ግንቦት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

ቅዱስነታቸው ከተሾሙ በኋላ የመጀሪያው የርክበ ካህናት ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዐት ላይ የሚከተለውን ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ምስጋና የባሕርዩ የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን ሁላችንንም ከየሀገረ ስብከቱ አሰባስቦ በዚህ ሐዋርያዊ፣ ቀኖናዊና ዐቢይ ጉባኤ ተገናኝተን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ለመወያየት ስለፈቀደ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡ እንደዚሁም በዚህ ዐቢይ ጉባኤ ለመገኘት ከቅርብም ከሩቁም የመጣችሁ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሁላችሁም እንኳን በደኅና መጣችሁ፡፡

‹‹አስተጋብአተነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ሐዋርያት፤ ኀበ ሀለዉ አግብርተ እግዚአብሔር – ሐዋርያት የሰበሰቧት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር አገልጋዮች ወደአሉበት ሰበሰበችን› (ቅዱስ ያሬድ)፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው እዚህ ቅዱስ ስፍራ የሰበሰበችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፤ መሪያችንም መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እኛን የሰበሰበችበት፤ አምላካዊ ሰማያዊና ዘለዓለማዊ ዓላማ እንዳላት የምንዘነጋው አይደለም፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን ዓላማ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን ማስተማርና መንፈሳዊ አገልግሎትን ለእግዚአብሔርና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማበርከት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ሳይዛባ፣ ሳይፋለስ፣ ፈሩን ሳይለቅ በነበረበት ለማስቀጠል የመንበረ ሐዋርያት ወራሾች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በዓመት ሁለት ጊዜ በቋሚነት እየተሰበሰቡ፣ ስለአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እየገመገሙ፣ እየመከሩና እየወሰኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እምነትዋንና ሥርዓቷን እንዲጠብቁ ቅዱሳን አበው በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ደንግገዋል፡፡ የዛሬው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤም ይህንን ቀኖና ተከትሎ የሚካሄድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትዋን፣ (ዶግማዋን) ቀኖናዋን፣ ታሪኳን ጠብቃ የቆየች ጥንታዊት የሃይማኖት ተቋም መሆንዋ በዓለም ታሪክ የተደገፈ ሐቅ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንዋ አስተዳደር ሂደት ሲመረመር ግን እጅግ የተንዛዛ ቢሮክራሲ የሰፈነበትና የሰው ኀይል አመዳደቡም ከመሠረታዊው ተልእኮ ዕቅድ ጋር ያልተቀናጀ ከመሆኑም በላይ የሠራተኛው አቀጣጠር የሥራ ችሎታን፣ ዕውቀትንና ልምድን እንደ መስፈርት ወስዶ የተፈጸመ ባለመሆኑ የሠራተኛው ቊጥር ከሚያስፈልገው በላይ ወጥቶ ይታያል፤ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ሲመረመርም በወገንተኝነትና በሙስና የተቀጠረ መሆኑንና እንዲሁም አፈጻጸሙ የተለያዩ የሥነ ምግባር ብልሹነት በስፋት የሚያንጸባርቅ ሆኖ ይስተዋላል፡፡

ይህ ከቤተ ክርስቲያኒቷ ክብርና ቅድስና ጋር የማይጣጣም ሂደት በመሆኑ ሁኔታውን ለማረም ቅዱስ ሲኖዶሱ አስቸኳይ እርምጃ ሊወስድበት ይገባል፡፡ አስፈላጊው እርማት በወቅቱ ሳይደረግ በመቅረቱ፣ የምእመናኑ በቤተ ክርስቲያኒቷ አመራር ላይ ቅሬታና እምነት ማጣትን እያሳደረ ሁኔታውም እየተባባሰ ሲሄድ ይታያል፡፡ ስለዚህ ታሪክ እንዳይፈርድብን ካህናቱንና ምእመናኑን በማስተባበር አስቸኳይ የእርምት እርምጃ መውሰድ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የሀገሪቱ መንግሥት ሙስናን ለማጥፋት በሚታገልበት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሙስና በፍጹም መታየት የለበትም፡፡

የቤተ ክርስቲያናችንን ስም ለመጠበቅና ክብርዋን ለማደስ እንዲቻል የሚከተሉት ሥር ነቀል የለውጥ እርምጃዎች በቈራጥነት ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

1.ብልሹ አሠራርን ለማረምና ለማስወገድ፤
ከሊቃነ ጳጳሳት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ እንዲሁም ከምእመናን የተውጣጡ አባላት የሚገኙበት ‹‹የፀረ ሙስና ዐቢይ ኮሚቴ›› እንዲቋቋም ሆኖ ፍትሓዊ በሆነ መንገድ ሁኔታውን እየመረመረ ስንዴውን ከእንክርዳድ ለይቶ እንዲያቀርብ ማድረግና እንክርዳድ ሆኖው በሚገኙት ላይ አስተማሪ የሚሆን ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ፡፡

2. አስተዳደሩን በአዲስ መልክ ስለማዋቀር፤
የቤተ ክርስቲያኒቱን የአስተዳደር መዋቅርና የሚሠሩባቸውን ደንቦችና ሕጎች ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ጨምሮ የሚመረምርና የማሻሻያ ሐሳብ የሚያቀርብ ‹‹የአስተዳደር መሻሻል ዐቢይ ኮሚቴ›› እንዲቋቋምና፤ አባላቱም አሁንም ከሊቃነ ጳጳሳት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከካህናትና ከምእመናን የተውጣጡ እንዲሆኑ ተደርጎ አስተዳደሩ ለለውጥ የተዘጋጀ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው ለማድረግና ውጤት ተኮር የሆነ ሥርዐት ለመዘርጋት የሚያስችል የማሻሻያ ጥናታዊ ሐሳብ እንዲያቀርብ ማድረግ፤ በተጨማሪም አስተዳደሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ራእይና ተልእኮ በግልጽ የሚያሳይ እስትራቴጂካዊ የአመራር ሥርዐት እንዲነድፍና የተሟላ የማሻሻያ ሐሳብ እንዲያቀርብ ማድረግ፡፡

3. የፋይናንስ አያያዝን በተመለከተ፤
የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዐት ዘመናዊ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለማደራጀት የሚያስችል ሥርዐት እንዲዘረጋ ለማድረግ ጥናት እንዲያቀርብ ባለሙያዎች በአባልነት የሚገኙበት ‹‹የገንዘብ አያያዝ ሥርዐት ማሻሻያ ዐቢይ ኮሚቴ›› እንዲቋቋምና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ የሚሠራበትን ሥርዐት መርምሮ አንድ ወጥ የሆነ ሥርዐት ለመዘርጋት የሚያስችል ሐሳብ እንዲቀርብ ማድረግ፡፡

እነዚህ ሦስት መሠረታዊ እርምጃዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ጤናማ ሂደት የሚወስኑ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የቀረበው ሐሳብ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ቈራጥ የሆነ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል፡፡ ሥር ሰዶ የሚታየው አሳፋሪና አሳዛኝ ብልሹ አሠራር ሳይታረም ቢቀጥል ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደምትወድቅ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ እኛ በአመራር ላይ ያለነውን ሰዎች ይህ ብልሹ አስተዳደር እንደሚያስወቅሠንና እንደሚያስፈርድብን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ እርምጃው፣ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ቈራጥነትን ይጠይቃል፡፡ በአጭር ጊዜ የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የሚያዳግት ቢሆንም የለውጡን መሠረት ግን በአስቸኳይ ማስቀመጥና አቅጣጫውን መቀየስ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤

ይህንን ስንል ግለሰቦችን ለማደንና ለመጒዳት አይደለም፤ የምናተኵረው ወደ ሥርዐቱ እንጂ ወደ ግለሰቦች አይደለም፡፡ ፀረ ሙስና ሥርዐት ከተደነገገ ሙስናው ይጠፋል፤ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ታገኛለች፤ ዓላማችን ይህ ብቻ ነው፤ ሌላ ጒዳይ የለንም፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በተመለከተ፤

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአራት ሊቃነ ጳጳሳትና በአራት ሥራ አስኪያጆች እንዲተዳደር የተወሰነ ቢሆንም፣ አሁን እየተሠራ ያለው በሁለት ሊቃነ ጳጳሳትና በአራት ሥራ አስኪያጆች ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደታሰበው አደረጃጀቱ ችግር ፈች ሆኖ አልተገኘም፡፡ በዋነኛነት ምደባው ጥናት ተደርጎለትና መስፈርት ወጥቶለት በውድድር መሆን ሲገባው ይህ ባለመፈጸሙ እንዲሁም በወረዳ ደረጃ ላለው መዋቅር ሥልጣን ተከፍሎ ያልተሰጠውና ሥራውን የማይሠራ ስለሆነ ችግሩ እየገዘፈና እየተመሰቃቀለ በመምጣቱ የመልካም አስተዳደር ዕጦት መንሥኤ በመሆኑ አሁን ያለውን አደረጃጀት መቀየር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ስለዚህ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ፓትርያርኩ ሀገረ ስብከት ስለሆነ፤ በአስተዳደር ችሎታው ጠንካራ የሆነ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በመመደብ፤ እንዲሁም እርሱን የሚረዱ በሥራ ችሎታው ብቁና ጠንካራ የሆኑ ሥራ አስኪያጆችን መድቦ በመሰየም ተጠያቂነትና ኀላፊነት ያለው ግልጽ የሆነ ጠንካራ የአስተዳደር ሥርዐት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

እግዚአብሔር በልዩ አጠራሩ ሁላችንንም ጠርቶና መርጦ እዚህ ቦታ አስቀምጦናል፤ በዚህ ቦታ ሆነን የምናካሂደው ጉባኤና የምናሳልፈው ውሳኔ ሁሉ በእግዚአብሔር፣ በታሪክና በመጪው ትውልድ ፊት ሁልጊዜ በሚዛን እየተመዘነ የሚኖር እንደሆነ ልንዘነጋው አይገባም፡፡

እኔም ሆንሁ ብፁዓን አባቶች ሁላችሁም፤ ትናንት አንድ ላይ ሆነን በቤተ ክርስቲያናችን መታየት የሚገባቸውን የአሠራር ክፍተቶች አሉና መፍትሄ እናበጅላቸው ብለን በዚህ ቦታ ብዙ ጊዜ አንሥተናል፡፡ ይሁን እንጂ እስከአሁን አልተስተካከሉም፤ በመሆኑም፤ እነርሱን ዛሬ በፍጥነት ማስተካከል ካልቻልን በቅድሚያ በእኛ ላይ የሚፈርድ የገዛ ራሳችን ኅሊና ነው፤ በይቀጥላልም እግዚአብሔርም ሌላውም ሁሉ ይፈርድብናል፡፡

እኔ ወንድማችሁንም በዚህች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳገለግልና እንድላላክ መርጣችሁ በዚህ ትልቅ ኀላፊነት ወንበር ላይ ስታስቀምጡኝ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ የምእመናንን የልብ ትርታ እያዳመጥሁ ለእናንተ ለብፁዓን አባቶች ሳቀርብ ይሁንታውንና እገዛውን እየለገሳችሁኝ የጋራ ኀላፊነታችንን እንድንወጣ መሆን አለበት፡፡

ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች የሚቀርፍ አጀንዳ በመያዝ፣ በማጽደቅ፣ በስፋትና በጥልቀት በመወያየት ቤተ ክርስቲያናችንን የሚታደግ ችግሮችን የሚቀርፍ መመሪያ እንዲያወጣ ጥሪዬን በእግዚአብሔር ስም አስተላልፋለሁ፡፡

እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ!

ሚያዝያ 27 ቀን 2005 ዓ.ም የበዓለ ትንሣኤ ሐዋርያዊ መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣

በትንሣኤው ትንሣኤያችንን ያበሠረን ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለ2005 ዓ.ም በዓለ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“እስመ ሐደሰ ለነ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት ንቅረብ እንከ በልበ ጽድቅ
የሕይወትና የእውነት መንገድን አድሶልናልና ከእንግዲህ በቅን ልቡና ወደ እርሱ እንቅረብ።”
(ዕብ. 1ዐ፣19)

የሰው ልጅ ለማያረጅና ለማያልፍ ሕይወት የታደለ፣ በእግዚአብሔር አምሳልና አርኣያ የተፈጠረ፣ እጅግ ክቡርና ታላቅ ፍጥረት እንደነበረ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ በምድር በሚገኙ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ያለው የበላይነት ሥልጣንም ይህንን ያረጋግጣል፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድ ይህን ያህል ጸጋ ቢኖረውም የተሰጠውን ክብርና ልዕልና በአግባቡ ጠብቆ መዝለቅ አልቻለም፤ በእግዚአብሔር ፊት በፈጸመው ከባድ በደል ምክንያት የተሰጠውን ጸጋና ክብር ከማጣቱም በላይ በሕይወት ፈንታ ሞትን፣ በእውነት ፈንታ ሐሰትን፣ በዘለዓለማዊነት ፈንታ ጊዜያዊነትን፣ በማያረጀው ፈንታ የሚያረጀውን ሕይወት ተላብሶ ወደ ምድረ ፍዳ ተባረረ፤ ከእግዚአብሔር ልጅነት ተራቈተ፣ ከማኅበረ መላእክት ተለየ፤ ረዳት የለሽና ጎስቋላ ሕይወት ተሸክሞ መኖር ጀመረ ፡፡

ለእርሱ ያልተፈጠሩ የሞትና የመቃብር ጎዳናዎች እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ድረስ በሰፊው ተጓዘባቸው፡፡ ከክርስቶስ በፊት የነበሩ በሺሕ የሚቀጠሩ ዓመታት ለሰው ልጅ የፍዳ፡ የመርገም፣ የከነኔ ዓመታት ነበሩ፤ ሲኦልና ገሃነም የሰው ዘርን በአጠቃላይ ለመዋጥ አፋቸውን የከፈቱበትና ሰውን ሁሉ በመራራ ሥቃይ የማገዱበት፣ ገነትና መንግሥተ ሰማያት አንድ ስንኳ ለእነርሱ የተገባ ፍጡር የሌለ እስኪመስሉ ድረስ ባዶአቸውን ተዘግተው የነበሩበት መራራ ጊዜ ነበር፡፡ እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ እንደመሆኑ መጠን በሰው በደል ምክንያት ትክክለኛ ፍርዱን ቢያስተላልፍም ከፈራጅነቱ ጎን ለጎን መሓሪነቱን የማያርቅ ለፍጥረቱ እጅግ ርህሩህ ነውና በሰው ላይ የተላለፈው የሞተ ነፍስ ፍርድ በልጁ በጌታችን በአምላካችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋትነት እንዲያከትም አደረገ፤ የተዘጋው የገነት በር እንዲከፈት፣ በሲኦል የተጋዙ ነፍሳት ወደ ገነት እንዲመለሱ፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሰው ጒዞ ወደ ሲኦል መሆኑ ቀርቶ ወደ ገነት እንዲሆን በማድረግ ሰውን በክርስቶስ ደም ታረቀው ፡፡

በዚህ ታላቅ መሥዋዕትነት ያረጀውን የሲኦል መንገድ ዘግቶ አዲስ የገነት መንገድን ስለከፈተልን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አዲስ የእውነትና የሕይወት መንገድ ከፍቶልናልና ከእንግዲህ ወዲህ በቅን ልቡና ወደርሱ እንቅረብ እንዳለ በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ሐሳባችን፣ በፍጹም ኀይላችን ወደ እርሱ ልንቀርብ ይገባል ፡፡

ያረጀው ነገር ሁሉ በክርስቶስ ደም ተቀድሶና ነጽቶ ሐዲስ ሆኖአል፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሠርቶ የሚያሠራ የመልካም ነገር ሁሉ አርኣያና መሪ እንደመሆኑ መጠን አዲሱን መንገድ ከፍቶ እንድንጓዝበት ሲያደርግ እኛም በሐዲስ መንፈስ በአዲስ ሕይወት ልንመላለስበት እንጂ እንደገና ወደ አደራጀውና ወደአፈጀው ሕይወት ተመልሰን ልንዘፈቅ አይደለም ፡፡ አዲስ ሕይወት ማለት እግዚአብሔር ለሰው ዘር ሁሉ መድኀኒት እንዲሆን በላከው በመድኀኒችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዘለዓለም ድኅነትን ማግኘት ነው፤ ምንም ዐይነት አማራጭ የማይገኝለት ይህ የእግዚአብሔር የማዳን ጸጋን የሰው ዘር ሁሉ ተቀዳሚ ሥራው አድርጎ ሊቀበለው ይገባል፤ በዚህ በኩል ካልሆነ ቢቀር ሌላ የምንድንበት መንገድ የምናመልጥበት ዓውድ ፈጽሞ የለምና፡፡

የክርስትና ሃይማኖት በቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ እንደተቀመጠው በመልካም ሥነ ምግባር ገዝፎ የሚታይ ሃይማኖት እንጂ በእምነት ብቻ ተደብቆ የሚኖር ሃይማኖት አይደለም፤ በርቀት ያለችው ነፍሳችን በግዙፉ የሥጋ አካላችን ውስጥ ሆና በምትሠራው ሥራ አማካይነት በአካላችን ውስጥ አንዳለች እንደምናውቅ ሁሉ አንድ ክርስቲያንም መልካም ሥራን አብዝቶ ሲሠራ በሥራ ገላጭነት ሃይማኖቱ ገዝፎ በጒልህ ይታያል፤ በመሆኑም በክርስትና ሕይወት ሃይማኖትና ሥነ ምግባር እንደነፍስና እንደሥጋ ተዋሕደው በአንድነት ሲኖሩ ሕይወተ ነፍስን እንደሚያጎናጽፉ ልብ ብሎ ማስተዋል ይገባል፡፡ ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ በሚመነጨው መርሕ መሠረት በሥራ በመትጋትና በፍጹም ፍቅር በመኖር ሕይወታችንን ይበልጥ ልናሳድገው ይገባል፤ ከሁሉ በፊት ሰው የተፈጠረው ለሥራና ለክብር እንደሆነ ከቶ ልንዘነጋው አይገባም፤ ይህም ከሆነ ሰው ለአንዲት ደቂቃ ያህል እንኳ እጅ እግርን አጣጥፎ ያለሥራ ሊቀመጥ እግዚአብሔር አልፈቀደም አይፈቅድምም፡፡ “ወበሐፈ ገጽከ ብላዕ ኅብስተከ — ወደ ወጣህባት መሬት እስክትመለስ ድረስ ጥረህ ግረህ ላብህን አንጠፍጥፈህ ብላ” ነውና ይላል (ዘፍ. 3፥19)፡፡ በዙሪያችንም ሆነ በሌላው አካባቢ የተሻለ ኑሮና ክብር ያላቸው ሆነው የሚታዩ ሁሉ የመክበራቸው ምሥጢር ጠንክረው መሥራታቸው እንደሆነ በውል ልናጤነው ይገባል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያንም በታላቁ የሕዳሴ ግድባችን እንደሚታየው ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ በትጋት ከሠራን በአጭር ጊዜ ሌሎች የበለጸጉ ሀገሮች ከደረሱበት የእድገት ደረጃ የማንደርስበት ምክንያት አይኖርም፤ ዋናው ቁም ነገር ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በኅብረት፣ በአንድነት፣ በስምምነት፣ በመተማመን፣ በመቻቻል ለሥራና ለሥራ ብቻ መነሣቱ ላይ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የምናየው ስለሆነ ለምንጣደፍለት የእድገት ሸግግር ትልቅ መሣሪያችን መሆኑን አውቀን እንደ ዐይን ብሌን ልንጠብቀው ይገባል፤ ይህ የሆነ እንደሆነ የሕዳሴውን ግድብ ጨምሮ በሀገራችን የተጀመሩትን ታላላቅ ሥራዎች ሁሉ ያለጥርጥር ማሳካት እንችላለን፡፡ የእውነትና የሕይወት መንገድ አድሶልናል የሚለውን የፋሲካ ትምህርተ ሃይማኖት የሕዳሴውን ልማት በማፋጠንና በማሳካት ልንገልጸው ይገባል፡፡

በሌላ በኩል ታላቁን የፋሲካ በዓላችንን ስናከብር ለእኛ ብሎ፣ በእኛ ፈንታ መሥዋዕት ሆኖ የዘለዓለም ሕይወትን ካጎናጸፈን ጌታ ጋር ማክበር አለብን፤ ፋሲካን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ማክበር የምንችለው የተራቡትን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታመሙትንና የታሠሩትን በመጠየቅ፣ እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ ነው፡፡ ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያኑ ከሃይማኖቱ፣ ከተቀደሰ ሥነ ምግባሩና ባህሉ በወረሰው ሥርዐት መሠረት እንደተለመደው በዓሉን በሰላም፣ በፍቅር፣ በስምምነትና በመረዳዳት፣ ድሆችን ይዞ በመመገብ በመንፈሳዊ ደስታ እንዲያከብር መንፈሳዊ መልእክታችንንና ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ የተቀደሰና የተባረከ የፋሲካ በዓል ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ሀገራችንንና ሕዝባችንን ይባርክ አሜን።