ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ እና በሰሜን አሜሪካ የኒዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
በአጠቃላይ በዚህ መንፈስ ቅዱሳዊና ሐዋርያዊ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፤

የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አካሉ ስለሆነች ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለመምከርና ለመወያየት ስለ ሰበሰበን ቅዱስ አምላካችን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡

“ወሑሩ ባሕቱ ኀበ አባግዕ ዘተኀጒላ እምቤተ እስራኤል
ነገር ግን ከቤተ እስራኤል ወገን ወደ ጠቦት በጎች ሂዱ”
ማቴ. 0፥6፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሥጋ ሰብእ እንዲገለጥ ያደረገው ዐቢይ ምክንያት፣ የጠትን በጎች ለመፈለግ እንደሆነ ከሚያስረዱ ትምህርቶች አንዱ ይህ የጌታችን አስተምህሮ ነው፡፡

የጌታችን አገላለጽ ለጊዜው ቤተ እስራኤልን ብቻ የሚመለከት ቢመስልም በዚያ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ግን አልነበረም፤ ይህም “ወብየ ካልኣትኒ አባግዕ እለ ኢኮና እምዝንቱ ዐጸድ& ወኪያሆንሂ ሀለወኒ ኣምጽኦን ዝየ& ወይሰምዓኒ ቃልየ& ወይከውና አሐደ መርዔተ ለአሐዱ ኖላዊ፡- ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ& እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል& ድምፄንም ይሰማሉ& አንድም መንጋ ይሆናሉ& እረኛውም አንድ” ብሎ ባስተማረው ትምህርት ይታወቃል፡፡

ከዚህ አንጻር ቤተ ክርስቲያን የቆመች በዚህ ዓለም ለሚገኙ በጎች ሁሉ እንደሆነ እንገነዘባለን& ግልገሎቼን ጠብቅ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን ጠብቅ በማለት በቅዱስ ጴጥሮስ በኩል የነገረንም ይህንን የሚያስረግጥ ነው& እኛም በየጊዜው የምናካሂደው ሐዋርያዊ ሲኖዶስ ይህንን አደራ ለመወጣት ነው፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!!

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በረጅሙ ታሪኳ ለሕዝባችንና ለሀገራችን ብዙ መልካም ነገርን አውርሳለች& በአንጻሩ ደግሞ ብዙ የተጋድሎ መከራን ተጋፍጣለች፡፡ በዘመኑ ሁሉ የቤተ ክርስቲያናችን ዙርያ መለስ አካሏ በተቃራኒ ነገር የተከበበ ቢሆንም፣ እጅግ በሚያስገርምና በሚያስደንቅ ሁኔታ ራሷን በመከላከል እስካሁን ዘልቃለች& ይህንን ዓለም ያስደነቀ ታሪኳን የማስጠበቅና የማስቀጠል ኀላፊነት አሁንም በቅዱስ ሲኖዶስና በምእመናኗ ጫንቃ ላይ ያረፈ መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ከዚህ አንጻር በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ ያሉ አሉታዊ ገጽታዎችን በንቃት ማየት፣ መከታተልና መፍትሔን እያስቀመጡ መሥራት የዚህ ዐቢይ ጉባኤ ኀላፊነት መሆኑ ላፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡ጌታችን “አንሥኡ አዕይንቲክሙ ወነጽሩ በሓውርቲክሙ” ብሎ እንዳስተማረን በውስጥም፣ በውጭም በዙርያ ጥምጥም ሁሉ እየሆነና እየተቃጣ ያለው ፈተና በአጠቃላይ፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ሥጋት ላይ እንዳይጥል በጋራም ሆነ በተናጠል በንቃት መከታተል ያስፈልጋል፡፡

ሁሉም እንደሚመሰክረው ቤተ ክርስቲያናችን በሰው ሀብትም ሆነ በምጣኔ ሀብት ባላት ዐቅም በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ክፍለ አህጉር ብሎም በኦሪየንታሉና በምሥራቁ ኦርቶዶክስ ጭምር በግምባር ቀደም ወይም በመጀመሪያ የምትቀመጥ ናት፡ይህንንም ደማቅ ታሪክ በዓለም የታሪክ መዝገብ ለማስመዝገብ የበቃችው ቤተ ክርስቲያናችን ባላት የረጅም ጊዜ ታሪክ በምድረ አፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ የክርስትና ሃይማኖትን ህላዌ ለማስከበርና ዘላቂ ለማድረግ በፈጸመችው ጠንካራና ውጤታማ ተጋድሎ የተገኘ ነው፡፡

ይህ ለሦስት ሺሕ ዘመናት ተጠብቆ የዘለቀውን የተጋድሎ ደማቅ ስኬት በዙሪያችን ሆነው በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ እይታ የሚመለከቱ ብዙ ናቸው፡፡ ይህንን ልዩ ሀብታችንና ታሪካችን አደንዛዥ በሚመስል ስልተ ሂደት እንዳንነጠቅ ጠንክረን መሥራት ይገባናል& የቤተ ክርስቲያናችን ሰብኣዊና ቊሳዊ ሀብታችንን አደራጅተን& አቀናጅተንና አዘምነን ለአጠቃላይ የሃይማኖታችን ጥበቃ ማዋል ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ቤተ ክርስቲያናችን የሃይማኖት፣ የቀኖና፣ የባህልና የሥርዐት እንከን የላትም& በአስተዳደር ስልታችን ግን ገና ብዙ እንደሚቀረን ግልጽ ነው:: በመሆኑም ይህንን እውነት ከልብ ተቀብለን፣ ከዛሬ ጀምሮ ካሁን በፊት ከነበረው ይበልጥ ዛሬ ዘመኑ በሚጠይቀው ጥበብ የሀብታችን ተጠቃሚ ለመሆን፣ የሕዝበ ክርስቲያኑን ጥያቄ ለመመለስ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችንን ህልውና በቀጣይነት ዋስትና ባለው ድልድይ ለማሸጋገር በሐቅና በሐቅ በርትተን የምንሠራበት ጊዜ መሆን አለበት፡፡

ታዲያ የምንመኘውና የምናልመው ሁሉ እውን ሊሆን የሚችለው ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ባለው የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር መልካም አስተዳደርን ስናሰፍን እንደሆነ መዘንጋት የለብንም& በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ መልካም አስተዳደር ካልተረጋገጠ እያኮረፈንና እየተወን ከሚሄድ በቀር ፍልሰተ ምእመናንን ማስቆምና ስንዝር የሚያህል እድገትን ማስመዝገብ አንችልም፡፡ ስለዚህ ቀጣዮቹ ዓመታት ቤተ ክርስቲያናችን በሁሉም አቅጣጫ መልካም አስተዳደርን የምታረጋግጥባቸው ዓመታት እንዲሆኑ በመወሰን የማስፈጸም ኀላፊነቱን መውሰድ አለብን፡፡

በሌላ በኩል መልካም አስተዳደር ያለ ፍትሕና ያለ ልማት የትም ሊደርስ አይችልምና ፍትሕ ይሰፍን ዘንድ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት በሀገር ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ ሥራ እንዲጀምር ያላሰለሰ ጥረት ብናደርግ፣ የልማትን ጉዳይ በተመለከተም የቤተ ክርስቲያናችንን የሀብት ምንጮች አጥንቶ፣ ለይቶና የትግበራ ሂደታቸውን አመላክቶ የሚያቀርብልን ከፍተኛ ባለሙያዎች ያሉበት ግብረ ኀይል በማቋቋም ወደ ግዙፍ የልማት መርሐ ግብር ብንሸጋገር፣ የምእመናን ጥበቃና አገልግሎትም በተመሳሳይ ሁኔታ ልዩ ስልት እና ጥበብ ተቀምጦለት ምእመናንን በመንፈስ ቅዱስ ኀይል የምንጠብቅበትንና የምናበዛበትን የትኲረት አቅጣጫ ብናስቀምጥ፣ በአጠቃላይ ዳር እስከ ዳር እየተናበብን በመሥራት ፈጣን እድገት የምናስመዘግብበትን ስልት ብንቀይስ፣ እግዚአብሔርና ምእመናን ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሹትን ማሟላት እንችላለን፡፡ ስለሆነም ጉባኤያችን በነኝህ ዙርያ በስፋትና በጥልቀት መክሮበት ወደ ተግባር ቢሸጋገር መልካም ነው እንላለን፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ሌላው በዚህ ዐቢይ ጉባኤ ትኲረት ሰጥተን መነጋገር ያለብን የሀገራችንን የሰላም ጉዳይ በተመለከተ ነው& መቼም ቤቱ እየተቃጠለ ዝም ብሎ የሚያይ ሰው ይኖራል ብለን አናስብም& ዛሬ የሁላችን ቤት የሆነች ሀገር በሰላም ዕጦት ከባድ ችግር ውስጥ ናት፡፡

በዚህ አስከፊ ጦርነት ሰውም፣ ንብረትም ቤተ ክርስቲያንም ክኛ እየተጐዱ ነው& እነዚህ ሁሉ የቤተ ክርስቲያናችንና የሀገራችን ምርጥ ቤቶች ናቸው& ቤቶቹ ተቃጥለው ይለቁ ወይስ ምን እናድርግ;ነው ጥያቄው& መልሱ ከቤቱ ቢሆን ምርጫችን ነው& ለማንኛውም ግን ቤተ ክርስቲያናችን ነገ የምትነቀፍበት፣ እኛም የምንገመገምበትና የምንተችበት ታሪክ አስቀምጠን እንዳናልፍ በብርቱ ልናስብበት ይገባል:: ከዚህ አኳያ የሀገራችንን ችግር የመፍትሔ አቅጣጫ በቅንነት፣ በገለልተኝነት፣ በማእከላዊነት እና በአቃፊነት መንፈስና እንደዚሁም፣ ሰላምንና አንድነትን፣ ዕርቅንና ይቅርታን ማእከል ባደረገ መንፈስ ብናየው ለቤተ ክርስቲያንም ለእኛም ይበጃል፡

በመጨረሻም፡ በሀገር ላይ እየተካሄደ ያለው ጦርነትና እሱን ተከትሎ ያንዣበበው የሥጋት ደመና ወደ ባሰ ጥፋት እንዳይወስደን የሀገራችን ችግሮች በሙሉ በሰላማዊ ውይይት ይፈቱ ዘንድ የሚመለከታቸው ሁሉ ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርጉ፣ በጦርነቱም ሆነ በድርቁ ምክንያት በረሀብና በበሽታ እየተጐዱ ላሉ ልጆቻችንም የምግብና የሕክምና አቅርቦት እንዲያገኙ ይደረግ ዘንድ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እያስተላለፍንና ቤተ ክርስቲያንም በዚህ ረገድ የበኩሏን ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን እየገለጽን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የጥቅምቱ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተከፈተ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑ እናበሥራለን።

እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፤

ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም 41ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በሰሜን አሜሪካ የኒዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳስት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
የተከበራችሁ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኀላፊዎች፤
የየአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆችና የየክፍሉ ኀላፊዎች፤
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኀላፊዎችና የየሀገረ ስብከቱ ተወካዮች፤
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣት ልጆቻችን፤
በውጭ አህጉር ከሚገኙ ልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት የመጣችሁ እንግዶች፤
በአጠቃላይ በዚህ ዓለም ዐቀፍ ጉባኤ ለመሳተፍ በዚህ ቅዱስ ስፍራ የተገኛችሁ ክቡራንና ክቡራት፡-

ሁሉ የሚቻለው የሚሳነው ነገርም የሌለው አምላካችን እግዚአብሔር አርባ አንደኛውን ዓለም ዐቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤ በዚህ ሰዓት እንድናካሂድ ስለፈቀደልን ክብርና ምስጋና አምልኮና ውዳሴ ለእሱ ይሁን፡፡ እናንተንም አቅፎ ደግፎ በሰላም ወደ ሀገራችሁና ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናችሁ መንፈሳዊ ጉባኤ ስላመጣልን በድጋሚ እሱን እያመሰገን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ደስታችንን ልንገልፅላችሁ እንወዳለን፡፡

“ገሥጽዎሙ ለሕዝብየ ወአጽንዕዎሙ ይቤ እግዚአብሔር
አጽናኑ፣ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል እግዚአብሔር”
(ኢሳ. 40፥1)

ይህ ቃል የኀያሉ አምላካችን የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ቃሉ እንደሚያመለክተው በዚህ ዓለም ያለው ሕዝብ ባለቤት ያለው መሆኑን ነው፡፡ ማንኛውም ፍጡር በራሱ ለራሱ የተፈጠረና በሕይወት የሚኖር የለም፡፡ ሁሉም በእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር ተፈጠረ፥ ለእግዚአብሔርም በሕይወት ይኖራል፡፡

ሰው በዚህም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም ለእግዚአብሔርና የእግዚአብሔር እንደ ሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ሲነግረን፡- “ወአልቦ እምውስቴትነ ዘለርእሱ የሐዩ፣ ወዘለርእሱ ይመውት፤ እመኒ ሐየውነ ለእግዚአብሔር ነሐዩ፤ ወእመኒ ሞትነ ለእግዚአብሔር ንመውት፤ እመኒ ሐየውነ ወእመኒ ሞትነ ለእግዚአብሔር ንሕነ፡- ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና ለራሱም የሚሞት የለምና፣ በሕይወት ብንኖር ለእግዚአብሔር እንኖራለን፤ ብንሞትም ለእግዚአብሔር እንሞታለን፤ በሕይወት ብንኖርም፣ ብንሞትም የእግዚአብሔር ነን ይለናል፡፡

ከዚህ ትምህርተ እግዚአብሔር እንደምንገነዘበው ሰው በዚህም ዓለም ሆነ በወዲያኛውም ዓለም፣ በሕይወት የሚኖር እንጂ የሚጠፋ አለመሆኑን፣ በዚህም ኖረ በዚያ ምን ጊዜም የእግዚአብሔር ገንዘብ መሆኑን፣ በዚህም ሆነ በዚያ ለእግዚአብሔር እንጂ ለራሱ እንዲኖር ያልተፈጠረ መሆኑን በግልጽ ያስረዳናል፡፡

ዋና ጭብጡ ሰው ፈቅዶ የፈጠረው ዛሬም ሆነ ለወደፊት የሚፈልገው ባለቤት ያለው መሆኑን፣ እሱም እግዚአብሔር እንደ ሆነ በውል ማስገንዘብ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ነው የሕዝቡ ፈጣሪና ባለቤት የሆነ እግዚአብሔር የእርሱ የሆነውን ሕዝብ እንከን እንዲነካው አልፈቀደም፤ ባለመፍቀዱም “ኢትግሥሡ መሲሓንየ፡- ማለት በልጅነት ያከበርኳቸውን ሕዝቤን አትንኩ” ብሎ ሲያስጠነቅቅ እንሰማለን፤ የሚነካም ካለ እናንተ “ሕዝቤን አጽናኑ” ብሎ አዝዞናል፡፡ የተነካውን ሕዝበ እግዚአብሔር ማጽናናት የእኛ ተቀዳሚ ተልእኮ እንደ ሆነ ይህ ዐቢይ ጉባኤ በአጽንዖት ሊቀበል ያስፈልጋል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡ የተከበራችሁ እንግዶች!!
በዚህ አሁን ባለንበት ዘመን የእግዚአብሔር ሕዝብ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው ብሎ መጠየቅ ከኛ ይጠበቃል፡፡ ሕዝባችን በአሁኑ ጊዜ ሕይወቱንና ንብረቱን፣ ልጁንና ሚስቱን፣ ቤተ ሰቡንና ሰላሙን እያጣ ነው፡፡ ያላጣው ነገር የለም፤ ሁለመናው ተነክቶአል፡፡ ይህ ሲሆን እኛ ማድረግ ያለብን ነገር ምን እንደሆነ ተነግሮናል፤ እርሱም ማጽናናት ነው፡፡ ከማጽናናትም አልፎ ቤዛ ሆኖ እስከ መሰጠት ድረስ መራመድ ነው፡፡

ያለንበት ጊዜ ይህንን ሁሉ እየጠየቀን ነው፡፡ ሕዝቡን ማጽናናት ከኛ ይጠበቃል፡፡ ሕዝቡን የምናጽናናው በቃላት ብቻ ሊሆን አይገባም፤ በመሐሉ ገብተን በመገሠጽና በመምከር፣ በማስተማርና በማሳመን፣ በማስታረቅና እፎይታን በማጐናጸፍ ሊሆን ይገባል፡፡ ሕዝቡ ሕዝባችን ነው፤ እኛም የእርሱ ነን፡፡ ሕዝባችን እርስ በርስ ነው እየተላለቀ ያለው፤ ሌላ ተጨማሪ ቢኖርም ከኛ በተፈጠረው ክፍተት እንጂ በሌላ አይደለም፡፡ ሕዝባችንን የሚያጣላና የሚያፋጅ፣ አሁን ከደረሰበት ደረጃም የሚያደርስ በቂ ምክንያት የለውም፡፡ ቢኖርም በውይይትና በምክክር፣ በፍቅርና ጊዜ ሰጥቶ በማሰላሰል መልክ ሊይዝ የሚችል ነው፡፡ መሬቱ እንደሆነ የትም አልሄደም፤ ሊሄድም አይችልም፤ እዚያው ከነበረበት ነው ያለው፡፡ ሕዝባችንን ግን ከነበረበት እያገኘነው አይደለንም፡፡ በዚህ ዓለም ድጋሚ ላናገኘው አግባብ በሌለው አኳኋን በየቀኑ እየተሰናበተን ነው፡፡ አሁን ጥያቄው ምን እናድርግ? ነው፤

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡራን እንግዶቻችን፤

ዛሬ ተሰብስበን የምንነጋገረው ስለ ሰበካ ጉባኤ ነው? ወይስ ስለመልካም አስተዳደር? ሕዝቡ ከሌለ እኮ ሃይማኖቱም፣ ገቢውም፣ አስተዳደሩም ነገ ሊቆም ይችላል፡፡ እዚህም እዚያም በየቀኑ እንደቅጠል እየረገፈ ያለው እኮ በመስቀላችን ያጠመቅነው፣ ማዕተበ ክርስትና ያሰርንለት፣ ለእግዚአብሔር መንግሥት አጭተን ያዘጋጀነው፣ ቤተ ክርስቲያንን ተረክቦ ሊያስቀጥልልን ዐይናችንን የጣልንበትና ተስፋም ያደረግንበት ልጃችንና ወገናችን ነው፡፡ ዝም ብሎ ማየቱ አያስጠይቅም ትላላችሁ?

እኛ ግን በእግዚአብሔርም፣ በሰውም፣ በታሪክም፣ በሞራልም ያስጠይቃል ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ ውስጥ እየተሳተፋ ያሉ ሁሉም ልጆቻችን ናቸው፡፡ የተጣሉበትንም ነገር በውል ማወቅ አንችልም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር እናውቃለን፤ እሱም ሁሉም የኛ ልጆች መሆናቸውን እና ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ነው፡፡ በመሆኑም ከነዚህ ውስጥ አንድስ እንኳ እንዲሞትብን ወይም እንዲጐድልብን አንፈልግም፡፡ ሁሉም በሕይወት፣ በሰላምና በጤና እንዲኖሩልን እንሻለን፡፡

ፍጅትና እልቂት ይጐዳናል እንጂ ማናችንንም አይጠቅምም፡፡ እስካሁን ጦርነት ይጠቅማል ብሎ ሲናገር የሰማነው አንድ ስንኳ የለም፡፡ ታድያ ለማይጠቅም ነገር ለምን እንለፋለን? ከኛ ውጭ ያለው ዓለም ግጭቱ ቆሞ ሰላማዊ ውይይት ይካሄድ ሲል፣ መንግሥትም ሲቀበል፣ በሌላ በኩል ያለው ወገናችንም ሲቀበል፣ እኛስ ይሄንን ደግፈን ድምፃችንን ለሕዝባችን፣ ለመንግሥት እና ለሰላም እየተጋ ላለው የዓለም ዐቀፍ ማበረሰብ ብናሰማ ተገቢ አይደለምን? ይህንን በተመለከተ የነገሩን አሳሳቢነት ከልብ ተገንዝቦ ይህ ጉባኤ የሚለው ነገር እንዲል እንጠብቃለን ፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡራን እንግዶቻችን!!

መቼም “እምነ ረኃብ ይኄይስ—-” እንደተባለው ሞትም ቢሆን እየበሉ ቢሆን ነውና የሚሻለው፣ በሰበካ ጉባኤ ሕገ ደንባችን መሠረት የቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ የሀገራችን ምጣኔ ሀብትን የማሳደግ፣ የመጠበቅና ፍትሓዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ማረጋገጥ የኛ ሌላኛው ተልእኮ ነው፡፡

ሰበካ ጉባኤ የተቋቋመውም ለዚህ ተብሎ እንደሆነ ሁላችሁም ታውቃላችሁ፤ ጠቃሚ ውጤቱም በተጨባጭ እየታየ ነው፡፡ ነገር ግን፡-

• የሰበካ ጉባኤ አመሠራረትና ጒዞው፣
• አሁን ያለበት ደረጃ ትክክል ነው ወይስ የሚቀረው አለ?
• የቀረው ካለስ ለምን አናስተካክለውም?
• ለወደፊትስ የሰበካ ጉባኤ ሀብተ በረከት እንደሚፈለገው በፍጥነት አድጎ ለሕዝቡ ተደራሽ እስከ መሆን ለምን አናደርሰውም? በሚል ትክክለኛና ሙያዊ ጥናት ተካሂዶ ለዚህ ጉባኤ ማቅረብ የሚቀርብን ይመስለናል፡፡

ይህ ነጥብ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ በሁለቱም ጉባኤያት እንድናየው ቢደረግ መልካም ይመስለናል፡፡ ምስጋና ይድረሳቸውና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስና ከጎናቸው የነበሩ ሊቃውንት አባቶች ለሰበካ ጉባኤ መመሥረትና ሥር መስደድ እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት እንደከፈሉ ይህ ጉባኤ መርሳት የለበትም፡፡ የእነርሱ ክብርና ሕያው ታሪክ መጠበቅ ያለብን በጽሑፍና በንግግር ብቻ ሳይሆን የሰበካ ጉባኤ ዐላማ ሙሉ በሙሉ ግቡን መትቶ ቤተ ክርስቲያን ከገጠር እስከ ከተማ ራሷን ስትችል፣ ከዚያም አልፋ ተርፋ በየቤተ ክርስቲያኑ የአብነት ት/ቤቶችና የዘመናዊ ት/ቤቶች በብዛትና በጥራት ተከፍተው፣ የሕዝበ ክርስቲያኑ ልጆችንና ሌሎችንም አቅፋ ስታስተምር፣ ዕጓለ ማውታና አረጋውያን ስትጦር፣ ሕሙማንን ስትፈውስ በአጠቃላይ የሕዝበ እግዚአብሔር እናትነትዋን በሚገባ ስትወጣ በማሳየት ሊሆን ይገባል፡፡ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ በቅጡ ባይያዝም ከገቢ አንጻር በከተሞች አካባቢ የተሻለ የሰበካ ጉባኤ ሀብተ በረከት ይታያል፡፡

እሱም ቅዱሱ ሕዝበ እግዚአብሔር በሙዳየ ምጽዋት ከሚያኖረው በረከት እንጂ፣ አስተምረንና ተከታትለን፣ ቀስቅሰንና አሳምነን በቃለ ዐዋዲው መሠረት አስተዋፅኦውን እንዲከፍል አድርገን እንዳልሆነ ጥቆማ ይደርሳል፡፡ በገጠርም በተመሳሳይ ሁኔታ ኮታ እየተጣለ የሚሰበሰብ እንጂ እያንዳንዱ ምእመን አስተዋፅኦውን በትክክል እንዲከፍል እያደረግን እንዳልሆነ ይሰማል:: ከዚህም ጋር በየመንገዱ የሚንጠባጠበው በዚያው ልክ እንደ ሆነ ይደመጣል፡፡ ታድያ እንዲህ ሲሆን ዝም የምንል ከሆነ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መንፈስ አይወቅሰንም? ለምንስ እንወቀሳለን? ጉባኤው ከተቀበለን አሁን አጥብቀን የምናሳስበው የሰበካ ጉባኤ ጉዛችን ምን እንደሚመስል በባለሙያዎች በትክክል ቢጠናና ቢገመገም፣ ከዚያም አይተነው ወደ ተሻለ የእድገት ጒዞ ብንራመድ እንላለን፡፡ ምክንያቱም አንድ ሥራ በየጊዜው እየተገመገመ፣ እየታረመና እየተስተካከለ ካልተሠራ የሚቀረው ነገር አይታጣምና ነው፡፡

ከዚህ በተረፈ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ሰጭነትና መሪነት ደጋውን ወጥታችሁ፣ ቈላውን ወርዳችሁ ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ አገልግሎቷን በማስቀጠል ሁላችሁም የቤተ ክርስቲያናችን ተጠሪዎች ላደረጋችሁት የላቀ አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርብላችኋለን፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አርባ አንደኛውን ዓለም ዐቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በእግዚአብሔር ፈቃድ የከፈትን መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑ እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡