• Amharic  
  • English 
  • Home
  • Papal Messages
  • Biography
  • Patriarchs
  • Contact
  • Menu Menu

ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

May 29, 2024

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ብፁዕ አቡነ አብርሃም
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ
የሰሜን ጎጃምና የባሕር ዳር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

እግዚአብሔር አምላካችን በቤተ ክርስቲያን ላይ በየጊዜው የሚደርሰውን ፈተና በማስቻል ለዚህ ሲኖዶሳዊ ምልአተ ጉባኤ እንኳን በሰላም አደረሰን!

‹‹አስተብቊዓክሙ አኃዊነ በስሙ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ትበሉ ኵልክሙ አሐደ ቃለ ወአሐደ ነገረ ወትኩኑ ፍጹማነ ወኢትትፋለጡ ወሀልዉ በአሐዱ ምክር ወበአሐዱ ልብ፤ ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ፣ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ›› (፩ቆሮ ፩፥፲)፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን መልእክት ለቆሮንቶስ ሰዎች ለመጻፍ ሲያስብ አንድ ዓቢይ ምክንያት እንዳለው ከመልእክቱ ይዘት መረዳት ይቻላል፤ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አንድነትንና ሰላምን ፍቅርንና መተባበርን ከምትሰብከው ወንጌለ መንግሥተ እግዚአብሔር ወጥተው ብዙ ርቀት ሂደዋል፤ አንድነቱ፣ ኅብረቱ መረዳዳቱ መተጋገዙና መተባበሩ ከመካከላቸው ጠፍቶአል፤ ሌላው ቀርቶ ቅዱስ ቊርባንን ለመቀበል በሚሰበሰቡበት ጊዜ እንኳ የሀብታምና የድሀ የሚል ክፍፍል ተፈጥሮ ቤተ ክርስቲያኗን አደጋ ላይ ጥሎአል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን እና ይህንን የመሳሰለ ፈተና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሥር እየሰደደ መምጣቱን በእጅጉ አሳስቦታል፤ ይህ የሰላምና የአንድነት ጠንቅ የሆነው የመለያየት አዝማሚያ በጣም ሰፍቶ ቤተ ክርስቲያንን ከማፍረሱ በፊት በትምህርት በምክርና በተግሣጽ ማረም እንዳለበት ቅዱስ ጳውሎስ ተገንዝቦአል፤ እሱ ራሱም በአካል በመካከላቸው ተገኝቶ ሊያስተካክላቸው ፈቃደኛ ነበረ፤ ነገር ግን እሱ በዚህ ጊዜ በሮም ውስጥ እስር ቤት ላይ ስለነበረ አልቻለም፤ የነበረው አማራጭ በጽሑፍ ማስተማርና መምከር ነውና፤ ይህንን መልእክት ጽፎላቸዋል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዘላቂው የቤተ ክርስቲያን ፈተና ሲነግረን ‹‹ወበዓለምሰ ሀለወክሙ ትርከቡ ሕማመ፤ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ›› እንዳለው ቤተ ክርስቲያን ከፈተና ተለይታ አታውቅም፤ ፈተናውም ከተወሰነ አቅጣጫ ብቻ የሚመጣ ሳይሆን ከብዙ አቅጣጫ ይከባታል፤ የቤተ ክርስቲያን መከራ ከውጭ ብቻም አይደለም ከውስጥም እንጂ፤ ከባዕድ ብቻም አይደለም ከወዳጅም እንጂ፣ የወዳጅ ፈታኝ እንደሚብስም ታውቆ ያደረ ነገር ነው፤ ባዕዳውያን አይሁድ ጌታን ይዘው የገደሉ የውስጥ ሰው የሆነው ይሁዳ በሰጣቸው ምልክት ነው፡፡

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በከባድ ፈተና ውስጥ እያለፈች ትገኛለች፤ እንደተነገረው የውጭው ፈተና ባይቀርላትም ከሱ በላይ ግን በውስጧ የሚነሡ ፈተናዎች ተልእኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ ዕንቅፋት ሆነውባታል፤ ከጥንት ጀምሮ የነበረ፣ በእግዚአብሔር ቃል የተቃኘ፣ የጸሊአ ሢመትና የጸሊአ ንዋይ መንፈሳዊ ባህሏ ተዘንግቶአል፤ በምትኩም ፍቅረ ሢመትና ፍቅረ ንዋይ ነግሦአል፤ መለያየትና መነቃቀፍ እየሰፉ መጥተዋል፣ ሃይማኖታችንንና ባህላችንን የማይወክሉ ኃይለ ቃላት፣ ኃላፊነት በጐደለው አገላለጽ እየተሰነዘሩ በጎቻችንን አስበርግገዋል፤ ድርጊቶቹ በበጎቻችን ዘንድ የነበረንን ተሰሚነትና ተደማጭነት ሊቀንሱብን እየተንደረደሩ ነው፡፡
እነዚህና እነዚህ የመሳሰሉ ክሥተቶች በውስጣችን ሥር በሰደዱ ቁጥር ጉዳትን እያስከተሉ ነው፤ ሰዎች ከኦርቶዶክሳዊ ቀኖና እና ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ ራስን በራስ የመሾም አባዜ እየተለማመዱ ነው፤ እሽቅድምድሙም በዚህ ዙሪያ አይሎአል፤ በአጠቃላይ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን የፈተነ መለያየት በቤተ ክርስቲያናችንም ብቅ ጥልቅ እያለ እየፈተነን ነው፤ የፈተናው መንሥኤ ውጫዊ ሳንካ ባይጠፋበትም የውስጣችን ሰዎች ለሱ ምቹ ሆነው መገኘታቸው አልቀረም፤ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ፈተና የማይናቅ ጉዳት እየደረሰባት ነው፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰላምዋና አንድነቷ ጥያቄ ላይ ወድቆአል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
በሀብተ መንፈስ ቅዱስ ወልደን፣ በሀብተ ክህነት ሹመን፣ በመዐርገ ምንኩስና አልቀን በቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ያስቀመጥናቸው ሰዎች በውኑ ‹‹እርስ በርስዋ የምትለያይ ቤት… የሚለውን አምላካዊ አስተምህሮ እንዴት ዘነጉት? ወይስ ድሮውንም ሳያውቁት ነው ኃላፊነቱ የተሰጣቸው? ወይስ ደግሞ ሆን ብለው ቃሉን ቸል ብለውታል? ሁሉም ውሉደ ክህነት ለዚህ መልስ መስጠት ይጠበቅበታል፤ በመልካም አስተዳደርና በቂም በቀል እያሳበቡ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ብሎም ለማፍረስ መሮጥ በማናቸውም መመዘኛ ሚዛን አይደፋም፤ ውሃም አያነሣም፡፡

ችግር ሲኖር በመወያየት በጥበብና በሕግ ማረም እንጂ የጋራ ችግርን ለተወሰነ አካል በመለጠፍና እሱን ብቻ ተጠያቂ በማድረግ ንጹህ መሆን አይቻልም፤ ሁሉም ጓዳው ቢፈተሽ ከዚህ የተለየ ነገር አይገኝም፤ አንድነትንና ሰላምን ግቡ ያደረገ ግምገማን መገምገም፣ መወያየትና መመካከር፣ ሕግንና ሥርዓትን ማእከል አድርጎ መሥራት ተመራጭ መፍትሔ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት አስከፊ በደል ተፈጽሞአል አሁንም አልቆመም፤ ይሁን እንጂ በደል ዛሬ ብቻ የተጀመረ አድርገን አናስብ፤ ይብዛም ይነስ በደል ፊትም ነበረ፤ ዛሬም አለ፤ ነገም የተለየ ነገር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡
በደልን በካሣና በዕርቅ በይቅርታና በምሕረት መዝጋት፣ ተመሳሳይ በደል እንዳይፈጸም አስተማማኝ የሆነ ተቅዋማዊ ሥርዓትን ማበጀት መልካም ፈሊጥ ይሆናል፤ በደልንና ጥፋትን ምክንያት አድርገን እስከ ዘለቄታው መለያየትን መምረጥ ግን ራስን በራስ መጉዳት ይሆናል፤ ስለዚህ ይህ ቅዱስ ጉባኤ በዚህ ዙሪያ በስፋትና በጥልቀት በመወያየት ሁሉንም ሊያስማማ በሚችል መልኩ ወደ ሰላምና ዕርቅ ሊያደርስ የሚችል ስራ መስራት ይኖርበታል፡፡

ብፀዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖስ አባላት!
የማኅበረ ሰባችን ችግር በቤተ ክርስቲያን ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ በሀገር ደረጃ እየቀጠለ ያለው አለመግባባትም ለጠቅላላ ማኅበረ ሰባችን ፈተና ከሆነ ውሎ አድሮአል፤ የቤተ ክርስቲያናችን ፈተና ምንጭ ከሆኑትም አንዱና ዕድል ሰጩ ይህ ሀገራዊ አለመግባባት ነው፤ በዚህ አለመግባባት ምክንያት ገዳማውያን መነኮሳት፤ መምህራን ካህናት ምእመናን አብያተ ክርስቲያናት ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በሰላም ወጥቶ መግባትም አጠራጣሪ ሆኖአል፤ ይህንን ችግር ለመፍታት የሚደረግ ጥረትም ጎልቶ አይታይም፡፡

በመሆኑም ይህ ክሥተት እውን ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት የማንችል ሰዎች ነን ወይ? ለኛስ ከኛ የበለጠ ማን ይመጣልናል? የሚለውን ጥያቄ ልናነሣ ግድ ነው፤ ስለዚህ ለሀገር ህልውናና ድኅነት የሚበጅ ነገር እንዲመጣ ቤተ ክርስቲያን ባላት ሃይማኖታዊና ሰብአዊ ኃላፊነት ጠንክራ መስራት ይጠበቅባታል፤ ከዚህ በተረፈ ይህ ዓቢይ ጉባኤ ወሳኝና ወቅታዊ እንዲሁም ሐዋርያዊና ቀኖናዊ በሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚበጁ ነገሮችን በማየት ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም
ዓመታዊው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በእግዚአብሔር ፈቃድ የተጀመረ መሆኑን በመንፈስ ቅዱስ ስም እናበስራለን ፡፡
መልካም ጉባኤ ያደርግልን!

እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት ፳፩ ቀን !፻0፮ ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/e/wp-content/uploads/441885174_768185728838510_2671012499094900898_n.jpg 850 1280 tc https://eotcp.org/e/wp-content/uploads/logo-en.svg tc2024-05-29 20:59:022025-02-28 21:04:23ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
  • የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው የዐቢይ ጾምን መግባት በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል
  • ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም የጾመ ነነዌ የሰላምና የጸሎት አዋጅ
  • በቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክና የተከናወኑና በታሪክ የሚዘከሩ ዐበይት ተግባራት፤

Archives

  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ቅዱስነታቸው የትንሣኤ በዓል በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል Link to: ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ቅዱስነታቸው የትንሣኤ በዓል በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ቅዱስነታቸው የትንሣኤ በዓል... Link to: ከግንቦት 21 ቀን እስከ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡ Link to: ከግንቦት 21 ቀን እስከ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡ ከግንቦት 21 ቀን እስከ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም የተካሄደው...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top