ግንቦት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
ሁሉን ያደረገ፣ የሚሳነው ነገር የሌለ፣ እግዚአብሔር አምላካችን ቅድስት የሆነችው በዓለ ትንሣኤውን በሰላም አክብረን፣ በርክበ ካህናቱ ዓመታዊ ቅዱስ ጉባኤ ተገናኝተን፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳዮች ለመመልከት ስለሰበሰበን፣ ክብርና ምስጋና ለአምላካችን ይሁን!!
“ወናሁ ወሀብኩክሙ ሥልጣነ ትኪዱ ዲበ ዐቃርብት ወዲበ አራዊተ ምድር ወዲበ ኵሉ ኀይለ ጸላኢ ወአልቦ ዘይነክየክሙ እነሆ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ በጠላትም ኀይል ሁሉ ላይ ሥልጣንን ሰጥቻችኋለሁ የሚጐዳችሁም ምንም የለም” (ሉቃ 10፥19)፡፡

ይህ ሥልጣን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠው ላዕላዊና መለኮታዊ ሥልጣን ነው፤ ሁላችንም እንደምንገነዘበው ይህ ቃል ለሁሉም ሐዋርያት በጥቅል የተሰጠ ሥልጣን እንጂ በተናጠል ለተወሰኑ ሐዋርያት የተሰጠ ሥልጣን አይደለም፤ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተሰጠ ሥልጣን መሆኑን የምናስተውለውም በዚሁ መንፈስ ነው፤ እያንዳንዱ ሐዋርያ በተሰማራበት ግብረ ተልእኮ በኀላፊነት የሚያከናውነው ተግባር እንኳ ቢኖር፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ የመነጨና ለእርሱም ተቃራኒ ያልሆነ እንደሆነም መገንዘብ አያዳግትም፤ ከጌታችን አስተምህሮ የምንገነዘበው በደሙና በቃሉ በምድር ላይ የመሠረታትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጨርሰው ባያጠፏትም የሚታገሏት መናፍስት መኖራቸውን ነው፤ በእባብና በጊንጥ የተመሰሉትም ሰውን በፍቅረ ንዋይ፣ በፍቅረ ሢመትና በክፉ መንፈስ በማለያየት የሚመርዙ እነዚህ እኩያን መናፍስት ናቸው፤ ነገር ግን ምስጋና ለእግዚአብሔር ይድረሰውና እነዚህ እኩያን መናፍስትን ማሸነፍ የሚያስችል ልዩ ሥልጣንና ኀይል ጌታችን ለዚህ ቅዱስ ጉባኤ ሰጥቶአል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ የዘወትር ተግባር ኀይለ ሃይማኖትን፣ ኀይለ ጸሎትን፣ ኀይለ ቃለ ቅዱስ ወንጌልንና ጥብዐተ ልቡናን ተጠቅሞ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እባቡንና ጊንጡን መርዝ አልባ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ጌታችን “ያለ እኔ ምንም ምን ማድረግ አትችሉም” ብሎ እንዳረጋገጠልን፣ ይህንን ሥልጣን በአግባቡ መለማመድና መተግበር የሚቻለው እግዚአብሔርን ይዞ እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ በሃይማኖት ስፍራ ይቅርና በሌላውም በማናቸውም ስፍራ ቢሆን የኀይል ሁሉ ምንጭ እግዚአብሔር ነውና ይህንን ኀይል መጠቀም የግድ ይላል፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን እስካሁን ድረስ በአሸናፊነት የዘለቀችው እባቡንና ጊንጡን በኀይለ እግዚአብሔር ድል እያደረገች ነው፤ አሁንም ይህን ኀይል በአግባቡ ለመጠቀም ከሁሉ በፊት ጽንዐ ሃይማኖትን መያዝ ነው፣ ለልዩ ልዩ ኀላፊ ጥቅም መንበርከክ አይደለም እስከ መጥዎተ ርእስ የሚዘልቅ ራስ መካድን ያስፈልገናል፡፡ ይህ ሲሆን ኀይለ እግዚአብሔር በምልአት ያድርብንና ያን ጊዜ በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ግዑዛን ፍጥረታት ሳይቀሩ ለተሰጠን ሥልጣን ይገዛሉ፡፡

ቀደምት ቅዱሳን አበው በዓመት ሁለት ጊዜ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲካሄድ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ሲደነግጉ እንዲሁ አልነበረም፤ የቤተ ክርስቲያን ሐዊረ ፍኖት ጸዊረ መስቀልና በፈተና የተሞላ በመሆኑ፣ በየጊዜው የሚያጋጥመውን ፈተና በትክክል በማጥናትና በመረዳት በተጠቀሰው ኀይለ ሥልጣን ለመመከት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ነው፤በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያናችን ህልውናዋን ‹ጨርሶ እስከ ማጥፋት የተገዳደሩዋትን ፈተናዎች መሻገር የቻለችው ራስን ከመካድ እስከ መጥዎተ ርእስ በዘለቀ ጽኑ ሃይማኖት ነው፤ በአሁኑ ጊዜ በኀላፊነት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስም እንደቀድሞዎቹ አባቶች እስከ መጥዎተ ርእስ የሚዘልቅ ብርቱ ጽንዐ ሃይማኖትን አንግቦ ቤተ ክርስቲያንን ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር ይጠበቅበታል፡፡

የዘመናችን ፈተና በአብዛኛው እንደቀድሞው በአዋጅ አስነግሮ፣ መሣሪያ ደግኖ፣ ጦር ሰብቆ፣ሰይፍ መዞ ላጥፋችሁ ብሎ የሚመጣብን ላይኖር ይችላል፤ ነገር ግን ውስጥ ውስጡን መርዝ ቀብቶ ላይ ላዩን ደግሞ ማር ለውሶ የሚመጣብንና በጐጂነቱም ከባለፈው የባሰ ሊሆን የሚችል መንፈስ ግን በዓለም እንዳለ በግልጽ እየተስተዋለ ነው፤ እነዚህ በርቀት እየተዋጉን ያሉ እባቦችና ጊንጦች ከእነሱ የበለጠ ረቂቅ ኀይልን ገንዘብ አድርጎ መመከት ያሻል፣ ነጋ ጠባ የምእመናን ፍልሰት፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የምጣኔ ሀብት አያያዝ ጒድለት፣ የቤተ ክርስቲያናችን አጀንዳ ሆነው መቀጠል የለባቸውም፤ “እነሆ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ ሥልጣንን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጎዳችሁም የለም” የሚል እጅግ ረቂቅ ኀይለ ሥልጣን የተሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ የተጠቀሱትን ጉድለቶች ማረም ዐቀበት ሊሆነው አይገባም፡፡

ስለሆነም በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የሚታዩ ወቅታዊ ችግሮች በጥቅል ሲታዩ ከተጠቀሱት ውጭ ስላልሆኑ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ፍልሰተ ምእመናንን የሚገታ፣ መልካም አስተዳደርን የሚያሰፍን፣ ምጣኔ ሀብትን የሚያስጠብቅ አሠራር እውን እንዲያደርግ ሕዝበ ክርስቲያኑ በጒጉት እንደሚጠብቅ ግንዛቤ መወሰድ አለበት፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን ኀላፊነት ድርብ ኀላፊነት እንደመሆኑ መጠን ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያን ህልውና የሚጨነቀውን ያህል፣ ለሀገር ሰላምና አንድነትም የመጨነቅ ኀላፊነት እንዳለበት ሁላችንም እንገነዘባለን፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገራችን እየተከሠተ ከሚገኘው መጠነ ሰፊ ችግር አንጻር፣ በተደጋጋሚ ምሕላና ጸሎት እንዲደረግ፣ የሰላምና የአንድነት አስተምህሮ በስፋት እንዲሰጥ፣ የዕርቅና የኀዲገ በቀል ልምድ እንዲሠርጽ፣ ሁሉም የሃይማኖት አባቶች በዚህ ዙርያ አጥብቀው እንዲሠሩ ከዚህ ቀደም መወሰኑ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ይሁን እንጂ በአክሱምና በሌሎች ጥቂት ገዳማትና አድባራት በዕንባና በልቅሶ የታጀበ ጸሎተ ምሕላ ቢደረግም፣ ከርእሰ ከተማው ከአዲስ አበባ ጀምሮ በብዙ ቦታ ጸሎተ ምሕላው ተጠናክሮ እንዳልተካሄደ ለማወቅ ተችሎአል፡፡ ይህም በመሆኑ መከራው ሊያጥር እንዳልቻለ፣ ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደሆነ እያየን ነው፡፡ እንደ ቀደምት አባቶቻችን ከሕፃን እስከ ሽማግሌ፣ እንስሳትም ሳይቀር፣ ከእህልና ከውኃ ተለይተን በኀዘንና በዕንባ፣ በልቅሶና በንስሓ፣ ፈጣሪያችንን ብንማፀነው ኖሮ ሰላማችንንና አንድታችንን በአጭር ጊዜ እንደሚያረጋገጥልን ጥርጥር የለውም፡፡

ከዚህ አኳያ አሁንም ሁሉን ማድረግ የሚችለው፣ ምንም ምን የሚሳነው የሌለ፣ እግዚአብሔር አምላካችን ብቻ ነውና፣ እሱ በመሠረተልን ስልት “እጃችንን ወደ እግዚአብሔር እንድንዘረጋ” ሕዝቡም ሁሉ፣ ሀገሪቱም በአጠቃላይ “እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር እንድትዘረጋ” እኛም በየሀገረ ስብከታችን ተገኝተን፣ ራሳችን መሪዎች ሆነን ጸሎተ ምሕላውን እንድንመራ፣ ትምህርተ ወንጌሉን እንድንሰጥ፣ ቂም በቀል እንዲከስም ይቅርታ እንዲያብብ ያለማቋረጥ የሽምግልና ሥራን መሥራት ከሁላችን ይጠበቃል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ የሕዝቡ እረኛ እንደመሆኑ መጠን አባቶች ከሀገረ ስብከታቸውና ከሕዝባቸው ሳይለዩ ሕዝቡን ሊመሩ፣ ሊያስተምሩ፣ ሊያስታርቁና ሊያጽናኑ ይገባል፤ ሕዝቡም የአባቶችን ድምፅና ትምህርት፣ ምክርና ተግሣጽ በአክብሮት ተቀብሎ ሊፈጽም ይገባል፤ ሀገርንና ሕዝብን ለማገልገል በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ለግጭትና ለመለያየት በር ከሚከፍቱ ተግባራትና ቅስቀሳዎች ተቈጥበው የሀገር ሰላምና አንድነትን የጋራ አጀንዳ አድርገው፣ ችግሮችን ሁሉ በውይይትና በውይይት ብቻ ለመፍታት በቊርጠኝነት እንዲሠሩ፣ ኀይለ ቃል መጠቀምንና ስም ማጥፋትን እንዲያቆሙ፣ በዚህ አጋጣሚ በኀያሉ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

የዘንድሮ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሚከናወነው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለዓመታት በአቤቱታ የደከመባቸውንና በጽ/ቤታችን አጠገብ የሚገኙትን ሁለት ታላላቅና ሁለት መለስተኛ የቤተ ክርስቲያናችን ሕንጻዎች፣ የኤፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መመለሳቸውን ባበሠሩንና ባረጋገጡልን ማግስት በመሆኑ፣ ጉባኤውን ከሌላው ጊዜ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የቤተ ክርስቲያናችንን የዓመታት አቤቱታ ከልብ አጢነውና ተቀብለው ሕንጻዎቻችን እንዲመለሡልን ያደረጉ እና ጥያቄያችንን የመለሱ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንንና መንግሥታችንን በቤተ ክርስቲያናችን ስም ከልብ እናመሰግናቸዋለን፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና መላው ሕዝበ ክርስቲያንም እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን፡፡

በመጨረሻም፡ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና፣ እንደዚሁም ስለ ሀገራችን ሰላምና አንድነት በየዓመቱ ሁለት ጊዜ እየተሰበሰበ በመገምገም ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎችን የሚያስተላልፈው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬ ግንቦት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በጸሎት የተከፈተ መሆኑን እናበሥራለን፡፡ እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ ይቀድስ እንደዚሁም ኢትዮጵያ ሀገራችንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡