መጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም የደብረ ዘይት በዓል መልእክት የሚከተለው ነው
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ከሚመጣው ቊጣ ማምለጥ ትችሉ ዘንድ በጾም፣ በጸሎትና ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ቀን ከሌሊት እየተጋችሁ የምትገኙ በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም ዙሪያ ያላችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤ በጾምና በኀይለ መንፈስ ዲያብሎስን ድል አድርጎ የድል መንገድን ያስተማረን ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለበዓለ ደብረ ዘይት በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ!!
‹‹ናሁ ተዐውቀ ከመ ሀለወነ ኵልነ ንትሐተት በኀበ እግዚአብሔር፤
በእግዚአብሔር ዘንድ ሁላችንም እንደምንጠየቅ እነሆ ታወቀ።››
(ሮሜ. 14፥12)
የነገሥታት ንጉሥ፣ የመሪዎች መሪ፣ የዳኞች ሁሉ የበላይ ዳኛ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻውን የዳኝነት ፍርድ ለመስጠት ዳግመኛ እንደሚመጣ የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ደጋግመው ይነግሩናል፤ በተለይም ደብረ ዘይት ተብሎ በሚጠራው ቅዱስ ተራራ ላይ ሆኖ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዳግም ምጽአቱ በዝርዝርና በስፋት ማስተማሩን ክርስቲያኖች የሆን ሁላችን በውል የምናውቀው ነው፤ ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ እንዳስተማረን የዳግም ምጽአቱ መቃረብ ምልክቶች ፍቅር ቀዝቅዞ ጥላቻ እንደሚስፋፋ፣ በርካታ የጦርነት ወሬዎች እንደሚሰሙ፣ ረኃብና ቸነፈር እንደሚከሠት፣ ብዙ ሐሰተኞች ክርስቲያኖች ተነሥተው እውነተኞች የሆኑ ክርስቲያኖችን እንደሚያሳስቱ፣ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ የሚናገሩ ሐሰተኞች ነቢያት እንደሚነሡና በአጠቃላይ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ሆኖ የማያውቅ መከራ እንደሚከሠት አስተምሮናል፤ ይሁን እንጂ ትዕግሥትን አጽንቶ የያዘ ሁሉ እንደሚድን ግልጽ አድርጎአል፤ መከራው ካለፈ በኋላ መብረቅ በምሥራቅ ሲወጣ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፣ የእርሱ አመጣጥም በዓለም ውስጥ ያሉ በሙሉ እያዩት በግልጽ እንደሚመጣ እንጂ በእልፍኝ ወይም በድብብቆሽ እንደማይመጣ በመግለጽ፣ ክርስቶስ እዚያ አለ፤ ኢየሱስ እዚህ አለ ኑ ወደኛ የሚሉትን እንዳንሰማና እንዳንከተልም አስጠንቅቆናል፤ በመሆኑም ቃሉን በምልአት በመቀበል በእምነትና በዕውቀት ላይ በተመሠረተ መንፈሳዊ አስተውሎት በመከታተል በጊዜያችን እየሆነ ያለውን ሁሉ ልንገነዘበው ይገባል፤ ከጥንቃቄ ጒድለት የተነሣ፣ ከስሕተት ከግድየለሽነትና ከክሕደት እንዳንወድቅም መጠንቀቅ ይኖርብናል ፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤
ዳግም ምጽአቱን በማመን፣ ምን ጊዜም በሥነ ምግባርና በሃይማኖት ጸንቶ መኖር የሃይማኖታችን ቀዋሚ አስተምህሮ ነው፤ ጌታችን ዳግመኛ ይመጣል ሲባል ለምን ጉዳይ እንደሚመጣ በሚገባ ማወቅና ቅድመ ዝግጅት ማድረግም ከነፍስ ወከፍ ክርስቲያን ይጠበቃል፤ ጌታችን ዳግመኛ ወደዚህ ዓለም የሚመጣበት ዋናው ምክንያት እውነተኛውንና የመጨረሻውን ፍርድ ለሰው ልጆች ለመስጠት ነው፤ የዳኝነቱ መሠረትም በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ሳለን የሠራነው ሥራ ነው፤ ዳኛው ፊትን አይቶ የማያፍር፣ የማይፈራ፣ የማያዳላና ሚዛንን የማያዛባ ነውና በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ሳለን የሠራናትን ያችንኑ እንደ ሥራችን ያስረክበናል፤ ይህ ዳኝነት ይግባኝ የሌለበት፣ ሙግትና ክርክር የማይካሄድበት፣ ምስክርና ማስረጃ አለኝ የማይባልበት ፍርድ ቤት ነው፤ ወደዚህ ፍርድ ቤት የማይቀርብና የማይጠየቅ ሰውም የለም አይኖርምም፤ ተሸፋፍኖ፣ ተደባብቆና ተሽለኩልኮ ማምለጥም አይቻልም፤ የሰው ልጆች የሆን ሁላችን ያለን ብቸኛ አዋጪ ስልት በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ስንኖር በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ጸንተን መኖር ብቻ ነው፤ የፈጸምነው ስሕተት ሲኖርም በንስሓ እንዲሠረዝ በማድረግ መንፈሳዊ ሕይወትን ጠብቀን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነትን አጽንተን መኖር ነው፡፡
ክርስቶስ አምላካችን ወደዚህ ዓለም ዳግመኛ ሲመጣ በሠራነው ሥራ መጠን ፍዳ ወይም ዋጋ እንደሚጠብቀን ተገንዝበን ከፍዳ የምናመልጥበትንና ዋጋ የምናገኝበትን ሥራ መሥራት ከጥበብ ሁሉ የበለጠ ጥበብ ነው ፡፡ ከዚህ አኳያ በልዩ ትኵረት ልንከታተላቸው፣ እንደዐይን ብሌንም ልንጠብቃቸው የሚገቡ ነገሮች ሁለት ዐበይት ነገሮች እንዳሉ ጌታችን አስተምሮናል፡፡ እነሱም (1ኛ) አንደኛው እግዚአብሔርን በሁለመናችን መውደድ ሲሆን፤ (2ኛ) ሁለተኛው ደግሞ ባልንጀራችንን እንደነፍሳችን መውደድ ናቸው፤ እነዚህ የፍጹም ፍቅር ሕግጋትን በአግባቡ ከጠበቅን ኀጢአት መግቢያ አይኖረውም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔርን ከልብ የምንወድ ከሆነ እንደፈቃዱ መኖር የሚከብድ አይሆንም፤ ሰውንም እንደነፍሳችን የምንወድ ከሆነ ለሰው መልካም ነገርን መሥራት የሚከብድ አይሆንም፤ በተወሰነ ደረጃ ብንሳሳት እንኳ ሥር የሰደደ የኀጢአት ልምድና ሱስ አይኖረንምና በፍጥነት ንስሓ ገብተን በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቢጽ ጸንተን መቀጠል እንችላለን፡፡
ዛሬ በዓለም እየተከሠቱ ያሉ ችግሮች ሁሉ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ እጥረቶች ያስገኙአቸው መዘዞች እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለንም፤ የዘመናችን ትውልድ እግዚአብሔርን ከልብ የሚያምን፣ የሚፈራና ለእሱ ለመታዘዝ ዝግጁ ቢሆን ኖሮ፣ ሰውንም እንደራሱ አድርጎ የሚወድ ቢሆን ኖሮ መሳሳቡ፣ መጨካከኑ፣ ራስ ወዳድነቱ፣ ከዚያም አልፎ ለመጠፋፋት መነሣሣቱ መቼ ዕድል ያገኝ ነበር፤ ዓለማችን፣ ሀገራችንም ጭምር እየተለማመደችው ያለው ይህ የጥላቻና የራስ ወዳድነት አመለካከት፣ በምድር ላይ በእጅጉ የሚጐዳንና በመጨረሻው የፍርድ ቀንም በዕዳና በፍዳ የሚያስጠይቀን ነው፡፡ ስለዚህ ለጠብና ለመለያየት መንሥኤ ናቸው የሚባሉ ምክንያቶች በሙሉ በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቢጽ ማማ ላይ ሆነን ብናያቸው ኖሮ ኢምንት ነበሩ፡፡ ሁሉም ችግሮች በውይይት ወይም በሰጥቶ መቀበል መርሕ አለያም በሕግና በሕግ ብቻ መፍታት እየተቻለ ሰው ሰውን ለመጕዳት መከጀል ትልቅ ስሕተት ነው፤ የሦስት ሺሕ ዘመናትና ከዚያም በላይ ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር ተሳስረው የኖሩ ሀገርና ሕዝቦች አሉን ብለን በኵራት የምንተርክ ሕዝቦች የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ የሆነውን ፍቅረ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን ማእከል አድርገን የውስጥ ችግራችንን በሰላማዊና በወንድማዊ መንፈስ መፍታት እንዴት ያቅተናል? ድንጋይ መወራወርስ ማንን ይጠቅማል? እኛ ኢትዮጵያውያን አሁን እየተከተልነው ያለው አካሄድ ለእኛ መልካም ነገርን የማይመኙልንና እድገታችንን የማይሹ እንዲሁም በአንድነታችን ከባድ ሥጋት የሚያድርባቸውን ብቻ ይጠቅም እንደሆነ እንጂ እኛን ፈጽሞ እንደማይጠቅመን በተጨባጭ እያየነው ነው፡፡
በመሆኑም አሁንም ወደልባችን እንመለስና ችግራችንን በራሳችን ፈትተን ወደፍጹም ፍቅራችንና ወደሃይማኖታችን በማምራት እድገታችንን ልናፋጥን ይገባል፤ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ምሁራንም በገለልተኝነትና በቅንነት ሆነን የመምከር፤ የማስታረቅና የማስማማት ሥራን አጠንክረን መሥራት ይገባናል፤ መንግሥትም ከፍተኛ ኀላፊነት ያለበት ነውና ነገሮችን ሁሉ በትዕግሥትና በአርቆ አስተዋይነት በመመልከት፣ ሁሉንም ለማሰባሰብና ለማቀፍ እንደዚሁም ቅሬታ ያላቸውን ወገኖች ይበልጥ በማቅረብና ሥጋታቸውን በመቅረፍ፣ አስተማማኝ ሰላምና ጠንካራ አንድነት በሀገሪቱ ሕዝቦች እንዲረጋገጥ ተግቶ እንዲሠራ እንመክራለን፤ ሕዝቡና የፖለቲካ ተፎካካሪ ወገኖቻችንም ልዩነቶችና አለመግባባቶች እየቀነሱ አንድነትና ፍቅርን፣ መተማመንና ከሥጋት ነፃ መሆንን እያጐለበቱ በከፍተኛ ኀላፊነት እንዲሠሩ በዚህ አጋጣሚ አባታዊ ምክራችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም፤ ሁሉም ነገር ከእግዚአብሔር ቍጥጥር ሥር በታች መሆኑን አምናችሁ በሀገራችን ፍጹም ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን ይህ አሁን በድንገት ተነሥቶ እንደ ሰደድ እሳት በመላው ዓለም ላይ የተለቀቀውን ‹‹ኮሮና ቫይረስ›› የተባለውን ወረርሽኝ በሽታ በመለኮታዊ ኀይሉ እንዲያስወግድልን በምሕላና በጸሎት እግዚአብሔርን በመማፀን ተጠምዳችሁ የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፣ አሁንም ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ሊሰጠን ወደሚችል ወደ እግዚአብሔር በኃዘንና በለቅሶ፣ በዕርቅና በይቅርታ በፍጹም ፍቅርም ልባችሁን በመስበር ወርኀ ጾሙ እስኪጠናቀቅ ድረስ ምሕላችሁን እንድትቀጥሉ አደራ ጭምር አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡ እግዚአብሔር ወርኀ ጾሙን አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን!!