ከጥቅምት 11 ቀን እስከ 21 ቀን 2011 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ አንድ ቅዱስ ሲኖዶስ

ከጥቅምት 11-21 ቀን 2011 ዓ.ም. የተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በአንድ ቀኖናና ማእከል እንድትመራ ሲወስን፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በካህናትና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ጥቃት በማውገዝ ጥቃቱ እንዲቆም መንግሥትን ጠይቋል፡፡ ይኽንንና ሌሎች ውሳኔዎችን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እንደሚከለተው አሰምተዋል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቍጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልአተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዐተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሂድ ሰንብቶ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡ በዚሁ መሠረት፤

1. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቀረበው አጀንዳ ተራ ቊጥር አንድ ላይ በተገለጸው የጉባኤ መክፈቻ ንግግር የተመዘገበው ፍሬ ሐሳብ የበጀት ዓመቱ መመሪያ ሆኖ ያገልግል ዘንድ ምልአተ ጉባኤው ተቀብሎታል።
2. የብፁዓን አባቶች የሥራ ምደባና ዝውውር በማስፈለጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለውን ሁኔታ ከመረመረ በኋላ ዝውውሩን አከናውኗል፤ አዲስ የሥራ ምደባም ተካሂዷል፡፡
3. በሀገራችን ኢትዮጵያ በአንዳንድ ክልሎችና ዞኖች ተከሥቶ የነበረው ኅልፈተ ሕይወት፣ የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠልና የንብረት መውደም የዜጎች መፈናቀል ይገታ ዘንድ በመደጋገም የተላለፈው ጥያቄ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግሥት በኩል ተቀባይነትን ያገኘ ቢሆንም፤ አሁንም በሀገሪቱ አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ እየተሰማ ነው፡፡ ስለዚህ ከየአቅጣጫው እየተሰማ ላለው ችግር አስቸኳይ መፍትሄ ተፈልጎ እንዲገታ ካልተደረገ እየሰፋና እያደገ ሊሄድ ስለሚችል መንግሥት ከዐቅም በላይ እየሆነ ለሚታየው ችግር አጽንዖት ሰጥቶ አስፈላጊውን ሕጋዊ መፍትሄ እንዲገኝ በማድረግ ተገቢውን እንዲፈጸም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በድጋሚ ያሳስባል፡፡
4. የዘንድሮውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ልዩ ታሪካዊ ጉባኤ ከሚያደርጉት መካከል፣ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አራተኛ ፓትርያርክ፣ አብረዋቸው ከነበሩት አባቶች ጋር ወደ እናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ የመመለሳቸው ጉዳይ አንዱ እንደሆነ አያጠያይቅም፤
5. ለኢትዮጵያ ምእመናን ከኤርትራ ምእመናን፤ ለኤርትራ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም የኤርትራ ቤተ ክርስቲያን የመፈቃቀርና የአንድነት እንዲሁም የበለጠ የክፉ ቀን ደራሽ ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ ስለዚህ በሁሉም መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ተቀራርቦ እየሠሩ መረዳዳት ይቻል ዘንድ ከወዲሁ ሁኔታዎችን የሚያመቻች የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
6. በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የጸደቀው ሠላሳ ሰባተኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ መግለጫ በአፈጻጸም ዙሪያ የሚከሠት ችግር ካጋጠመው በቋሚ ሲኖዶስ እየተመረመረ ለውጤት ይበቃ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቶ መመሪያ አስተላልፏል፤
7. በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ያለው የሰላም ዕጦት ችግር በቀላሉ የሚገታ ሆኖ ካልተገኘ ወደፊት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊከሠቱ ይችላሉ የሚል ሥጋት አለ፤ ስለዚህ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዐት የወንጌል ስምሪት ተዘጋጅቶ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትምህርተ ወንጌል ተጠናክሮ እንዲሰጥ ሆኖ ከዚህም ጋር ከኅዳር 1 እስከ ኅዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መመሪያውን አስተላልፎአል፤
8. በተቀረጸው አጀንዳ መሠረት አቤቱታ የቀረበባቸውን አህጉረ ስብከቶች በተመለከተ መርምሮና አጣርቶ መፍትሔን የሰጠ ሲሆን በአንጻሩ ከቅን አስተዳደር የሚጠበቅ ድርሻ ስለሆነ አስተዳደራዊ ችግር ያጋጠማቸው አህጉረ ስብከት ተመርምረው ውጤታቸው ተፋጥኖ ይቀርብ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያን ሰጥቷል፡፡
9. በበጀትና ሒሳብ መምሪያ በኩል የቀረበው የዘመኑ ገቢና ወጭ ሒሳብ ሪፖርት ከተሰማ በኋላ ገቢው በትክክል እንዲመዘገብ ሆኖ፤ የወጭው አርእስት ተጠብቆ በበጀት ዓመቱ እንዲሠራበት ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያን ሰጥቷል፡፡
10. በጥንታዊት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በመንፈሳዊውም ሆነ በማኅበራዊው ረገድ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን ቅዱስ ሲኖዶስ ገምግሟል፡፡ በቀጣይም የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልእኮ ለማስፋት በቤተ ክርስቲያኒቱ ከላይ እስከታች የሚተገበር የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ችግርና መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶ የቀረበ በመሆኑ ለዚሁ ተግባር በተከፈተው ጽ/ቤት ሥራው እንዲቀጥል፣ በውጭ አገር ለምትገኘውም ቤተ ክርስቲያናችን የየአገሮቹን ሕገ መንግሥት ባገናዘበ መልኩ ቃለ ዐዋዲ እንዲዘጋጅና ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በመዋቅራዊ አስተዳደር እንዲመራ ተወስኖአል፡፡
11. አሁን በቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ሲኖዶስ መካከል የተፈጠረው አንድነት ለቀጣይ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥራችን መቃናት በር ከፋች በመሆኑ ከአሁን በኋላ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ያለችው ቤተ ክርስቲያን በአንዲት ቀኖናዊት ቤተ ክርስቲያን በማእከል እንድትመራ ወስኗል፡፡
12. ከሐምሌ ወር በዋሽንግተን ዲሲ የሁለቱ ሲኖዶስ ልኡካን የስምምነቱን ሰነድ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተቀበሎ በማጽደቅ በሰነድነት እንዲቀመጥ ወስኗል፡፡
13. በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በዴር ሡልጣን ገዳማችን ይዞታ ላይ እየታየ ያለው ችግር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ከመሄዱ የተነሣ ችግሩ ይፈታ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽሑፍም ሆነ በቃል ለሚመለከተው ሁሉ በአካል ቀርቦ ከማመልከት የተገታበት ጊዜ እንደሌለ ይታወቃል፤ ታሪካዊ እውነትን ለመሻር በማይገባ ሁኔታ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሌላት ርስትና መብት የዴር ሡልጣን ገዳማችን ባለቤትነታችንን ለማሳጣት ብዙ የፈጠራ ወሬዎችን በመንዛት የተሰማሩት ግብጻውያን ኮፕቲኮች ሊያውቁት የሚገባ ትልቁ ጉዳይ በማን ርስት ማን ያዝዛል? ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሕይወታቸውን ሳይቀር መሥዋዕት በማድረግ ሃይማኖታቸውንና ጥንታዊ ታሪካቸውን ጠብቀው ለእኛ አስረክበውናል፤ እኛም ጠብቀን ለትውልዱ የማስረከብ ኀላፊነታችንን እንወጣለን፡፡ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ በይዞታችን ላይ አግባብነት የሌለው ሥራን የማደናቀፍና በታሪክም ሆነ በማንኛውም የሰነድ መረጃ የሌለው የባለቤትነት ጥያቄ በማንሣት እየተፈጠረ ያለውን አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ ማቆም አለባቸው፤ ዴር ሡልጣን ትናትም ዛሬም ነገም የኢትዮጵያ ገዳም ነው፡፡ ዳሩ ግን መፍትሔውን ከማስገኘት ይልቅ እየደረሰ ያለው ተጽዕኖ እየሰፋና እየከበደ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ገዳሙን በሚጠብቁና በሚቈጣጠሩ መነኮሳት ላይ በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ያልተጠበቀ ከፍተኛ ችግር እየደረሰ ስለሆነ የችግሩን አስገዳጅነት አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥት የጉዳዩ ባለቤት እንደመሆኑ አስፈላጊውን መፍትሔ እንዲያስገኝልን እንጠይቃለን፡፡
14. የቦታቸው ታላቅነትና የታሪካቸው ስፋት ዓለም ዐቀፍ ዕውቅናን ባስገኘላቸው በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን እየተገነባ ላለው ሙዝየምና፣ የመሰነጣጠቅ አደጋ ለሚታይበት ለቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለጥገናና ለግንባታ አገልግሎት የሚውል ገንዘብ ተፈቅዷል፤ በዚሁ መሠረት፤ ለርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሥራ ማከናወኛ ብር 20,000,000 /ሃያ ሚሊዮን ብር/ ለቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ማስጠገኛ፤ ብር 20,000,000 /ሃያ ሚሊዮን ብር/ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ወጭ ሆኖ እንዲሰጥ ተወስኗል፤
15. አንዳንድ ግለሰዎች በግልና በቡድን በመደራጀት የቤተ ክርስቲያኗ መብትና ቀኖና እየተጋፉ መሆናቸውን ከቀረበው ሪፖርት ጉባኤው ተገንዝቧል፡፡ ስለዚህ መንግሥት በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩትን የሕግ ከለላ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ዐበይት ጉዳዮች ላይ ለ11 ቀናት ያህል በአገር ዐቀፍና በዓለም ዐቀፍ ጉዳዮች በስፋትና በጥልቀት ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቅቋል፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

የግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በዴር ሡልጣን ገዳማችን የምታደርገው
ከታሪክ የወጣና ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ የተወገዘ ነው፡፡

ከጥቅምት 11-21 ቀን 2011 ዓ/ም የተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልአተ ጉባኤ የኢትዮጵያ ይዞታ በሆነው በዴር ሡልጣን ገዳም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ እድሳት ወቅት የግብጽ እስክንድርያ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ያሳየችውን ሕገ ወጥ ተቃውሞ አውግዟል፤ ይህንንና ሌሎች ውሳኔዎች በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እንደሚከለተው አስታውቀዋል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
የኢትዮጵያውያን ይዞታ በሆነው በዴር ሡልጣን ገዳም የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ እድሳት ላይ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ያሳዩትን ሕገ ወጥ ተቃውሞ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መግለጫ፤

ሁላችሁም እንደምታውቁት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም ካሏት ጥንታውያንና ታሪካውያን ቅዱሳት መካናት ውስጥ አንዱና ዋናው በዴር ሡልጣን የሚገኘው የመድኀኔዓለም፣ የአርባዕቱ እንስሳ እና የቅዱስ ሚካኤል ገዳማት ናቸው፡፡ ከታሪክ እንደምንረዳው ኢትዮጵያውያን በምድረ እስራኤል የነበራቸው ርስት ከሦስት ሽህ ዓመት በላይ ያስቈጠረ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የአሁኗ ኢትዮጵያ መልክዐ ምድራዊ መገኛዋን ከዐባይ ምንጭ ጋር በማያያዝ ያለምንም ማሳሳት ከአርባ ጊዜ በላይ የተመዘገበች፤ በታሪክ፣ በእምነትና በማኅበራዊ ትስስር ከእስራኤል ጋር የጸና ግንኙነት ያላት ሀገር ናት፡፡

ከንግሥተ ሳባ የኢየሩሳሌም ጒብኝት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ወደ ቅድስት ሀገር ያለማቋረጥ በየዓመቱ በዓለ ፋሲካን ለማክበር፣ ዓመታዊ አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም፣ በርስት የተሰጣቸውን ይዞታ ለማስከበርና በንግድ ሥራዎች ይጓዙ እንደነበር በታሪክም በቅዱሳት መጻሕፍትም የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ ለዚህም በሐዲስ ኪዳን ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ለመግባቱ ምክንያት የሆነውና በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ከቍጥር 26 እስከ 40 የተጻፈው የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ታሪክ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ወደ ኢየሩሳሌም በሚያደርጉት ጒዞ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትስስርን ከማጠናከር ባሻገር በዴር ሡልጣን እና በብዙ መካናት ቋሚ ይዞታን በማቋቋም በርካታ ገዳማትንና አድባራትን መሥርተዋል፣ መንበረ ጵጵስናም አቋቁመዋል፡፡ ይህም ድርጊት ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም የሕዝቦቿ ምልክትና መመኪያ እድትሆን አድርጓታል፡፡ ይሁን እንጅ ነባሩን ታሪካዊ እውነት ለመሻርና በማይገባ ሁኔታ ግብጻውያን በሌላቸው መብትና ሕጋዊ ባልሆነ የፈጠራ መረጃ ኢትዮጵያን ከኢየሩሳሌም የዴር ሡልጣን ገዳም ባለቤትነቷን ለማሳጣት ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆዩም ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ሳይቀር መሥዋዕት በማድረግ ሃይማኖታቸውንና ጥንታዊ ገዳማቸውን ጠብቀው እስከ አሁን ቆይተዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን የኢየሩሳሌም ይዞታ ከቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃነት በተጨማሪ ኢየሩሳሌምን ይገዙ በነበሩ መሪዎች የግብርና የመንግሥት አዋጅ መዛግብት፣ ኢየሩሳሌም ድረስ ተጕዘው ታሪክ በጻፉ ምሁራን፣ በኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች የግል ማስታወሻ እና በዓለም ዐቀፍ መዛግብት ሳይቀር የተመዘገበ ሐቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም እንደነ አባ ጀሮም ያሉ የላቲን ታሪክ ጸሐፊዎች፣ እንደነ ከሊፋ ዑመርና ሳላሐዲን ባሉ ገዥዎች፣ በኢየሩሳሌም ተመሳሳይ ይዞታ ባላቸው በአርመንና በሶርያ ኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፣ በግሪክና በራሽያ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ ገዳማት መዛግብት የተመሰከረ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ግብጻውያን በሚፈጥሩት ግፍና ኢሰብኣዊ ድርጊት በይዞታችን ያለውን ገዳም ከጉዳት ለመጠበቅና ለማደስ አንኳ ሳንችል በመቅረታችን እየፈራረሰ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ቤተክርስቲያኒቱ ስታሰማ በነበረው ተደጋጋሚ አቤቱታና የኢትዮጵያ መንግሥት ባቀረበው ሕጋዊ የመብት ጥያቄ መሠረት የእስራኤል መንግሥት ገዳሙን ለማደስ ቃል በመግባቱ እና በዚሁ መሠረት መንግሥት ቃሉን በመጠበቅ በቅርቡ ጉዳት ከደረሰበት ከቅዱስ ሚካኤል ቤተመቅደስ እድሳቱ በመጀመሩ የተሰማንን ከፍተኛ ደስታ በቅድስት ቤተክርስቲያን እና በመላው ኢትዮጵያውያን ስም በመግለጽ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ የተጀመረው እድሳት በዴርሡልጣን የሚገኙ እና እጅግ በአስከፊ ጉዳት ላይ ያሉ ሁሉንም የኢትዮጵያ ይዞታዎች በማዳረስ ገዳሙ ጥንታዊ ይዞታውን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እንደሚደረግልን እናምናለን፡፡

አሁን እየተደረገ ያለውን ጥገና አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለእስራኤል መንግሥት ምስጋናችሁን እንድታቀርቡልን የግብጽ ቤተክርስቲያንን መሠረት የለሽ ክስና ሁከት በመቃወም ገዳማችሁን በመጠበቅ የበኩላችሁን እንድትወጡ፣ ወደ ፊትም ከግብጽ ያልተመለሱ ይዞታዎቻችንን ለማስመለስ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንድታደርጉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡

በዚሁ አጋጣሚ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት በይዞታችን ላይ አግባብነት የሌለው ሥራን የማደናቀፍና በታሪክም ሆነ በማንኛውም የሰነድ ማስረጃ መሠረት የሌለው የባለቤትንት ጥያቄ በማንሣት እየፈጠሩት ያለውን አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ እንዲያቆሙ፣ ዴርሡልጣን የኢትዮጵያ ገዳም ምንጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ የነበረና ወደፊትም የኢትዮጵያ ሆኖ የሚቆይ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሳችን፣ የኢትዮጵያውያን በኢየሩሳሌም ቅድስት ሀገር በሁሉም ዘመን በቋሚነት ለመገኘታቸው ምስክር ስለሆነ ከዚህ የተሳሳተ ትንኮሳና ሁከት እንዲታቀቡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም የተጀመረው የእድሳት ሥራ ተጠናክሮ በመቀጠል ሁሉንም የኢትዮጵያ የዴር ሡልጣን ይዞታዎች በአግባቡ እንዲጠገኑልን፣ በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የሰው ልጅ ቅርስ ጥበቃ ለሚያሳስባቸው በጎ አድራጊዎች ሁሉ ጥሪያችንን እያስተላለፍን እድሳቱ ያለምንም ዕንቅፋትና ሁከት ከፍጻሜ እንዲደርስ ጸሎታችንና ምኞታችን መሆኑን እናስታውቃለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፣ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

የመጀመሪያው የአንድነት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ

የጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ምልአተ ጉባኤ ለየት ያለ ነበር፡፡ ምንም እንኳ በአራተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ወደ ሀገራቸው መግባት ማግስት ሲኖዶሳዊ ትውውቅ የተደረገ ቢሆንም በዚህ ዓለም ዐቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የመጀመሪያው የአንድነት የሲኖዶስ ጉባኤ ተደርጓል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የምልአተ ጉባኤ መከፈትን አስመልክተው የሚከተለውን አባታዊ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላለፈዋል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ራብዓይ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣

ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ባለችው ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን፣ ሃይማኖታዊ አገልግሎታችንን እየባረከ ዘወትር ከእኛ የማይለይ እግዚአብሔር አምላካችን፣ አሁንም ለበለጠ ሐዋርያዊ ሥራ እንድንመካከር በስሙ ስለ ሰበሰበን ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡

በቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ በዓለም ዐቀፍ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ እንደሚታወቀው፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መሠረቱ ክርስቶሳዊ አስተምህሮ፣ሐዋርያዊ ትውፊትና ቀኖና ቅዱሳን አበው ነው፡፡

ክርስቶስ መድኀኒታችን “በስሜ በምትሰበሰቡበት እኔ በመካከላችሁ እኖራለሁ” ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶአል፤ ይህን ተከትሎም የመጀመሪያው ሲኖዶሳዊ ጉባኤ በቅዱሳን ሐዋርያትና በቀሲሳን ኅብረት በቅድስት ሀገር በኢየሩሳሌም ማእከላዊነት፣ በቅዱስ ያዕቆብ እኁሁ ለእግዚእነ ርእሰ መንበርነት፣ በዘመነ ሐዋርያት እንደተካሄደ “ወአንገለጉ ሐዋርያት ወቀሲሳን ከመ ይርአዩ ዘይገብሩ በእንተዝ ነገር፣ ሐዋርያትና ቀሳውስትም ስለዚህ ነገር ለመመካከር ተሰበሰቡ” ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ ተመዝግቦአል፡፡ የተወሰነው ውሳኔም መንፈስ ቅዱስ ያለበት መሆኑን ለማመልከት “እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅዶናል” ተብሎ ተገልጾአል፡፡ (የሐ.ሥራ 15፤6-29)፡፡

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ያጋጠሙ ፈተናዎችን ለማየት፣ ላለፈው እርማትና ማስተካከያን ለመስጠት፣ ለሚቀጥለው የሥራ አቅጣጫን ለማስቀመጥ፣ ተላውያነ ሐዋርያት በየጊዜው ሲኖዶሳዊ ጉባኤ ያካሂዱ እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ነው፤ በተለይም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዓለ ቅዱስ መስቀል በተከበረ በሃያ አምስተኛው ቀን ጥቅምት ዐሥራ ሁለትና የትንሣኤ በዓል በዋለ በሃያ አምስተኛው ቀን ርክበ ካህናት በድምሩ በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲካሄድ በቀኖና ቤተክርስቲያን መደንገጉ በፍትሕ መንፈሳዊ ተጽፎ ይገኛል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዋና ዓላማ ቤተ ክርስቲያን ከዐላውያን፣ ከአረማውያንና ከከሐድያን በየጊዜውና በየአቅጣጫው የሚሰነዘርባትን ጥቃት በሃይማኖት ጽናት ለመቋቋም፣ በድንበር፣ በወንዝ፣ በባሕር፣ በየብስ፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በፆታ፣ በቀለም፣ በሀብት፣ በሥልጣን፣ በዕውቀት፣ በጒልበት፣ ወ.ዘ.ተ ሳትገደብ መንግሥተ እግዚአብሔርን በዓለም ዙሪያ ሁሉ ለመስበክ፣ ለምእመናን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎትን ለማበርከት፣ በሰው ልጆች መካከል እኩልነት፣ሰብአዊነትና ፍትሕ እንዲሰፍን የበኩሏን አስተዋፅኦ ለማድረግ እንድትችል ነው፡፡

ሐዋርያዊት፣ ዓለም አቀፋዊት፣ አንዲትና ቅድስት የሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን የክርስቶስን አስተምህሮ፣ የቅዱሳን ሐዋርያትና የቀደምት ቅዱሳን አበውን ፈለግ ተከትላ፣ እነኝህን ዐላማዎች በመፈጸም ለሁለት ሺሕ ዘመናት ያህል ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ስታገለግል ኖራለች፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊውን የሐዋርያት ትውፊት፣ቀኖና እና ሥርዐት ጠብቃ በማስጠበቅ ያልተበረዘ፣ ያልተከለሰና ያልተሸራረፈ ሃይማኖታዊ አስተምህሮን በመከተል በዓለም ውስጥ የተዋጣላት ብቸኛዋ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ሁሉም የዓለም ክርስቲያኖችና ተመራማሪዎች ያረጋገጡት እውነት ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በምትከተለው ጥንቁቅ አስተምህሮና የማይናወጽ ጽንዐ ሃይማኖት ለሀገሪቱ አንድነትና ነፃነት፣ የግልዋ መለያ ለሆኑ ባህላዊ፣ ቍሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች መጠበቅ የአንበሳውን ድርሻ ወስዳ እስከ ዛሬ በድል ለመዝለቅ የቻለች ብቸኛ ኀያል እርስዋ እንደሆነች ማንም አይክደውም፤ ቤተ ክርስቲያናችን ይህ ጽናቷ በአፍሪካ ክፍለ ዓለምና በኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የቊጥር አንድ ደረጃን፣ በአጠቃላይ በኦርቶዶክሱ ዓለም ደግሞ በታሪክና በዶግማ ባይሆንም በቊጥር ብቻ ከሩስያ ቤተክርስቲያን ቀጥላ የቊጥር ሁለት ደረጃን ይዛ ትገኛለች፣ ይህ ጥንካሬና ጸጋ በቀደምት ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ የተገኘ ደማቅና አኵሪ ታሪክ መሆኑን ኦርቶዶክሳውያን ብቻ ሳይሆኑ መላ ኢትዮጵያውያን ሊያውቁት፣ ሊኰሩበት፣ ሊንከባከቡትና ሊጠቀሙበት የሚገባ የጋራ ሀብት ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በዚህ ሀብተ ጸጋ ሲጠቀሙ ኖረዋል፣ አሁንም እየተጠቀሙ ነውና፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምእመናንም ይህንን ሐቅ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የማሳወቅ ኀላፊነት ስላለባቸው በዚህ ዙሪያ በሰፊው ሊሠሩበት እንደሚገባ ሳንመክር አናልፍም፡፡

የዘንድሮ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ልዩ የሚያደርገው፣ ቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ ዕንቅፋት ሆኖ የቆየው የመለያየት ጠንቅ ተወግዶ፣ በምትኩ አንድነትዋ ገሃድ ሆኖ በምሕረተ እግዚአብሔር በተጐበኘችበት ወቅት ላይ የሚካሄድ ጉባኤ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ዕድል በመልካም ጎኑ የምንመለከተው ሆኖ፣ በተቃራኒው ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን በከፋ መልኩ የተደፈረችበት፣ ካህናቶቻችንና ምእመናን ልጆቻችን ለሰው ኅሊና በሚከብድ ድርጊት በአሠቃቂ ጭካኔ የሰማዕትነትን ጽዋ በተቀበሉበት ማግስት የሚካሄድ ጉባኤ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡

በመሆኑም ከዐሥር ዓመታት በፊት በጂማና በኢልባቦር አህጉረ ስብከት፣ በጉራጌና በአርሲ ነገሌ፣ በቅርቡም በባሌ ተቃጥቶ በነበረው አደገኛ ሙከራ፣ ከሁሉም የባሰ ደግሞ በኢትዮጵያ ሶማሌ ሀገረ ስብከት የተፈጸመው ጣራ የነካ ግፍና ጭካኔ፣ እልቂትና ውድመት ቤተ ክርስቲያናችንን ክፉኛ የጎዱና የተዳፈሩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ችግሩ ወደሌሎችም እንዳይስፋፋና የከፋ ጉዳትን እንዳያስከትል በከፍተኛ የኀላፊነት ስሜት ኀዘንዋን በልብዋ አምቃ ለማለፍ ብትሞክርም፣ ድፍረቱ ከቀን ቀን እየባሰ፣ ዕልቂቱም እየጨመረ፣ ተጽዕኖው እየተባባሰ በመሄዱ ልትታገሠው ከማትችልበት ደረጃ እየደረሰ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ በፊደልዋ ማዕድ ዕውቀትን እየመገበች፣ በታቦትዋ አዝማችነት ለነፃነትና ለወገን ክብር መተኪያ የሌለው መሥዋዕትነትን እየከፈለች፣ የሁሉም እምነቶች ነጻነት ሳትጋፋ፣ አንዱን ስንኳ ሳትጫንና ክብሩን ሳትነካ በሺሕ ለሚቈጠሩ ዘመናት እንዳልዘለቀች ሁሉ፣ ዛሬ በኢትዮጵያውያን ወገኖችዋ ስትቃጠል ማየት አሳፋሪና የድፍረት ድፍረት ነው፤ የቤተ ክርስቲያናችን ተከታይ ምእመናንና አገልጋይ ካህናት በነፃ የማስተማር፣ የማምለክና የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በሚቃረን አኳኋን በሚደርሳቸው ተጽዕኖ ከቀያቸው እየተፈናቀሉ እንዲወጡና ሃይማኖቱ እንዲዳከም የሚደረጉ ደባዎች እየተበራከቱ ነው፡፡

ይህ ሁሉ እየሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ለካህናትና ለምእመናን አስተማማኝ የሆነ መፍትሔ አበጅቶ ዘላቂ ዋስትና የማያረጋግጥ ከሆነ በታሪክና በእግዚአብሔር ዘንድ ተወቃሽ መሆኑ አይቀርም፤ በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ ይህ መሰሉ ችግር ተወግዶ ካህናትና ምእመናን ያለምንም ተጽዕኖና ሥጋት በነፃነት ሥርዐተ አምልኮአቸውን የሚፈጽሙበትና የመኖር መብታቸው የሚከበርበት ድባብ ለመፍጠር በየአካባቢው ጠንካራ የግንኙነት መረብ ዘርግቶ የቅድመ ትንበያ ሥራ በመሥራት፣ እንደዚሁም ከፍትሕና ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት፣በቤተ ክርስቲያንና በአማንያን የሚሰነዘረውን ጥቃትን አስቀድሞ ማምከን የሚቻልበትን አሠራር መቀየስ የግድ ይላል፡፡

ከዚህም ሌላ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደር ክፉኛ እያስተቸ የሚገኘው የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የሀብት አያያዝ ክፍተት፣ የምእመናን ፍልሰት፣ የተልእኮ ሐዋርያት አለመጠናከር፣ በውጭም በውስጥም ከቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውጭ በግላቸው አስተዳደራዊ መዋቅርን ከላይ እስከ ታች እየዘረጉ ቤተ ክርስቲያንን የሚጋፉ ልዩ ልዩ ማኅበራት፣ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት በሕግ፣ በመሪ ዕቅድ፣ በፖሊሲ፣ በደንብና በመመሪያ መልክን እያስያዙ የቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ክብርና መብት መጠበቅ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ሆኖ ይገኛል፡፡

ከዚህም ሌላ ያለንበት ወቅት ሀገራችን በብሩህ ተስፋና በሥጋት መንታ መንገድ ላይ የቆመችበት ጊዜ እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ በመሆኑም ሥጋቱ ተወግዶ ብሩህ ተስፋው ብቻ እንዲፈነጥቅ ቀጣዩ ዘመን ለሕዝባችን ወንድማማችነትና እኩልነት፣ለሀገር አንድነትና ለዜጎች ደኅንነት ያለዕረፍት ድምፃችንን ከፍ አድርገን የምንሰብክበት፣ከማንም የፖለቲካ ርእዮት ገለልተኛ በመሆን በአስታራቂነት ብቻ የምንቆምበት ጊዜ አሁን እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

እኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ካህናት፣ መምህራንና ሰባክያን የሁሉም ፖለቲከኞች አባቶች መሆናችንን ዐውቀን፣ ሁሉንም በአባትነት መንፈስ መመልከት፣ ማስተማርና መምከር እንጂ አንዱን አገልግሎ ሌላውን አቅርቦ ማየት ከሃይማኖት አስተምህሮ ጋር የማይሄድ ስለሆነ ልንጠነቀቅበት ይገባል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን አጠቃላይ አሠራር የዘመነና የሠለጠነ፣ ግልጽነትንና ተአማኒነትን ያሰፈነ፣ በልጆቻችን ምእመናን ዘንድ አድናቆትን፣ተቀባይነትንና ይሁንታን ያተረፈ እንዲሆን ለማድረግ ሁሉን የቤተ ክርስቲያን ሥራዎች ያካተተ፣ ጥልቅና ችግር ፈቺ የሆነ፣ ሰፊና ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል መሪ ዕቅድ የሚዘጋጅበት መደላድል መፍጠር አለብን፣ ይህም ጊዜ ሳይወስድ በፍጥነት ተሠርቶ ለቀጣዩ ስብሰባ እንዲቀርብ ዛሬ መወሰን ይኖርብናል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን የተዋጣለት መሪ ዕቅድ ሲኖራት፣ በእርግጠኝነት ሁሉንም ችግሮች ተቋቁመን የተሻለ ልማትና እድገትን በሁሉም አቅጣጫ እናስመዘግባለን፣ የምንጓዝበት ፍኖተ ምሕዋርና የምንደርስበት ጫፍም በትክክል ማወቅ እንችላለን፤ ፈጣን የሆነ ሐዋርያዊ፣ መንፈሳዊ፣ አስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትንም እናስመዘግባለን፤ ስለሆነም የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ ችግርን መፍታት የምንችለው በመሪ ዕቅድ በመመራትና መልካም አስተዳደርን በማበልፀግ እንደሆነ፣ ከዚህ ውጭ ግን ሌላ አማራጭ ሊኖር እንደማይችል መገንዘብ ይኖርብናል፤ ሌላው በዚህ ጉባኤ ሳናነሣው የማናልፍ ዐቢይ ነጥብ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ነው፤ የታሪክ አጋጣሚና የትውልድ ዕድል ጉዳይ ሆኖ አሁን ላለንበት ሁኔታ ብንዳረግም ከኢትዮጵያ የተነጠለ የኤርትራ ታሪክ፣ ከኤርትራ የተነጠለ የኢትዮጵያ ታሪክ ፍጹም እንደሌለ እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም በሙሉ የሚያውቀው ሐቅ ነው፡፡

ከጅምሩም ግራና ቀኛችን በሚገባ አርቀን ካለማየታችን የተነሣ ለጊዜው ተለያይተን ቆየን እንጂ የሚለያየን ሃይማኖታዊም ሆነ ቀኖናዊ ምክንያት የለንም፤ ምድራዊ መንግሥት በፖለቲካ ምክንያት ቢለይም እንኳ፣ ለሃይማኖት ድንበር ስለሌለው በአንድነት እየተደጋገፍን መቀጠል ይገባን ነበር፡፡ ይህ እውነታ ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያኑ ባያድለንም፣ ሌሎች መሰል አብያተ ክርስቲያናት ግን እስካሁን ጠብቀውት እንዳለ ማየት እንችላለን፤ ነገር ግን “ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራም” እንደሚባለው ያለፈውን ለታሪክ ትተን፣ ለወደፊቱ ተጋግዘን፣ ተረዳድተንና ተደጋግፈን፣ የጋራችን የሆነ ሃይማኖትን፣ ታሪክና ባህልን ጠብቀን በማስጠበቅ ኦርቶዶክሳዊውን ሕዝብ ማገልገል እግዚአብሔርና ታሪክ የጣሉብን አደራ መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡

እውነቱን ለመናገር ለኢትዮጵያ ምእመናን ከኤርትራ ምእመናን፣ ለኤርትራ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የበለጠ የክፉ ቀን ደራሽ የላቸውም ፣በመሆኑም በሁሉም ሃይማኖታዊ የሥራ መስክ ተቀራርቦ ለመሥራት ቅዱስ ሲኖዶስ ዝግጁነቱን መግለጽ ይኖርበታል፤ በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖር የጋራ ኮሚሽን አቋቁመን መንቀሳቀስም ይገባናል፡፡

በመጨረሻም፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱትን አንገብጋቢ የአገርና የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን አንድ በአንድ ተመልክቶና በጥልቀት መርምሮ አገራችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን ያሳልፍ ዘንድ፣ እንደዚሁም የቤተ ክርስቲያናችን የቀደመው ክብርና ሞገስን፣ ሉዐላዊነትና አንድነትን ጠብቆ ያስጠብቅ ዘንድ ከማሳሰብ ጋር የጥቅምቱን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎት መከፈቱን በእግዚአብሔር ስም እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ጉባኤያችንን ይባርክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿንም ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

37ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በአጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ ዓለም ዐቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለመሳተፍ በዚህ ስፍራ የተገኛችሁ ክቡራንና ክቡራት፤ የቤተ ክርስርቲያን አንድነትን በቅዱስ መንፈሱ ኀይል ዘወትር የሚጠብቅ እግዚአብሔር አምላካችን አንድነታችንን መልሶ፣ ወንድማማችነታችንን፣ ፍቅራችንንና ሰላማችንን አድሶ ለዚህ ታሪካዊና ዓመታዊ ዓለም ዐቀፍ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሰላም ስላደረሰን ክብርና ምስጋና ለእርሱ እናቀርባለን፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ተቀብላችሁ በዚህ ጉባኤ ለመገኘት ከቅርብም ከሩቅም፣ ከውስጥም ከውጭም ለመጣችሁና የእግዚአብሔር ሠራዊት ለሆናችሁ ለእናንተም እንኳን በደኅና መጣችሁ እንላለን፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፣

ሐዋርያዊት፣ዓለም አቀፋዊት፣ አንዲትና ቅድስት የሆነች ቤተ ክርስቲያናችን በቅዱስ ባኮስ ኅጽዋ ለሕንደኬ ንግሥተ ኢትዮጵያ አማካኝነት እንደተመሠረተች ቅዱስ መጽሐፍና የታሪክ መጻሕፍተ አበው የመሰከሩት እውነት ነው፡፡ ከዚህም በኋላ በቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዘኵሎን አድያማተ ኢትዮጵያ ትጋት፣ በቅዱሳን ነገሥት አብርሀ ወአጽብሐ አደራጅነት፣ በሀገረ ስብከት ደረጃ ተቋቁማ የተሟላ ሐዋርያዊ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለመላው ሕዝበ ኢትዮጵያ ስታበረክት ኖራለች፡፡ቅዱሳን ነገሥት አብርሀ ወአጽብሐ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ከመሆናቸውም ባሻገር የቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲቃና ድጋፍ ሰጭ ብቻ ሳይሆኑ ከሊቀ ጳጳሱ ጋር እንደ አንድ ሐዋርያ ሆነው ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን ሁሉ አስተምረው፣አሳምነውና አጥምቀው የሥላሴ ልጅነትን እንዳጎናጸፉት፣ ትዕይንተ ደብተራ ዘአክሱም፣ ባሕረ ጣና ዘጎንደር ፣ መርጡለ ማርያም ዘጎጃም፣ ተድባበ ማርያም ዘወሎ፣ ጎሐ ጽዮን ዘሸዋ፣ በሓ ጊዮርጊስ ዘከፋ የዐይን ምስክሮች ናቸው፡፡

ቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃንና ቅዱሳን ነገሥት አብርሀ ወአጽብሐ ሃይማኖተ ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን በአዋጅ ከማጽናታቸውም ሌላ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ለካህናት መተዳደሪያ የሚሆን መሬት በበቂ ሁኔታ እንዲሰጥ በማድረጋቸው ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ሥርዐተ ምግብና እስከ 1969 ዓ.ም. ስትተዳደር ኖራለች፡፡ አበው “መሰላል ሳይፈጥር ገደል አይፈጥርም” እንደሚሉት እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን ፊት ለፊት ከተጋረጠባት ፈተና ለመታደግ ሲል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ላይ ቅዱስ መንፈስን አሳደረ፤ ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያን በመሬት ሥሪት የመተዳደር ዕድሏ ቀጣይ እንደማይሆን፣ የተደቀነው ፈተናም ለቤተ ክርስቲያን አሥጊ መሆኑን እንዲገነዘቡና መፍትሔ እንዲያበጁ እግዚአብሔር ስላመለከታቸው ቤተ ክርስቲያን እንደ ጥንቱ እንደ ዘመነ ሐዋርያት በልበ ምእመናን ተጠልላ በእደ ምእመናን እንድትመገብ የሚያስችል አሠራርን ቀየሱ፡፡

እግዚአብሔርም ሩቅና ዘላቂ ሕልማቸውን ባርኮላቸው ቤተ ክርስቲያን በልበ ምእመናን ተጠልላ በእደ ምእመናን እንድትመገብ የሚያስችል የቃለ ዐዋዲ መተዳደሪያ ደምብን በቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቀው፣ በፍትሐ ብሔር ዕውቅና አሰጥተው ለቤተ ክርስቲያን የህልውና ማስቀጠያ ዋስትና አስረክበው በሰማዕትነት አልፈዋል፤

ካህናትን፣ ምእመናንና ወጣቶችን በአንድነት አደራጅቶ፣ በሐብለ ሃይማኖት ባስተሳሰረው በቃለ ዐዋዲ ደምብ የምትመራው ቤተ ክርስቲያናችን ይህ መሰሉን ዓለም አቀፋዊ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስታካሄድ እነሆ ዛሬ ሠላሳ ሰባተኛው ጉባኤ ላይ ደርሳለች፡፡ በመሆኑም፣ ይህ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያንን አጠቃላይ የሥራ ክንዋኔ የምንመዝንበት፣ ባለፈው ዓመት ያጋጠሙንን ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ፈተናዎችን የምንገመግምበት፣ በአንጻሩ ደግሞ ባለፉት ዓመታት የተከሠቱ ፈተናዎች በቤተ ክርስቲያንና በሕዝበ ክርስቲያን ላይ ዳግም እንዳይከሠቱ መብታችንንና ክብራችንን ለማስጠበቅ በቊርጠኝነት ለመሥራት የምንነሣበት፣ ክፍተት የሚታይባቸውን የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የሀብት አያያዝ ብክነት፣ የምእመናን ፍልሰት፣ በውጭ የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት ውሕደት፣ የሀገር ሰላምና አንድነት፣ የዜጎችን ደኅንነት አንሥቶ በስፋትና በጥልቀት ይወያይባቸዋል፤ የጋራ አቋምም ይወስድባቸዋል የሚል ጽኑ እምነት አለን፡፡ መቼም ሁላችንም እንደምንገነዘበው የጉባኤ አስፈላጊነት፣ በሥራ ሂደት የተከሠተውን ደግም ይሁን መጥፎ ገጠመኝ በጋራ ለማየትና ለመመዘን፣ ከዚያም ካለፈው ልምድና ተሞክሮ ግንዛቤ በመውሰድ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ ግምታዊ ተነብዮን አስቀምጦ ለወደፊት የተሻለ የቅድመ መከላከያና ማስተካከያ አሠራር ለመዘርጋት ነው፡፡

የሰበካ ጉባኤ የጀርባ አጥንት በሆነው የቃለ ዐዋዲ ደንብ የተገኘው የሰበካ ጉባኤ ለውጥ ቀላል ባይሆንም በደምቡ መሠረት በምልአት ቢሠራበት ኖሮ ማለትም በዘመነ የሰው ኀይል አስተዳደር፣ በሠለጠነ የሀብት አያያዝ፣ እንዲሁም በጠነከረ አሓዳዊ መዋቅር ቢታጀብ ኖሮ አሁን ካለው የበለጠ እድገት ማስመዝገብ ይቻል እንደነበር በግልጽ ይታያል፡፡ ከስድሳ ሚሊዮን ያላነሰ የምእመናን ብዛት ይዛ፣ በቢሊዮን ብር የሚገመት የመሬት ይዞታ ጨብጣ፣ ብዙ ትርፍ ሊያስገኙ የሚችሉ የንዋየ ቅድሳት ምርቶችን ተጠቃሚ ሆና፣ በቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ ልትጠቀምባቸው የሚችሉ ኁልቈ መስፈርት የሌላቸው ቅርሶችን በጉያዋ ታቅፋ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያናችን ድሀ ናት ብለን መናገር እንዴት እንችላለን? ይህ ሁሉ ሀብት ያላት ቤተ ክርስቲያንን ምንም እንደሌላት ቈጥረን የአብነት ት/ቤቶች ሲዳከሙ፣ ገዳማት ሲዘጉ ዝም ብለን ማየትስ ኀጢአት አይደለምን?

የሠላሳ ሰባተኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤን ልዩ የሚያደርገው ቤተ ክርስቲያናችን ብዙ አስደሳችም አሳዛኝም ድርጊቶች ባስተናገደችበት ማግስት የሚካሄድ መሆኑ ነው፡፡ ከመልካም አጋጣሚዎች መካከል ለብዙ ዓመታት ተለይተውን በባዕድ ሀገር የቆዩት አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘአትዮጵያ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ወደ ሀገራቸው ገብተው የቤተ ክርስቲያን አንድነት ወደነበረበት መመለሱ ነው፤ እንደዚሁም የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታትና ሕዝብ ወደ ሰላምና ዕርቅ ተሸጋግረው፣ ወንድማማችነታቸውን አጽንተው፣ የጥል ግድግዳን አፍርሰው፣ በፍቅር ተሳስረው ለመኖር መስማማታቸው ከመልካም አጋጣዊዎች መካከል የሚጠቀሱት ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ዓመታዊው ጉባኤያችን ካለፉት 3 ዓመታት በፊት ጀምሮ እየባሰበት የመጣ ግጭት ቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ምእመናን ልጆችዋ ከቀያቸው የተፈናቀሉበት፣ የቆሰሉበት፣ የተጎዱበትና የሞቱበት፣ በተለይም በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎችና በርካታ ዞኖች የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ከነ ሙሉ ንብረታቸው የተቃጠሉበት፣ ካህናትና ምእመናን በሚዘገንን የጭካኔ ተግባር የተገደሉበት አሳዛኝ ድርጊት በተፈጸመበት ማግስት የሚካሄድ በመሆኑ በደጉም በክፉም ገጽታው እናስታውሰዋለን፤ ይሁንና ሁሌም እንደሚባለው ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራምና፥ እንደዚህ ዐይነቱ ድርጊት እየተለመደ እንዳይሄድ ቤተ ክርስቲያን ልዩ የግንኙነት መረብ ወይም የኮሙዩኒኬሽን ሲስተም ዘርግታ የአምልኮ ቦታዋንና የምእመናን ልጆችዋን ደኅንነት በቅርበት በመከታተል ኀላፊነትዋን መወጣት ይኖርባታል፡፡ ይህ ምልዓተ ጉባኤም በመላ ሀገራችን ጸሎት እንዲታወጅ ውሳኔ ማሳለፍ አለብን፤ ቤተ ክርስቲያናችን ከሆነ በኋላ ማልቀስና በዐሥር ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አውጥታ መደጎም ሳይሆን፣ በዐሥር ሚሊዮን ብር የግንኙነት መረብ ዘርግታ ችግር ከመፈጠሩ በፊት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ በመሥራትና ከመንግሥት የጸጥታ ኀይል ጋር ተቀናጅታ አደጋዎችን አስቀድማ መከላከል አለባት፤ በዚህ ዙሪያ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤም ጠንካራና ትክክለኛ ውሳኔ በመወሰን አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚህም ሌላ ባለፉት ዓመታት በነበረው የአባቶች መለያየት ምክንያት አንዱ የውጭ ሲኖዶስ፣ ሌላው የሀገር ውስጥ ሲኖዶስ፣ ሌላው ደግሞ ገለልተኛ በሚል ስያሜ ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችን አንድነትዋን አጥታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አስዳደርዋን በአግባቡ ለማከናወን ብዙ እክል እያጋጠማት እንደቆየ የሚዘነጋ አይደለም፤ አሁን ግን በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በመንግሥታችን ድጋፍ ፣ በሕዝበ ክርስቲያኑ ጸሎት የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት የተረጋገጠ በመሆኑ ከቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ አስተዳደር ውጪ ሆኖ መኖር ክርስቶስ ደሙን አፍስሶ በመሠረታት ቤተ ክርስቲያን ላይ መዘበት ነው የሚሆነው፤ ከሁሉም በላይ በመላው ዓለም ላይ የሚገኙ ካህናትና ምእመናን፣ እናቶችና አባቶች ወጣቶች በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ መሠረት በፍትሕ መንፈሳዊ እንደተደነገገው ቅዱስ ሲኖዶስ በመደበው ሊቀ ጳጳስ በሚተዳደር ሀገረ ስብከት ሥር ታቅፋ የማትመራ ቤተ ክርስቲያን፣ እንደዚሁም በሊቀ ጳጳስ አስተዳደር ሥር ባለች ቤተ ክርስቲያን ያልታቀፈ ማንኛውም ካህን ይሁን ምእመን፣ ምእመናት ሴቶች ይሁኑ ወጣቶች ኦርዶክሳዊ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን እየጣሱ እንደሆነ ሊያውቁና ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ በመሆኑም ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም በየአካባቢያቸው ባለው ሀገረ ስብከት እየታቀፉ በሊቀ ጳጳሱ ሥር በመሆን ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁ ለቤተ ክርስቲያናቸው መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲያበረክቱ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም፡ ይህ ዐቢይ ጉባኤ በሐዋርያዊ ተልእኮ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በቤተ ክርስቲያን ሀብት አጠባበቅ፣ በቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ ውሕደት፣ በሀራዊ ሰላምና አንድነት፣ በቤተ ክርስቲያን ቀጣይ ልማትና እድገት፣ እንደዚሁም በቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊ ህልውና፣ በመብቷና በክብሯ መጠበቅ ላይ አጥብቆ በመወያየት ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ ውሳኔ እንዲያሳልፍ፣ ከዚህም ጋር ለተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትና ለተጎዱ ምእመናን ድጋፍ እንዲደረግላቸው በሰፊው እንዲመክር በማሳሰብ ሠላሳ ሰባተኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተከፈተ መሆኑን በእግዚአብሔር ስም እናበሥራለን፡፡ እግዚአብሔር ጉባኤውን የተባረከና የተቀደሰ ያድርግልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡