ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ችግር አስመልክቶ ከሰኔ 21 እስከ ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ለሁለት ሱባኤ ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ መታወጁን ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ እየታየ ያለውን ወቅታዊ የሰላም ዕጦት አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ
ሀገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ በዓለም የምትታወቅበት የነበረ ሀብቷ ሰላም አንድነትና አብሮነት ሆኖ ሕዝቧ በፈሪሀ እግዚአብሔርና በበጎ ሥነ-ምግባር የሚታወቅ አገሪቱ የአየር ንብረቷ ለዜጎቿ ቀርቶ በውጭው ዓለም የሚገኙ ሁሉ የሚናፍቁት የሰው ልጅ መኖሪያና ምድረ-ገነት መሆኗን ዓለም የሚገነዘበው ሐቅ ነው፡፡ በእነዚህ በርካታ ዘመናትም በአገሪቱ ውስጥ በመሪና በተመሪ በአጠቃላይ በዜጎች መካከል የነበረው የመከባበር እርስ-በርስ የመግባባትና የመፈቃቀር ሁኔታ አልፎ አልፎ ዕንቅፋት ቢያጋጥመውም የቀደሙ አባቶቻችን የነበራቸው የችግር አፈታትና ወደ አንድነት ለመመለስ ያደርጉት የነበረ ጥረትና ተቀባይነቱም በእጅጉ የሚያስመሰግን እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ግን በአገራችን እየታየ ያለው ችግርና አለመግባባት ከእርስ በርስ ግጭትና ከውይይት አለመግባባት አልፎ እስከ ሕይወት መጠፋፋት መድረሱ የአገራችንንና የዜጎቿን የዘመናት አኵሪ ታሪክና ምሳሌነት እንዳልነበር ያደረገው መሆኑ መላውን ዜጎችም በሀገራዊው ሰላም ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ያደረገ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ይኸው ሀገራዊ ችግር አስመልክቶ የግንቦት ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሰፊው ተነጋግሮ ችግሩ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ማድረግ እንዲቻል ችግር ባለባቸው የአገራችን ክልሎች ሁሉ ዕርቀ ሰላም ማውረድ በቀጣይም ችግር እንዳይፈጠር መከላከል እንዲቻል ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ያካተተ የሰላምና የአንድነት ኮሚቴ መሰየሙና ለዚሁ የሰላም ተልእኮ ማስፈጸሚያ በጀት መመደቡና የሰላም ኮሚቴውም ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡
ሆኖም በአገራችን እንደ ችንሽ ነገር እየተቈጠረ የተጀመረው አለመግባባት በየክልሉ ለብዙዎች ዜጎቻችንና ሕይወት መጥፋትና ከቄያቸው መፈናቀል ለረኃብና ለስደት መዳረግ ምክንያት መሆኑ ከዚያም አልፎ ተርፎ የአገርን ህልውና አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ እስከ ሕይወት መጠፋፋት መድረሱ ከወዲሁ በአጭሩ እስከአልተቋጨ ድረስ በቀጣይ ምን ሊመጣ እንደሚችል መገመቱ ቀላል አይሆንም፡፡
ስለዚህ የሀገራችን ዜጐች ሁሉ ስለዚህች እናት ሀገራችን ስትሉ ትናንት የነበረውን የመከባበርና የአንድነት ባህላችሁን አጥብቃችሁ በመያዝ ለነገ ትልቅ ተስፋ ያላት አገራችን እንደምኞታችንና ሐሳባችን ካሰብነው ደርሳ ልማቷ አድጎ፥ አንድነቷ ተጠብቆ ሕፃናት የሚያድጉበት፣ ሽማግሌዎች የሚጦሩበት፣ የሁሉ ተስፋ የሆነች አገር እንድትኖረን ለማድረግ ሁላችሁም የዜግነታችሁን እንድታበረክቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ከዚህም ጋር የሰላም አምላክ ሰላም ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር ጸሎታችንና ልመናችንን ሰምቶ መዓቱን በምሕረት ቍጣውን በትዕግሥት እንዲመልስልን በአገራችንም ሆነ በውጭው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር በሚገኙ ገዳማትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ከዛሬ ሰኔ 21 እስከ ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ሁለት ሱባኤ ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ አውጇል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!