ ከእግዚአብሔር ሠራዊት ጋር በአንድነት ስለ ሰላም፣ ስለዕርቅና ስለፍቅር መዘመር ነው፣ ይህ ከሆነ የተመሰቃቀለ ሕይወት አይኖርም፤ ሥጋት፣ ጭንቀት አይኖርም፤ ቢከሠትም እንኳ በፍቅርና በሰላም ይሸነፋል፤ ስለዚህ የሰው ልጅ በአጠቃላይ ለሰላምና ለአንድነት ዋጋ እንዲሰጥ ያስፈልጋል፤ ችግሮች በዓለማችን ተበራክተዋል፤ የኮሮና በሽታ በአንድ ወገን ክትባት ተገኘለት ሲባል፣ እንደገና ሌላ መሰል በሽታ በአዲስ ሁኔታ እንደተከሠተ እየሰማን ነው፤ የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታም ገና ፋይሉ አልተዘጋም፣ አለመግባባቶችም እየተካረሩ መጥተው ወደ ግጭት አምርተዋል፣ ረኃብ መፈናቀል እና ሌሎች ችግሮች ዓለማችንን እየናጧት ይገኛሉ፣ ይኼ ለምን ሆነ ቢባል የልደተ ክርስቶስ መልእክት ቸል ከመባሉ የተከሠተ ችግር ከመሆን አያልፍም፡፡ ስለሆነም የዚህ ሁሉ መፍትሔ የሚገኘው ከክርስቶስ ልደት ነውና ልደቱን ስናከብር ለእግዚአብሔር ክብር በመቆም፣ ለሰው ልጅም ሰላምን ለመስጠትና ለመቀበል በመዘጋጀት ሊሆን ይገባል፤ ከዚህም ጋር የታመሙትንና፣ የታሠሩትን በመጠየቅ፣ የተራቡትንና የተጠሙትን በማብላትና በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ ለእግዚአብሔር ያለንን ክብርና፣ ለወገን ያለንን ፍቅር በመግለጽ በዓሉን ልናከብር ይገባል፡፡

በመጨረሻም በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ በየአቅጣጫው እየተከሠተ ያለው አለመግባባት ልማታችንን፣ ነፃነታችንንና ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተን እንዳይሆን መላው ሕዝባችን በንቃት በጥበብና በማስተዋል እንዲከታተለው፣ ሁሉም ለሀገሩና ለሃይማኖቱ ለወገኑም ተገቢ ትኲረት በመስጠት በጸሎትና በሚችለው ሁሉ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል በዚህ አጋጣሚ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡ መልካም የልደት በዓል!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።