ነሐሴ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ በዓለ ዕርገት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በመላው ዓለምና በሀገር ውስጥ ሆናችሁ፣ በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቅድስት ድንግል ማርያም ተስባችሁ፣ የጾመ ፍልሰታ ለማርያምን በጾም ፣ በጸሎት፣ በምጽዋት፣ በአምልኮና ቅዱስ ቊርባንን በመቀበል ያሳለፋችሁ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት በሙሉ፡፡

በቅዱስ አጠራሩ ወደ እርሱ ያቀረበን፣ ከቅዱሳን ጋር ሰማያዊ ርስቱን እንድንካፈል ያደረገ፣ ሰውን የሚወድ፣ መሓሪውና ይቅር ባዩ አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ ፍልሰታ ለቅድስት ድንግል ማርያም በሰላም አደረሳችሁ!!

“እስመ ኅሉቀ ወምቱረ ነገር ይነግር እግዚአብሔር ውስተ ዓለም ዘሀለዎ ይግበር
እግዚአብሔር በዓለም ውስጥ ያደርገው ዘንድ ያለውን ያለቀና የተቈረጠ ነገርን ይናገራል።”
(ሮሜ 9÷28)፡፡

ይህንን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የትምህርተ ወንጌል መርሐ ግብር በመከታተል የምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፣ በዛሬው ትምህርታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ነገረ ትንሣኤ እንማራለን፤ በዚህ መነሻነትም እግዚአብሔር ከሞት በኋላ ስላለው አጠቃላይ ዘለዓለማዊ ሕይወት የገለጸልንን እንሰማለን፡፡ በተለይም የእኛ የሰው ልጆች ትልቁና የመጨረሻው ተስፋችን ትንሣኤ ሙታን ስለሆነ በዚህ ዙሪያ እግዚአብሔር በተግባርና በትምህርት የገለጸልንን እንመለከታለን፤ ስለሆነም ቃሉን ሰምተን እንድናስተውልና ለእርሱ ታዛዥ ሆነን በቃሉ እንድንኖር እግዚአብሔር ዐይነ ልቡናችንን ያብራልን፡፡

የትምህርታችን ርእስ፦ “እስመ ኅሉቀ ወምቱረ ነገረ ይነግር እግዚአብሔር ማለትም እግዚአብሔር ያደርገው ዘንድ ያለውን ያለቀና የተቈረጠ ነገርን ይናገራልና” የሚል ነው ፡፡

በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ እንደተጻፈው የሙታን መነሣትን በተመለከተ እግዚአብሔር ያለቀና የተቈረጠ ጉዳይ እንደሆነ በብዙ ቦታ በማያሻማ መልኩ አሳውቆናል፡፡ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር የሚያደርገውን ሥራ ለወዳጆቹ ለነቢያት ሳይገልጽ የሠራበት ጊዜ የለም፣ ሲናገርም ግልጽና የማያሻማ አድርጎ በቊርጥ እንደሚያሳውቅ የርእሳችን ኀይለ ቃል ያሳያል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በነቢዩ በአሞጽ አድሮ እንደገለጸው “እስመ አልቦ ዘይገብር እግዚአብሔር ዘኢተናገረ ወዘኢከሠተ ለአግብርቲሁ ነቢያት፤ በእውነት ጌታ እግዚአብሔር (ምሥጢሩን) ለባሪያዎቹ ለነቢያት ያልገለጸውናን ያልተናገረውን ምንም አያደርግም” ብሏል (አሞ. 3÷7)። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ለወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን ሥራ ለወዳጆቹ ሳይገልጽ እንደማይሠራ ያስገነዝባሉ።

እኛም ኅሊናችንን እና መንፈስ ቅዱስን አስተማሪ፣ መሪ አድርገን ነገሩን ስናጤነው ትክክለኛ መሆኑን ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኖ አይታይም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሥራዎቹን ሁሉ ከመሆናቸው በፊት ለነቢያቱ እየገለጸ እንደሠራ፣ ለነቢያቱ ከገለጸውም አንዳች ስንኳ ሳያስቀር እንደፈጸመ በብዙ ቦታ ተጽፎ እናገኘዋለንና ነው፤ ይኸውም እውነት እንደሆነ በቅዱስ መጽሐፍ፣ በታሪክ ፍጻሜ፣ በሥነ ምድር ጥናት ሳይቀር የተረጋገጠና በየጊዜው እየተረጋገጠ ያለ ሐቀ ነው፡፡ እግዚአብሔር ካሁን በፊት ተናግሮ ሳይፈጽመው የቀረ ነገር እንደሌለ፣ ለወደፊትም ከተናገረው ውስጥ የሚቀር ነገር እንደሌለ መገንዘብ ከእኛ ከፍጡራኑ ይጠበቃል፡፡

እግዚአብሔር ግልጽ አድርጎና በማያወላውል ሁኔታ ከተናገረው ውሰጥ ያልተፈጸመው አንዱና ዋነኛው የትንሣኤ ሙታን ነገር ነው፤ ይህም ቢሆን ፍጻሜው ስላልደረሰ ጊዜውን እየጠበቀ ያለ ጉዳይ እንጂ የሚቀር ሆኖ አይደለም፤ ከዚህ አኳያ እግዚአብሔር ስለ ትንሣኤ ሙታንና ስለቀጣዩ ለዘለዓለማዊ ሕይወት በትምህርትም፣ በቃልም፣ በተግባርም አስተምሮአል አሳይቶአልም፡፡ በእግዚአብሔር ቊጣ አጠገብ ምሕረቱም አይለይምና ሰዎችን ከኀጢአታቸው የተነሣ ተቈጥቶ ከገነት ካስወጣ በኋላ ፍጡራን የአቤልን መሞት በተረዱበት ማግስት ሄኖክን ሳይሞት እንዳለ ከነሥጋው ወደ ሕይወታዊ ዓለም መውሰዱ ሞት ብቻ ሳይሆን ከሞት በኋላም ሕይወት እንዳለ እግዚአብሔር ለሰዎች የተናገረበት ክሥተት ነበረ፤ ሰዎች ይህንን የሄኖክን አለመሞት አይተው በተስፋ መሞላታቸውን ሲያመለክት ከአበው አንዱ “በአቤል አፍርሆሙ ወበሄኖክ አንቅሆሙ ማለትም በአቤል መሞት አስደነገጣቸው ወይም አስፈራቸው፤ በሄኖክ አለመሞት ደግሞ አነቃቃቸው ” ሲል ተናግሮአል፡፡

በይቀጥላልም እነ ኤልያስ፣ እነ ዕዝራ ሳይሞቱ እንዳሉ ወደ ሕያዋን ዓለም ሲወሰዱ፣ እንደዚሁም እግዚአብሔር ለአርእስተ አበው የገባው ዘለዓለማዊና የሕይወት ቃል ኪዳን ጥልቅና እስከ ወዲያኛው ዓለም ድረስ የሚዘልቅ መሆኑን ግልጽ እየሆነ ሲመጣ፣ ከዚህም ጋር ነቢዩ ኤልያስ አንድ ምዉትን ሲያስነሣ፣ የእርሱ ደቀ መዝሙር የነበረ ኤልሳዕም በአጥንቱ ንክኪነት ሳይቀር ሁለት ሙታንን ሲያስነሣ፣ ነቢዩ ዳንኤልም “በምድር ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎቹ ይነቃሉ” ብሎ ሲናገር የትንሣኤ ሙታን ነገር ያለቀና የደቀቀ መሆኑ ታወቀ፤ ነቢዩ ኢሳይያስም “ሙታን ይትነሥኡ ወየሐይዉ እለ ውስተ መቃብር፤ ሙታን ይነሣሉ በመቃብር ያሉትም ይድናሉ በሕይወትም ይኖራሉ” ሲል የሙታን ትንሣኤን አይቀሬነት አስረድቶአል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ እግዚአብሔር ወልድ ሥጋችንን ለብሶ በዚህ ዓለም በተገለጠ ጊዜ ወልደ መበለትን፣ ወለተ ኢያኢሮስን፣ አልዓዛርን፣ አምስት መቶ ቢጽን ከሞት ከማስነሣቱም ሌላ ስለ ትንሣኤ ሙታን በሰፊው ማስተማሩን፣ ከዚህም ሌላ በትንሣኤ ሙታን እምነት ያልነበራቸው ሰዱቃውያን የተባሉ የአይሁድ ክፍሎች ስለ ትንሣኤ ሙታን ጉዳይ መስቀለኛ ጥያቄን ባቀረቡለት ጊዜ የእግዚአብሔር ኀይልና የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል ባለማወቅ ስሕተት ላይ መውደቃቸውን ገልጾ ሙታን እንደሚነሡ፣ ሰማያዊ ሕይወታቸውም እንደ መላእክት እንደሚሆን አስረግጦ ነግሮአቸዋል፡፡ በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ነገረ ትንሣኤ ሙታንን በማያወላውልና በማያሻማ ሁኔታ ለዓለም በቊርጥ ተናግሮአል፡፡

የተወደዳችሁ ልጆቻችን ሕዝበ ክርስቲያን፤

በየዓመቱ በጾም፣ በጸሎት፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር፣ በቅዳሴ፣ በውዳሴና፣ ቅዱስ ቊርባንን በመቀበል የምናከብረው የቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ፍልሰታ ወይም በዓለ ትንሣኤ ከዚህ በላይ ከተገለጸው ነገረ ትንሣኤ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ዓለም ለስድሳ አራት ዓመታት ያህል በሕይወተ ሥጋ ከቆየች በኋላ ጥር ሃያ አንድ ቀን ጽርሐ ጽዮን ውስጥ በሚገኘው በባለ አደራው በዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ቤት ዐርፋለች፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ነፍስ በእደ እግዚአብሔር ፣ በይባቤ መላእክት፣ ወደ ብርሃናዊውና ሰማያዊው ዓለም ስትወሰድ፣ ሥጋዋ ደግሞ ጌቴሴማኒ ውስጥ በሚገኘው በወላጆቿ መቃብር ለማሳረፍ ቅዱሳን ሐዋርያት ሥጋዋን ተሸክመው ጒዞ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን የክርስትናውን እምነትና አስተምህሮ ያልተዋጠላቸው የአይሁድ ወገኖች ሥርዐተ ቀብሯ በሰላም እንዳይፈጸም ከመዶለታቸውም ሌላ ቅዱስ የሆነው ሥጋዋን ከሐዋርያት እጅ ለመንጠቅና ለመውሰድ ሞከሩ፡፡

ይህንን ሙከራ ያደረገ ታውፋንያ የሚባል ሰው ነበረና መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እሱን ቀጥቶ ቅዱሱን የእመቤታችን ሥጋን ከባለ አደራው ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ነጥቆ ወደ ገነት ወሰደው፤ በዚህ ሁኔታ የቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ በዚያ እንዲቀመጥ ሆነ፤ ቅዱስ ዮሐንስ ግን ወደ ወንድሞቹ ወደ ሐዋርያት ተመልሶ የድንግል ማርያምን ቅዱስ ሥጋ በገነት ውስጥ በዕፀ ሕይወት ሥር መቀመጡን ለሐዋርያት ነገረ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ወኵሎ ዘሰአልክሙ በስምየ ይትገበር ለክሙ፤ በስሜ የምትለምኑት ሁሉ ይደረግላቸኋል” ብሎ የገባላቸውን ቃል ኪዳን በመከተል የቅድስት ድንግል ማርያም አስከሬን ያለበትን ቦታ ማየትና ቅዱሱ ሥጋዋን መሳለም እንዲችሉ ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ዐሥራ አራት በጾምና በጸሎት ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን ደጅ ጸኑ፡፡ጌታችንም እንደ ቃሉ ጸሎታቸውንና ጾማቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ዐሥራ አራት ቀን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥጋን አምጥቶ ሰጣቸው፤ እነሱም ሥጋዋን ተቀብለው በታላቅ ክብር በጌቴሴማኒ ውስጥ በወላጆችዋ ርስት ቀበሩአት፡፡

ከዚህ በኋላ የእመቤታችን ሥጋን በተቀበረ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን ጌታችን ነፍሷን ከሥጋዋ ጋር አዋሕዶ በማስነሣት ወደ ብርሃናዊው ዓለም ወደ መንግሥተ ሰማያት አሳርጎአታል፡፡ በዕርገቷ ጊዜ በሕንድ ሀገር ቅዱስ ወንጌልን እያስተማረ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በደመና ሰማይ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ፣ እመቤታችን በሰማያውያን ሠራዊት ታጅባ በመላእክት ዝማሬና በቅዱሳን ይባቤ ስታርግ አገኛት፡፡ቅዱስ ቶማስ ከነበረው የድንግል ማርያም ጽኑ ፍቅር የተነሣ በቁጭት በትንሣኤሽ ቀን ሳልገኝ ቀረሁን! ብሎ ሲያዝን፣ አይዞህ ወዳጄ ቶማስ ወንድሞችህ ሐዋርያትም በክብር ገንዘው ቀበሩኝ እንጂ ትንሣኤዬን አላዩም፤ አንተ ብቻ ነህ ትንሣኤዬን ያየህ፤ ስለዚህ እኔን የገነዙበት ሰበን (መጐናጸፊያ) ለሁላችሁም ለበረከት እንዲሆናችሁ ይኸው ሰጥቻችኋለሁ ብላ በመስጠትና በማጽናናት ትንሣኤዋን ለሐዋርያት እንዲያበሥር ነግራው ዐረገች፡፡ ቅዱስ ቶማስም የተሰጠውን ሰበን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ከሐዋርያት ጋር ተገናኘ፤ ሐዋርያትም በበኩላቸው ጌታ የእመቤታችንን ሥጋዋን እንደሰጣቸውና በክብር ገንዘው እንደቀበሯት ነገሩት፤ ቅዱስ ቶማስ ግን በያዘው ሰበን ትንሣኤዋን ለመግለጽ ስለፈለገ “ሞት በጥር፣ በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” ብሎ ተከራከራቸው፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ነገሩ እውነት እንደሆነ ለመግለጽና እርሱን ለማሳመን ሲል መቃብሯን ቈፈረ፤ ሆኖም ሥጋዋን አላገኘም፤ ቅዱስ ጴጥሮስና ሐዋርያት በሁኔታው ደነገጡ፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ እኔ ብቻ ከምነግራችሁ እናንተም ራሳችሁ አይታችሁ እንድታምኑ ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንማ ተነሥታ አርጋለች፤ እርሷን የገነዛችሁበት ሰበንም ለወንድሞቼ ለሐዋርያት ለበረከት እንዲሆናቸው ስጣቸው ብላኝ ይኸው ይዤ መጥቻለሁ ብሎ አሳያቸው፤ እነሱም ነገረ ትንሣኤዋን በመስማታቸው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ የተገነዘችበትን ሰበን ተካፈሉት፡፡

ዛሬ በምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናትና በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ከመስቀል ጋር የሚያዘው ሰበን የእመቤታችን ትንሣኤ መታሰቢያ እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ለቶማስ የተገለጸውን ነገረ ትንሣኤዋ ለእነርሱም እንዲገለጸላቸው በመሻት በድጋሚ በዓመቱ ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ጾምና ጸሎት ያዙ ሱባዔም ገቡ፤ አሁንም ጌታችን ጸሎታቸውንና ጾማቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ዐሥራ አምስት ቀን ሐዋርያትን ከያሉበት ሀገረ ሰብከት በደመና ሰማይ ሰበሰባቸው፤ በበነጋው ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን ጌታችን እመቤታችንን፣ ቅዱሳን መላእክትን፣ ከአዳም ጀምሮ እስከዚያው ያሉትን ቅዱሳን ሁሉ አስከትሎ ተገለጠላቸው፣ ጸሎተ ቅዳሴን አድርሶ ቅዱስ ቊርባንን አቀበላቸው፤ በዚህ ሁኔታ ትንሣኤዋን ከገለጸላቸው በኋላ ይህንን ትንሣኤዋን እንዲያስተምሩ አዘዛቸው፤ ለእርሷም ሐዋርያት ለፍቅሯ ሲሉ በጾሙት በጾመ ፍልሰታ ጾምን የጾመ፣ ቅዱስ ቊርባንን የተቀበለ፣ የተራበውን ያበላ፣ የተጠማውን ያጠጣ፣ የታረዘውን ያለበሰ እምርልሻለሁ ብሎ ቃል ኪዳን በመግባት በመጣበት አኳኋን ወደ ሰማያት አርጓል፡፡

ጌታችንም ሆነ ሐዋርያት የሠሩትን ተኣምራትና ምግባር ትሩፋት እንደዚሁም ያስተማሩትን ትምህርት ሙሉ በሙሉ በጽሑፍ እንዳልሰፈረ በቅዱስ መጽሐፍ የተረጋገጠና በዮሐ ፳፩÷፳5 ተጽፎ የምናገኘው ሐቅ ነው፡፡ በመሆኑም ቅዱሳን ሐዋርያት በመልእክታቸው ውስጥ በጽሑፍ የሰፈረውን ብቻ ሳይሆን በትውፊትና በቃላቸው ያስተላለፉትንም ጭምር አጥብቀን እንድንይዝ “ወንድሞች ሆይ ጸንታችሁ ቁሙ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ሁሉ ወግ (ትምህርት) ያዙ” ብለው አስተምረውናል፤( ፪ ተሰ ፪.፲5) ቅዱሳን ሐዋርያት በቃል ካስተማሩት ውስጥ አንዱ ፍልሰታ እያልን የምንጠራው የቅድስት ድንግል ማርያም ነገረ ትንሣኤ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከዕርገተ ክርስቶስ በኋላ በአንደኛው ዓመት፣ ከልደተ ክርስቶስ ደግሞ በሠላሳ አራተኛው ዓመት ማለትም ሁሉም ሐዋርያት በሕይወተ ሥጋ እያሉ የክርስትና ሃይማኖትን የተቀበለች በመሆኗ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ትባላለች፤ ይህም ማለት በትውፊትም ሆነ በቃላዊ ትምህርት ከተላለፈው ከሐዋርያት አስተምህሮ ያመለጣት ምንም ነገር እንደሌለ ያመለክታል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ የቅድስት ድንግል ማርያምን ሱባዔና በዓለ ትንሣኤ በከፍተኛ ሁኔታ እያከበረች ትምህርቱንም እምነቱንም ሥርዐቱንም በምልአት ይዛ መገኘቷ የዚሁ እውነት ማረጋገጫ ነው፡፡ ለነገሩ እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎቹ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናትም ማለትም ከደኃራውያኑ በቀር ጥንታውያኑ ሁሉ የምዕራቡም ሆኑ የምሥራቁ ክፍለ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት የድንግል ማርያምን ትንሣኤ እንደኛ ያምናሉ ያስተምራሉ ጾሙንም ይጾማሉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከሁሉም ይልቅ የሐዋርያት ትውፊትና ትምህርት፣ የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅር በኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በእጅጉ እንደሚያይል ለማንም ግልጽ ነው፤ ይህም የቤተ ክርስቲያናችንና የምእመናኖቻችን ሃይማኖት ምን ያህል በጸጋ እግዚአብሔር የተሞላ መሆኑን ያሳያል፡፡

የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ልጆቻችን፤

የሙታን ትንሣኤ በቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ የሚያቆም ሳይሆን በፊታችን ቆሞ ሁላችንንም እየጠበቀ የሚገኝ ድንቅ የእግዚአብሔር ግብዣ ነውና በእርስዋ ትንሣኤ ልክ እንድንነሣ ከሐዋርያት የወረስነውን ትምህርትና ትውፊት እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አጥብቀን በመያዝ እርሱን በማመንና በመጠባበቅ ለተጠራንለት የትንሣኤ ዘጉባኤ አምላካዊ ግብዣ በሚገባ ልንዘጋጅ ይገባል፤ ለዚህም እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፤ ቅድስት ድንግል ማርያምም በጸሎቷና በአማላጅነቷ አትለየን፡፡ በድጋሚ እንኳን ለበዓለ ፍልሰታ ለማርያም በሰላም አደረሳችሁ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. የጾመ ፍልሰታ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገር ውስጥና በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፤

እኛን ለክብርና ለምስጋና የፈጠረ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት የጾመ ማርያም ሱባዔ በሰላም አደረሳችሁ።

“ታዓብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር
ነፍሴ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ ”
(ሉቃ. 1÷47)

ይህንን የምስጋና ቃል የተናገረችው ወላዲተ እግዚአብሔር ቃልና ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን የአምልኮ ምስጋና ለእግዚአብሔር ስታቀርብ እርሱ ያደረገላትን ሦስት ዐበይት ምክንያቶች በመጥቀስ እንደሆነ ከቅዱስ መጽሐፍ እናስተውላለን፡፡ እመቤታችን ይህንን ምስጋና ከማቅረቧ በፊት እግዚአብሔር ለታላቅ በረከትና ለፍጹም ደስታ እንደመረጣት፣ የእርሱ ባለሟልና ምልእተ ጸጋ እንዳደረጋት፣ ቅዱሱን የእግዚአብሔር ልጅ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ እንደምትወልድና እግዚአብሔር ከእርሷ ጋር እንደሆነ በመልእክተኛ በቅዱስ ገብርኤል በኩል ነግሮአታል፡፡

እርሷም በቅዱስ ገብርኤል በኩል የተላከላትን የእግዚአብሔር ቃል ተቀብላ እነሆ የእግዚአብሔር ባሪያ ነኝ እንዳልከኝ ይሁንልኝ በማለት በታዛዥነትና በትሕትና ለደረሳት መለኮታዊ ጥሪ ተገቢውን የይሁንታ መልስ ሰጥታለች፡፡ በዚህ ጊዜ ቀዳማዊ ወልደ እግዚአብሔር በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍስዋ ነፍስን ነሥቶ ራሱን በማዋሐድ የዕለት ፅንስ ሆኖ በማሕፀንዋ አደረ፡፡ ጌታችን አምላካዊ ማንነቱን መግለጽ የጀመረው ከማሕፀን አንሥቶ ነውና እመቤታችን እሱን ፀንሳ ሳለች ኤልሳቤጥን እንዴት ነሽ ብላ የሰላምታ ድምፅን ስታሰማት በማሕፀነ ኤልሳቤጥ ያለው ፅንስ በማሕፀነ ማርያም ላለው ፅንስ በደስታ ሰግዶአል፡፡ ይህ አምላካዊ ምሥጢር በድንግል ማርያም ማሕፀን ውስጥ ያለው ፅንስ የአምልኮ ስግደት የሚገባውና ሁሉን የፈጠረ፣ ሁሉንም ማድረግ የሚችል የባሕርይ አምላክ መሆኑን አሳይቶአል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም የቅድስት ድንግል ማርያም የሰላምታ ድምፅ በኤልሳቤጥ ጆሮ በተሰማ ጊዜ በማሕፀንዋ ያለ ፅንስ በደስታ ሲሰግድ፣ በዚያ ቅጽበት ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ እግዚአብሔር በቅዱስ ገብርኤል በኩል የገለጸውን የእመቤታችን ክብርና ጸጋ፣ በረከትና ብፅዕና፣ የጌታ እናትነትና ባለሟልነት፣ የልጇ በረከትና አምላክነት በኤልሳቤጥ አንደበትም በድጋሚ እንዲነገር ማድረጉ የነገሩ ክብደትና ታላቅነት ምን ያህል እንደሆነ እንዲታወቅ አስችሎአል፡፡

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በቅዱስ ገብርኤልና በቅድስት ኤልሳቤጥ በኩል ስለ እርስዋ መናገሩና የእግዚአብሔር ወልድ በማሕፀኗ ማደሩ በዚህ ሁሉ እጅግ በጣምከኀይል ሁሉ የበለጠ ታላቅ ኀይል በእርስዋ ላይ እንደተደረገ እመቤታችን በሚገባ አውቃለች፡፡ ይህ እጅግ በጣም ታላቅ የሆነ ጸጋ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚተርፍ ልዩ በረከትና የእግዚአብሔር የማዳን ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ለማመልከትም ካንቺ የሚወለደው ሕዝቡን ከኀጢአታቸው የሚያድናቸው ስለሆነ ስሙ ኢየሱስ ትይዋለሽ ተብሎ በመልአኩ ተነግሮአታል፤ እርስዋም አምና ተቀብላለች፤ ለዚህ ታላቅ በረከትና መዳን በመሣሪያነት እርሷ መመረጥዋንም ልዩ ዕድል መሆኑን አልዘነጋችም፡፡ እንግዲህ እነዚህ ዐበይት ነገሮች በእመቤታችን አእምሮ ውሰጥ ከፍተኛ ስፍራ ነበራቸውና ያለምስጋና ልታልፋቸው አልፈለገችም፡፡ በመሆኑም የሆነው ነገር በሙሉ ለእርስዋና ለሰው ልጆች ሁሉ መሆኑን በሚገልጽ ኀይለ ቃል የአምልኮ ምስጋናዋን ለፈጣሪዋ ለእግዚአብሔር ግሩም በሆነ ሁኔታ አቅርባለች፡፡ በምስጋናዋም “ነፍሴ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬና በመድኀኒቴ ደስ ይላታል፤ የባርያይቱን ውርደት አይቶአልና፤ እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ነሽ ይሉኛል፤ እርሱ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶልኛልና” የሚል ጥልቅ ምሥጢር ያለው ኀይለ ቃል ይገኝበታል፡፡ ይኸውም “ብዙኃ አበዝኆ ለሕማምኪ ወለፃዕርኪ፤ በሕማም ለዲ፤ ምጥሽን ጣርሽን እጅግ አበዛዋለሁ፤ በጭንቅም ትወልጂያለሽ የሚል መርገም ተሸክማ በመከራ የኖረችውና ይህንን መከራ ለልጆችዋ ያወረሰችው ሔዋን በእርስዋ ጊዜና መሣሪያነት ከመርገም ተላቃ ወደ ገነት የምትመለስበት ጊዜ እየተቃረበ መምጣቱን ስታመለክት የባርያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና ነፍሴ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች በማለት አመሰገነች፡፡

የሰው ልጅን በአጠቃላይ ከገጠመው ውድቀት ለመታደግ እግዚአብሔር በጀመረው ነገረ አድኅኖ ከኀይል ሁሉ የበለጠ ኀይል እግዚአብሔር ወልድ በማሕፀኗ ማደሩ፣ እንደዚህም እርስዋ ለዚህ የበቃች ቅድስት፣ ንጽሕት፣ ቡርክት፣ ልዕልት፣ ብፅዕትና ከሴቶች ሁሉ የተለየች ምልእተ ጸጋ፣ ሙኃዘ ፍሥሐ፣ የእግዚአብሔር ልዩ ባለሟልና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ አድርጎ መምረጡንና ማክበሩን ሁሉ ለእርስዋ የተደረጉ ታላላቅ ነገሮች መሆናቸውን በመገንዘብዋ እመቤታችን ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶልኛልና መንፈሴ በአምላኬና በመድኀኒቴ ደስ ይላታል በማለት ፈጣሪዋን አመስግናለች፡፡ ከዚህም አይይዛ በእግዚአብሔር መልእክተኛ በቅዱስ ገብርኤልና መንፈስ ቅዱስ በሞላባት በቅድስት ኤልሳቤጥ የተገለጸውን ቅድስናዋና ብፅዕናዋ ዘመንና የስሑታን ትምህርት ሳይገቱት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይቋረጥ እንደ ወራጅ ውኃ እስከ ዕለተ ምጽአት እንደሚነገርና እንደሚተገበር በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝታ ተናግራለች፤ ቤተ ክርስቲያናችንም የእመቤታችንን ብፅዕና አክባሪና ከአማላጅነቷ ተጠቀሚ ሆና መገኝቷ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በደምብ ያወቀችና ቃሉን በምልአት የተቀበለች መሆኗን ያረጋግጣል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም የምስጋና ቃል የምንማረው ብዙ ትምህርት እንዳለ ማስተዋልና መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ከሁሉ በፊት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የተነገሩ ነገሮች በሙሉ ከፍጡራን መንጭተው የተነገሩ ሳይሆኑ ከእግዚአብሔር በቀጥታ ከተላከው መልአክ ከቅዱስ ገብርኤል፣ መንፈስ ቅዱስ ከሞላባት ከቅድስት ኤልሳቤጥና እንደዚሁም መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል ከተባለላት ከቅድስት ድንግል ማርያም የተነገሩ በመሆናቸው ምንጫቸውና ተናጋሪያቸው ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ መገንዘቡ አያዳግትም፤ ምክንያቱም ተላኪ የላኪውን፣ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት የመንፈስ ቅዱስን ቃል እንደሚናገር ለሁሉም ግልጽ ነውና፤ ቅዱስ መጽሐፍም እነዚህን በጥንቃቄ መዝግቦ መገኘቱ ይህንን እንድንገነዘበው ብሎ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህ አንጻር እግዚአብሔር ራሱ በፍጹም ክብር ያከበራትንና ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ነሽ እያሉ እንዲያመሰግኗት በቅዱስ መንፈሱ ያናገረላትን ቅድስት ድንግል ማርያምን ማክበርና ማመስገን፣ብፅዕናዋንና ቅድስናዋን ማመን፣ መስበክና ማሰተማር የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ተረድቶ ለቃሉ መታዘዝና ለተግባራዊነቱ መቆም እንደሆነ ለሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ ግልጽ ሊሆንለት ይገባል፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ላደረገላት ታላቅ ነገር ሁሉ ምስጋናን አምልኮትንና ምስክርነትን በመስጠት ለእኛ መልካም አስተማሪና አርኣያ መሆኗን ማስተዋል ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ ሁላችንም ልብ ብለን ካየነው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በአጠቃላይ ታላላቅ ሥራዎችን ያልሠራበት ቀን አይገኝም፤ ነገር ግን በየጊዜው ለሠራልን ሥራዎች ተገቢ ዕውቅና በመስጠትና በመመስከር እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም በደስታ የአምልኮ ምስጋናን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ስንት ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ብናነሣ መልሱ አስቸጋሪ ሳይሆን አይቀርም፤ ነገር ግን ድሮም እኛ የተፈጠርነው ለምስጋና ነውና እግዚአብሔር ያለሟቋረጥ ሁሌም ታላላቅ ነገሮችን እየሠራልን እንደሆነ ዐውቀንና አምነን ለእርሱ የሚገባ የአምልኮ ምስጋና ልናቀርብ ይገባል፡፡

ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በቀኖና ጸድቆ በጥንታውያንና በኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እየተፈጸመ የሚገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ ዐላማም፣ እግዚአብሔርን በምስጋና በቅዳሴ በውዳሴ ለማምለክ፣ ለቅዱስ ቃሉ ፍጹም ታዛዥ በመሆን ምሥጢረ ቊርባንን ለመቀበልና ከኀጢአት ሸክም ተላቀን ከእግዚብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር ነው፡፡

በዘመነ ብሉይም ሆነ በዘመነ ሐዲስ የእግዚአብሔር ሞገስና ጸጋ አግኝተው ለቅድስና ደረጃ የበቁ ቅዱሳን ሁሉ ጸሎታቸውና፣ ተማሕፅኖአቸው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለዓለሙ ሁሉ እንደሚተርፍ ቅዱስ መጽሐፍ በትምህርትም ሆነ በተግባር ያረጋገጠውና የመዘገበው ነው፡፡ ይልቁንም “እስመ ረከብኪ ሞገሰ በኀበ እግዚአብሔር ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና ምልእተ ጸጋ ነሽ፤ደስ ይበልሽ ብሎ እግዚአብሔር በመልእክተኛው ያረጋገጠላት ቅድስት ድንግል ማርያም ባላት ከፍተኛ የእግዚአብሔር ባለሟልነት በጸሎቷ በአማላጅነቷና ወደ እግዚአብሔር በምታቀርበው ተማሕፅኖ ግዳጃችንን እንደምትፈጽም የቃና ዘገሊላው ምልጃዋና የተገኘው በረከት በቂ ማስረጃችን ነው፡፡

በመሆኑም የጾመ ፍልሰታ ሱባዔ እግዚአብሔርን በአባትነት፣ ቅድስት ድንግል ማርያምን በእናትነት የምናገኝበት ልዩ ወቅት በመሆኑ እግዚአብሔር በቃሉ የተናገረውን በመከተልና እንደ ቃሉ በመመላለስ ጾሙን ልንጾም ይገባል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ፍቅርና ሰላም፣ መተጋገዝና መረዳዳት፣ ንስሓ መግባት፥ ጸሎት መጸለይ፣ ቅዱስ ቊርባንን መቀበል፥ ሰውን ማክበር የእግዚአብሔርን ቃል በማዳመጥና በመከተል መጾም ይኖርብናል፡፡ ይህ ጾም የሀገራችንን አንድነትና ነፃነት፣ የሕዝባችንን አብሮነትና የእርስ በርስ መተሳሰብ፣ እግዚአብሔርን የመፍራትና ድንግል ማርያምን የመውደድ፣ ሃይማኖታዊና ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን ሁሉ አዳብሮ ጥሩ ሰብእና ያለው ማኅበረ ሰብን ያፈራ፣ እንደ አሸንዳ የመሳሰሉ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ባህሎችን የገነባ ጾም ስለሆነ፣ ለሃይማኖታችን መጠበቅ፣ ለሀገራችን መልካም ገጽታ ግንባታና ለልማት መፋጠን እንደዚሁም ለቱሪዝም ክፍለ አኮኖሚ መበልፀግ የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ስለሆነ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ሀገራዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡

በመጨረሻም፡ የጾም ወቅት ምእመናን ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት፣ ርኅራኄና አዘኔታ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚያደርጉበት እንደመሆኑ መጠን፣ ምእመናን እጆቻቸውን ለተቸገሩ ወገኖች እንዲዘረጉ፣ ስለ ሀገርና ስለ ዓለም ሁሉ ሰላም መጠበቅ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት እንዲያቀርቡ፣ በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ዙሪያ መለስ የልማትና የእድገት ሽግግር እንዲሰምር በፍቅርና በሰላም ቆመው በአንድነት ጸሎታቸውን ሁሉን ወደሚችል ወደ ኀያሉ እግዚአብሔር ለማቅረብ እንዲተጉ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናሰተላልፋለን፡ ወትረ ድንግል ማርያም፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡