• Amharic  
  • English 
  • Home
  • Papal Messages
  • Biography
  • Patriarchs
  • Contact
  • Menu Menu

ጥር 11 ቀን የ2007 ዓ.ም. በዓለ ጥምቀት በተመለከተ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

February 16, 2015

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

“ወደምሰሰ ለነ መጽሐፈ ዕዳነ
የዕዳችንን መጽሐፍ ደመሰሰልን።”
(ቈላ. 214)

የሰው ልጅና የሌሎች ፍጡራን መኖሪያ የሆነው ዓለም በኀጢአተ ሰብእ ምክንያት ክፉኛ ተበክሎ እስከ ክርስቶስ ድረስ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ያህል በፍዳና በኵነኔ ዕዳ ተይዞ መቆየቱ ይታወሳል፤ የዕዳው መነሻ ኀጢአተ አዳም ቢሆንም ከእርሱ በኋላ የተነሡ ልጆቹም በተመሳሳይ ኀጢአተኞች ሆነው ስለቀጠሉ ችግሩ እየባሰና እየሰፋ መጥቶ ከነፍሳዊ ኵነኔ በተጨማሪ ምድርን በጥፋት ውኃና በእሳተ ገሞራ ሊያስቀጣ ችሎአል፤ ያም ሆኖ በበደል ላይ በደል፣ በስሕተት ላይ ስሕተት ከመጨመር በቀር የተሻለ ነገር አልታየም፤ በመሆኑም ሰው ሁሉ በኀጢአት ዕዳ ተይዞ ነበር፤ (ዘፍ. 31-24፤ 717-23፤ 191-29)

እግዚአብሔር በሁለመናው ንጹሕና ቅዱስ በመሆኑ በኀጢአት የተዳደፈው ፍጡር በመንግሥቱ እንዲኖር አይፈቅድም፤ ይልቁኑም እውነተኛ ፈራጅ በመሆኑ በኀጢአት ላይ ፈርዶ ኀጢአተኛውን ይቀጣል፤ ጻድቁን ደግሞ በጽድቅ ሥራው ያከብራል፤ (ማቴ. 2546፣ ማቴ. 2211-14)፡፡ ከዚህ አንጻር ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ የነበረው ሰው ሁሉ ኀጢአተኛ ሆኖ ስለተገኘ በኀጢአት ዕዳው ከሚፈረድበት በቀር የሚድንበት ቀዳዳ አልነበረምና የሰው ዘር ሁሉ ለኀጢአት ፍርድ የተጋለጠ ሆነ፤ (ሮሜ.323)፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እውነተኛ ፈራጅ ቢሆንም መሓሪና ይቅር ባይም ነውና በልጁ መሥዋዕትነት የሰውን ዕዳ ኀጢአት ሠርዞ ሰውን በምሕረቱ የሚቀበልበት ዕድል እንዳመቻቸ በአፈ ነቢያቱ ገለጠ፤ (ኢሳ. 531-12) ዘመኑ ሲደርስም ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ሰብእ ተወለደ፤ ግዕዘ ሕጻናትን ጠብቆ በየጥቂቱ አደገ፤ በሠላሳ ዓመቱም በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡

በአራቱ ወንጌላውያን ትምህርትና ምስክርነት እንደተገለጸው ጌታችን ሲጠመቅ እግዚአብሔር አብ በብሩህ ደመና ሆኖ “ይህ የምወደው ልጄ ነው እርሱን ስሙት” ሲል፣ መንፈስ ቅዱስም በነጭ ርግብ አምሳል ወርዶ በጌታችን ላይ ሲቀመጥ፣ ሰማያትም ሲከፈቱ መታየታቸው፣እግዚአብሔር በአካል ሦስት መሆኑንና ኢየሱስ ክርስቶስም ከሦስቱ አካላት አንዱ መሆኑን ከመታወቁም በላይ ሰው ከዕዳ ኀጢአት ነፃ ሆኖ በልጅነት ክብር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት የሚችልበት ዕድል ምን እንደሆነ በግልጽ ያመላከተ ነበር፤ ይኸውም ሰው በእምነትና በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት እንደሚችል ያረጋገጠ ክሥተት ነው፡፡

የክርስትና አስተምህሮ ትምህርተ ይማኖትንና ትምህርተ ድኅነትን በተመለከተ መሠረት አድርጎ የሚነሣው ከዚህ አስተርእዮተ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር መገለጥ) ነው፤ በጌታ ጥምቀት ከተፈጸመው አስተርእዮተ እግዚአብሔር የምንወስዳቸው ዐበይት ትምህርቶች የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፤ ይኸውም፡- (1) እግዚአብሔር በአካል ሦስት በባሕርይ አንድ መሆኑን፤ (2) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ አካላት አንዱ መሆኑን፤ (3) ሰው በንስሓ ተነሥቶ፣ በእምነት ተጒዞ፣ በጥምቀት ነጽቶ፣ በሥነ ምግባር ጸንቶ ሲገኝ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆን እንደሚድንና መንግሥተ ሰማያት ለእርሱ ክፍት እንደሆነች ጌታ ሲጠመቅ ከተገለጡት ተኣምራዊ ትምህርቶች እናስተውላለን፤ (ማቴ. 31-17)

ጥምቀት ለድኅነተ ሰብእ የመጀመሪያው በር ነውና ጌታችን በጥምቀቱ ከገለጠው ተኣምራዊና ገቢራዊ ትምህርት በተጨማሪ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን በሚያስተምርበት ጊዜ “ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ብሎ የምሥጢረ ጥምቀትን ትምህርት አጠንክሮታል፤ (ዮሐ. 35)፡፡ ዓለምን የማዳን ሥራው ፈጽሞ ከተነሣ በኋላም “ሰዎችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል” ብሎ አጽንቶታል (ማቴ 2819፤ ማር. 1616) በመሆኑም የምሥጢረ ጥምቀት ትምህርት ከጌታችን የጥምቀት ዋዜማ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ፣ ከዚያም በስብከተ ሐዋርያት ወቅት የትምህርተ ወንጌል ማእከል ሆኖ መነገሩና በጥብቅ መተግበሩ ጥምቀት ለሰው ልጅ ድኅነት ያለው ትርጒም ምን ያህል የላቀ እንደሆነ በትክክል ያሳየናል፤ (የሐ. ሥራ 238-42) የጥምቀትን በዓል በየዓመቱ ስናከብር በዮርዳኖስ ወንዝ ስለ እግዚአብሔር ማንነትና ስለ ድኅነታችን ክንዋኔ የተላለፉ አምላካዊ መልእክቶችን በሚገባ በማስታወስ፣ በማስተዋልና በተግባር በመፈጸም ሊሆን ይገባል፡፡

ከጥምቀት በዓል የምንወስደው ትምህርት ሃይማኖታዊውን ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊውንም ጭምር ነው፤ በዓለ ጥምቀት ተራራውና ኮረብታው ዝቅ ይበል፣ ጐድጓዳው ይሙላ፣ ጠማማውም መንገድ ቀጥ ይበል እያለ ሁሉም በእኩልነትና በጥሩ ሥነ ምግባር፣ በመከባበርና በመረዳዳት እንዲኖር የሚያስተምር ነው (ሉቃ. 33)፡፡ በመሆኑም በዓሉ ተወዳጅና የፍቅር በዓል በመሆኑ ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ በአጠቃላይ ያለው ጠቃሚነት እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ የጥምቀት በዓል ሁሉም ከሸፍጥና ከቅጥፈት ርቆ በደመወዙ ብቻ እንዲተዳደር፣ ትርፍ የሆነ ልብስና ምግብ ያለውም ለሌለው ወገኑ እንዲያካፍል፣ ጒልበተኛም በጒልበቱ ተመክቶ ደካማውን እንዳይቀማ፣ ባለሥልጣንም ሥልጣኑን መከታ አድርጎ ግፍ እንዳይፈጽም አጥብቆ የሚያስተምር በዓል በመሆኑ በዓሉ ከሃይማኖታዊ አስተምህሮው ሌላ በሥነ ምግባርና በማኅበራዊ አስተምህሮም በማናቸውም መመዘኛ ተወዳዳሪ የሌለው በዓል ነው (ሉቃ. 33-14)። በበዓለ ጥምቀት አስተማሪነት ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሃይማኖታቸውን፣ አንድነታቸውን፣ ፍቅራቸውንና ባህላቸውን ጠብቀው ለዘመናት ዘልቀዋል፤ በዓለ ጥምቀት ዘር፣ ጎሳ፣ ዕድሜ፣ ፆታ፣ ቀለም፣ ቋንቋ፣ ወንዝ፣ ተራራ ሳይገድበው ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የሚያስተናግድና የማይበጠስ የአንድነት ገመድ ነው፡፡

ስለሆነም በዓለ ጥምቀት የሃይማኖታችን ብቻ ሳይሆን የአንድነታችንና የእኩልነታችን፣ የባህላችንና የአብሮነታችን ጠባቂ በዓል በመሆኑ ልንጠብቀው፣ ልናከብረውና ለዓለም ሁሉ ልናስተዋውቀው ይገባል፤ የበዓሉ አጠቃላይ ገጽታ ሃይማኖትና ክብር፣ ሰላምና ፍቅር፣ ነፃነትና ደስታ፣ እኩልነትና አንድነት፣ ምሕረትና ይቅርታ ነው፤ እነዚህ ዕሴቶች ለሰው ልጅ የተስተካከለ አኗኗር እጅግ አስፈላጊ ናቸውና እነዚህን ጠብቀን ከተጓዝን የማንወጣው ተራራና የማንሻገረው ወንዝ አይኖርም፤ በዘመናችን ልማቱና እድገቱ መከባበሩና ወንድማማችነቱ በሚያስደንቅ ሁኔታ እየጎለበተ የመጣው እኩልነትና ሰላም ስለተረጋገጠ ብቻ ነው፤ ስለዚህ ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገ ወዲያም፣ ሰላምና እኩልነት፣ ፍትሓዊነትና ሕዝባዊነት ቦታ ሊነፈጋቸው አይገባም፤ እነዚህ መርሆዎች የሃይማኖታችን ዋና ምሰሶዎች ከመሆናቸውም ሌላ የልማታችንና የእድገታችን ዘላቂ ዋስትና ናቸውና ከማንም በላይ አብልጠን ልንጠነቀቅላቸው ይገባል፡፡ እግዚአብሔር መልካም የጥምቀት በዓል ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤ ይቀድሳችሁ፤ አሜን!

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/e/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc3 https://eotcp.org/e/wp-content/uploads/logo-en.svg tc32015-02-16 12:46:592025-01-28 12:48:11ጥር 11 ቀን የ2007 ዓ.ም. በዓለ ጥምቀት በተመለከተ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
  • የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው የዐቢይ ጾምን መግባት በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል
  • ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም የጾመ ነነዌ የሰላምና የጸሎት አዋጅ
  • በቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክና የተከናወኑና በታሪክ የሚዘከሩ ዐበይት ተግባራት፤

Archives

  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ታኅሣሥ 29 ቀን የ2007 ዓ.ም የልደት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: ታኅሣሥ 29 ቀን የ2007 ዓ.ም የልደት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ታኅሣሥ 29 ቀን የ2007 ዓ.ም የልደት በዓል ቃለ ምዕዳንና... Link to: የካቲት 9 ቀን የ2007 ዓ.ም የዐቢይ ጾም መግቢያ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: የካቲት 9 ቀን የ2007 ዓ.ም የዐቢይ ጾም መግቢያ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የካቲት 9 ቀን የ2007 ዓ.ም የዐቢይ ጾም መግቢያ ቃለ...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top