መስከረም 16 ቀን የ2009 ዓ.ም. በበዓለ መስቀል ላይ በአደባባይ የተሰጠ መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ከአራቱ የከተማችን መዓዝን የመጣችሁ ሕዝበ ክርስቲያን፤ እንደዚሁም በሀገር ውስጥና በውጭ ሆናችሁ የበዓለ መስቀሉን ሥነ በዓል በመከታተል የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በመስቀሉ ተሰቅሎ ባፈሰሰው ደሙ ሰማያውያንና ምድራውያንን አስታርቆ ፍጹም ሰላምን ያጎናጸፈን ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ መስቀል በሰላም አደረሳችሁ።

‹‹ወለጽልእ ቀተሎ በመስቀሉ
ጥልንም በመስቀሉ ገደለው።››
(ኤፌ. 2፥16)

ቅዱስ መጽሐፍ በግልጽ እንደሚነግረን ዓለም እንደተፈጠረ ብዙም ሳይቆይ የጥል ግንብ እንደተገነባ ነው፤ የጠቡ መነሻ የሆነው መሠረታዊ ችግር ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ፣ ታማኝ ሆኖ አለመገኘት፣ ሕግን መጣስ፣ ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ የዲያብሎስን ምክር መቀበል ነው፤ (ዘፍ.2፡16-17፤ ዘፍ.3፡1-8)፡፡ ይህ አድራጎት የተፈጸመው በአባታችን አዳምና በእናታችን ሔዋን ሲሆን ድርጊቱ በፈጣሪና በፍጡራን፣ እንደዚሁም በፍጡራንና በፍጡራን መካከል ጽኑ የሆነ ጥል ፈጠረ፤ ከባድ የሆነ መርገምትና መለያየትም አስከተለ (ዘፍ. 3፥10-24)፡፡

ጥል ካለ ዘንድ መለያየቱም እየሰፋና እየከፋ መሄዱ የማይቀር ነውና ከአዳምና ከሔዋን የተገኘ የሰው ዘር በሙሉ እርስ በእርስ መጣላቱንና መለያየቱን በስፋት ቀጠለበት፣ በዚህም ሂደት የሰው ልጅ ሕይወት ጣዕም የለሽና መራራ ሆነች፣ ሁሉም በአምልኮ ባዕድና በድንቊርና ተዋጠ፤ ቀለም፣ እምነት፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ መልክዐ ምድር ከባቢያዊ ባህል፣ ሀብት፣ ሥልጣን፣ ዕውቀት የመሳሰሉ ሁሉ ሰውን እርስ በርሱ ለያይተው ለከፋ ጕዳት ዳረጉት፤ እነዚህ ሁሉ ኀጢአት ወልዳ ያሳደገቻቸው የአለመታዘዝ ውጤቶች እንጂ ከጥንተ ፍጥረት የተገኙ አይደሉም፡፡ የሰው ዘር በአጠቃላይ ከአዳም ውድቀት አንሥቶ እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ድረስ በዚህ የጨለማ ሕይወት ተውጦ ስለነበረ ቅዱስ መጽሐፍ “በጨለማና በሞት ጥላ የሚኖር ሕዝብ” ብሎ ይገልጸዋል፤ (ኢሳ. 9፡2)፡፡ ያ ዘመን የሰው ዘር በአጠቃላይ በሰማይም ሆነ በምድር፣ በነፍስም ሆነ በሥጋ ከባድ የሆነ የሞት ቅጣትን ያስተናገደበት ዘመን በመሆኑ ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኵነኔ ተብሎ ተገልጾአል፤ (ሮሜ 5፥12-19)፡፡ ይሁንና ምሕረት፣ ይቅርታ፣ ገደብ የለሽ ፍቅርና አዘኔታ ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር አምላክ አንድ ቀን ሰውን ከዚህ የሞት ቅጣት እንደሚታደገው ከመጀመሪያው አንሥቶ ተስፋውን ያሰማ ነበር፤ (ዘፍ. 3፥15፤ ዘፍ. 22፡፥6-18፣ ኢሳ. 53፥4-12፤ ዳን. 9፥24-27)፡፡

ከዘመን በኋላ እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት የባሕርይ ልጁ የሆነ ቀዳማዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድን ወደዚህ ዓለም ላከ፤ እሱም መጥቶ ሥጋችንን ተዋሐደ፤ የጥል ምክንያት የሆነውን ኀጢአትን ያጠፋ ዘንድ የኀጢአት መካካሻ ሆኖ በመስቀል ላይ መሥዋዕት ሆነ፤ በቀዳማዊ አዳም አለመታዘዝ የተበደለ እግዚአብሔር በዳግማዊ አዳም (በክርስቶስ) ድንቅ መታዘዝ ተካሰ፤ (ሮሜ 5፥19፤ 2ቆሮ. 5፥19፤ ዕብ. 5፥7-8)፡፡ በመሆኑም በዚህ መሥዋዕት ምክንያት እግዚአብሔር የዓለሙን ወይም የሰውን ኀጢአት ይቅር ብሎ የምሕረት በሩን ከፈተ፤ በሰውና በእግዚአብሔር የተገነባው ጥል ፈራርሶ በጥምቀትና በቅዱስ ቁርባን አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር የአባትና የልጅ የሆነ ግንኙነትን መመሥረት ተቻለ፤ (ኤፌ2፡13-16፤ ዮሐ.6፡56፤ ሮሜ.6፡3-4)፡፡ በቀለም፣ በዘር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት ወዘተ ተፈጥሮ የቆየውን የሰው ከሰው መለያየት ቀርቶ ሁሉም በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምኖ እንዲድን የሁሉም መዳኛ የሚሆን ስም ሰጠ፤ ‹‹ከሰማይ በታች ከዚህ ስም በቀር የምንድንበት ሌላ ስም የለምና›› ተብሎ እንደተጻፈው፤ (የሐዋ.ሥራ 4፥9-12)፡፡

ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ያህል ሥር ሰዶ የነበረው የጥል ግድግዳ በመስቀሉ ላይ በተፈጸመው የዕርቀ ሰላም መሥዋዕትነት ስለፈራረሰ ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት የሚከለክለን የለም፣ የኀጢአት ግንብ ቢኖርም እንኳ በንስሓ ይናዳል፤ ዛሬ በቀለም፣ በዘር፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በዕውቀት፣ በሀብት፣ በሥልጣን ወዘተ ከእግዚአብሔር ምሥጢረ ድኅነት የሚከለከል የለም፣ የሚጠየቀው አንድና አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ማመንና ቀጥሎም በሥነ ምግባር ተወስኖ መኖር ነው።

ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ጸንቶ የቆየው የጥል ግድግዳ የፈራረሰው በጌታችን በአምላካችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት ሲሆን፤ መሥዋዕትነቱም የተፈጸመው በመስቀል ላይ ነው፤ ለዚህም ነው ‹‹ጥልን በመስቀሉ ገደለ›› ተብሎ እየተነገረን ያለው፤ ሁላችንም እንደምናውቀው መግደል ማለት ማጥፋት፣ ህልውናን ማሳጣት ማለት እንደሆነ ለሁሉም ግልጽ ነው፤ከዚህ አንጻር ክርስቶስ በመስቀሉ ጥልን ገደለ ሲባል በፈጣሪና በፍጡራን መካከል የነበረውን የጥል ህልውና ጨርሶ አጠፋ ደመሰሰ ማለት እንደሆነ እናስተውላለን፤ ይሁንና በመስቀል የተፈጸመው ምሥጢር ጥልን ማጥፋት ብቻ አይደለም ዕርቅን፣ ሰላምን፣ አንድነትንና ነፃነትን በአጠቃላይ በመስቀል ላይ በተፈጸመው መሥዋዕትነት ተከናውኖአል፤ (ሮሜ 5፥10-11፣ 1ተሰ. 2፥13-15)፡፡ በመሆኑም መስቀልን ማሰብና ማክበር ሁለት ነገሮችን እንድናስታውስ ያስገድደናል፤ ይኸውም፡ (1) በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ያዳነን ክርስቶስንና የክርስቶስ ፍቅርን፣ (2) በመስቀል ላይ የተፈጸመው የድኅነታችን መሥዋዕትን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ስለሆነም መስቀሉን ማሰብ ማለት ክርስቶስንና የክርስቶስን የማዳን ምሥጢር ማሰብ ማለት እንደሆነ አንዘንጋ፤ መስቀል ሰላምን፣ አንድነትን፣ ነፃነትን ዕርቅን የሚሰብክና የሚያስተምር፣ ስለድኅነተ ሰብእ የሚመሰክር፣ የእግዚአብሔር የማዳን ዐርማ፣ የድልና የአሸናፊነት ምልክት ነው፤ ኀጢአትና ሞት ተሸንፈውበታልና (1ቆሮ. 15፥55-57)፡፡ ከዚህ አኳያ የክርስቶስ መስቀል ተራ ነገር ሳይሆን በስተጀርባው ነገረ ክርስቶስን ያዘለ በመሆኑ ክርስቶስንና የማዳን ተግባሩን እንደዚሁም የምንድንበትን መንገድ የሚያስተምረን ቅዱስ የሆነ ትእምርተ አድኅኖ ነው፡፡

በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ክፍለ ዘመናት የነበሩ አይሁዳውያንና ክርስቲያኖች የተጋጩበት ዐቢይ ነጥብ በዚህ መሠረታዊ ምክንያት ነው፤ ሁለቱም ክፍሎች ትእምርተ መስቀሉ ክርስቶስን በቀጥታ እየሰበከ እንደሆነ አልሳቱትም፤ በመሆኑም አይሁዳውያኑ ክርስቶስን መስበኩ እንዲያቆም ፈልገው መስቀልን በጒድጓድ ሲቀብሩት፣ ክርስቲያኖቹ ደግሞ መስቀሉ ከተቀበረበት ወጥቶ ክርስቶስን መስበክ አለበት በማለታቸው በመካከላቸው ቅራኔ ተፈጥሮአል፡፡ ይሁንና “የማታ ማታ እውነታ ይረታ” እንዲሉ፤ ምንም ቢሆን እውነት መርታቱ አይቀርምና መስቀሉ ከተቀበረበት ወጣ፤ እውነትም ረታ፤ እኛም ዛሬ በከፍተኛ ድምቀት የምናከብረው በዓል መስቀሉ ከተቀበረበት ጒድጓድ የወጣበትን ለማሰብ ብቻ ሳይሆን መስቀሉ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መድረክ አግኝቶ የክርስቶስን አዳኝነት ለዓለም ሕዝብ እንዲሰብክ፣ እንዲያስተምርና እንዲመሰክር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርም ጭምር ነው፡፡

ምስጋና ለኀያሉ አምላካችን ለእግዚአብሔር ይሁንና ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመናት ጥረት በዘመናችን እውን ሆኖ እነሆ መስቀለ ክርስቶስ ዓለምን በአጠቃላይ ለመስበክ የሚያስችል ምቹ መድረክ አግኝቶአል፡፡ ይኸውም በዓለ መስቀል በኢትዮጵያ ስም በተባበሩት የዓለም መንግሥታት ድርጅት መመዝገቡ ነው፤ በዚህም ለዚህ ታላቅ ዕድል ያበቃንን እግዚአብሔርን እጅግ አድርገን እናመሰግነዋለን፤ እንግዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀልን በዓል በከፍተኛ ሁኔታ የምታከብርበት ዋና ምክንያት የጥል ግድግዳን የሚያፈርስ፣ መለያየትን የሚንድ፣ በምትኩ ደግሞ ሰላምን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ መተማመንን፣ መቻቻልን፣ መተጋገዝን ፍጹምና ዘላቂ የሆነ ፍቅርን የሚያሰፍን በመሆኑ ነው፤ በተለይም ደግሞ ሰላምን በዋናነት ማግኘት የሚቻለው ከመስቀል አስተምህሮ በመሆኑ ነው፤ መስቀል ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› ብሎ ለገዳዮች ምሕረትንና ይቅርታን እየለመነ ፍጹም ፍቅርን ይሰብካል፤ መስቀል በንስሓ ለቀረበ በደለኛ ‹‹ዛሬውኑ ከኔ ጋር በገነት ትኖራለህ›› እያለ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ እንዲኖር ይጋብዛል፤ መስቀል ለሰው ድኅነት ሲባል ራስን አሳልፎ በመስጠት ፍጹም ድኅነትን ይሰብካል፤ ሌላም ለሰው ልጅ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ የሰላም ትምህርቶችን ያስተምራል፤ በትምህርቱም በነፍስና በሥጋ ያድናል፡፡

ዛሬ በሀገራችን አልፎ አልፎ የሚከሠተው የጥል መንፈስ ያለበት የሚመስል ክሥተት የመስቀሉ ስብከትና ትምህርት በቅጡ ካለማጤንና ካለማስተዋል የተነሣ እንደሆነ መገንዘብ አለብን፤ የመስቀልን ምልክት በአካሉ፣ በአንገቱ፣ በግንባሩና በልብሱ የተሸከመ ሰው ወንድሙን አይጠላም፣ መናናቅንም አያስተናግድም፣ መከፋፈልን፣ መለያየትን፣ መነታረክን፣ መጨቃጨቅንና ራስ ወዳድነትን የመሳሰሉ የዲያብሎስ የጥፋት ሠራዊት መስቀልን ባነገበ ክርስቲያን ዘንድ ቦታ የላቸውም፡፡ የመስቀሉ ትምህርት በእኛ አስተማሪነት የሰላም ምሥጢርነቱን በዓለሙ ሁሉ ለማዳረስ በምንሮጥበት በአሁኑ ጊዜ እኛው ራሳችን የመስቀል ትርጒም ሰላምና ፍቅር መሆኑን መረዳት አቅቶን በጥላቻ ዐይን የምንተያይ ከሆነ ስለመስቀል ማስተማር እንችላለን ብለን ሁላችንም በዓለም ሕዝብ ፊት ቃል የገባንበት የማስተማር ብቃታችን ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፤ መስቀል የገደለውን ጥል እንደገና ስበንና ጎትተን እንዳናመጣው ማሰብና መጠንቀቅ አለብን፡፡ ባለፉት ወራት በሀገራችን ውስጥ የተከሠቱ ግጭቶች ቤተ ክርስቲያናችንን ያሳዘኑና ያሳሰቡ መሆናቸውን ካሁን ቀደም ቤተ ክርስቲያናችን በየሚድያውና በየዐውደ ምሕረቱ በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷ አይዘነጋም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ሁሉም ኢትዮጵያውያን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከማእዷ ተቋዳሾች ናቸውና ሁሉም ኢትዮጵያውያን ልጆቿ እንደሆኑ በጽኑ የምታምንበት ጉዳይ ነው፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ነፃነትና እኩልነት አክብራ ከሦስት ሺሕ ዘመናት በላይ የሀገር አለኝታ ሆና የኖረችበት ምሥጢርም ይኸው ከእግዚአብሔር የተቀበለችው ሕዝብን አስማምታ የመጠበቅ አደራ በሚገባ መወጣት በመቻሏ እንደሆነ የሚካድ አይደለም፡፡

ስለሆነም የቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም ልጆችዋን በሰላምና በፍቅር ተንከባክባና አስማምታ ማገልገል ነውና የሀገራችን ሕዝቦች አንድነትና ነፃነት መከባበርና መተማመን፣ መቻቻልና መስማማት ተጠብቆ ይቀጥል ዘንድ እንደዚሁም የሀገራችን ሕዝቦች አንጸባራቂ ታሪክ ባህልና ትስስር በወቅታዊ ትኵሳት ፈተና ላይ እንዳይወድቅ ኢትዮጵያን ከልብ የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሰላማዊ፣ በወንድማዊና በሀገራዊ ፍቅር ችግሮችን በጋራ ውይይት እየፈታ በቆየው የወንድማማችነት መንፈስ ልማቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩሉን ያደርግ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታሳስባለች፡፡

በመጨረሻም፡ ሕዝባችን ከሰላምና ከፍቅር፣ ከመከባበርና ከመተማመን፣ ከወንድማማችነትና ከመፈቃቀር ጥቅም እንጂ ጕዳት እንደሌለ በጥልቀት የሚገነዘበው ነው፤ ኢትዮጵያ ሀገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታም ይህንን ሐቅ ያረጋገጠ ነው፤ በሰላምና በፍቅር ስንኖር ዐባይን የመሰለ ታላቅ ወንዝ መገደብ ችለናል፤ የሕዝቡ አንድነት ፍቅርና ሰላም እስከተጠበቀ ድረስ እንደአባቶቻችን ሌሎች ብዙ አስደናቂ የሆኑ የልማት ሥራዎችን ከመሥራት የሚገድበን እንደሌለ በሚገባ ተገንዝበናል፤ ስለሆነም የመስቀል መልእክትም፣ ትምህርትም ሰላምና ሰላም ብቻ ነውና የሀገራችን ሕዝቦች ከምንም በላይ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ረገድ የማያወላውል አቋም እንዲይዙ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡