• Amharic  
  • English 
  • Home
  • Papal Messages
  • Biography
  • Patriarchs
  • Contact
  • Menu Menu

የመስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ዘመን መለወጫ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

September 11, 2018

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ፤

ምድራችንን በልምላሜ፣ በአበባ፣ በእሸት በአጠቃላይ በፍጹም በረከት እያደሰ ዘመንን በዘመን እየተካ ጸጋውን ያበዛልን እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከሁለት ሺሕ ዐሥር ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማርቆስ ወደ ሁለት ሺሕ ዐሥራ አንድ ዓመተ ምሕረት ዘመነ ሉቃስ በሰላም አደረሳችሁ!!

“ሐድሱ መንፈሰ ልብክሙ፤የልቡናችሁን ዕውቀት አድሱ፤እግዚአብሔር ያደሰውን አዲሱን ሰውነት በእውነት በቅንነትና በንጽሕና ልበሱት፤ ሐሰትን ተዉአት፣ ሁላችሁም ከወንድሞቻችሁ ጋር እውነትን ተናገሩ፤ እኛ አንድ አካል ነንና” (ኤፌ 4፥23)፡፡

እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ከለገሳቸው ስጦታዎች አንዱና ዋነኛው የመታደስ ጸጋ ነው፤ እግዚአብሔር፣ እያረጀ እንደገናም እየታደሰ የሚኖር የግዙፋን ፍጥረታት ዓለምና እርጅና የማይነካው የመንፈሳውያን ፍጥረታት ዓለም በድምሩ ሁለት ዐይነት ዓለም እንደፈጠረ ይታወቃል፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከግዙፋኑ ወገን ቢሆንም ለተወሰነ ጊዜ በግዙፉ ዓለም ከቆየ በኋላ ታድሶ ወደ ረቂቁ መንፈሳዊ ዓለም በመሻገር ያለ እርጅና ለዘለዓለም ጸንቶ ለሚኖር ሕይወት የታደለ ፍጡር እንደነበረ በመጽሐፍም በተግባርም የተረጋገጠ ነው፤ ይህ ዐይነቱ የሰው ዕድል በኀጢአት ምክንያት ለጊዜው ቢደናቀፍም የተዘጋጀልንን ጸጋ በውል እንድናውቅ እነ ሄኖክና እነ ኤልያስ የመሳሰሉትን ሞትና እርጅና ወደ ሌለበት ዓለም በመውሰድ በተግባር አሳይቶናል፡፡

የሰው ልጅ የመታደስ ጸጋ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እንደገና እንደሚቀጥል በነቢያቱ በኩል ተስፋው ሲገለጽ ከቆየ በኋላ፣በባሕርይ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ዳግመኛ ዕድሉ ተሰጥቶን እነሆ ሙሉ በሙሉ ታድሰን ወደማያረጀው መንፈሳዊ ዓለም ለመሸጋገር የጌታ ቀንን እየጠበቅን እንገኛለን፡፡ የሰው ልጅ በአጠቃላይ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ታሪክ ሁለት ታላላቅ ነገሮች አጋጥመውታል፤ እነሱም ብልየትና ሕዳሴ ወይም ማርጀትና መታደስ ናቸው፤ እነዚህ ሁለቱ በዘመን ውስጥ ያለፉ በመሆናቸው ዘመነ ብሉይ፣ ዘመነ ሐዲስ ተብለው ይታወቃሉ፤ ዘመነ ብሉይ የሚባለው ከአዳም ውድቀት ጀምሮ እስከ ልደተ ክርስቶስ ያለው ሲሆን፣ ከልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ያለው ደግሞ ዘመነ ሐዲስ ይባላል፤ ይህ ዘመን መጨረሻ የሌለው ሐዲስ ሕይወት የተገኘበት ስለሆነ እስከ የለውም፤ከዚህ አንጻር ከልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ባለው ዘመን የምንኖር ሁላችን በመታደስ ዘመን ውስጥ የምንገኝ ስለሆን ጽዉዓን ኅሩያን ማለትም የተጠሩ የተመረጡ እንባላለን፤ ዘመኑም ዓመተ ምሕረት ይባላል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፡ በፀሓይ አቈጣጠር መስከረም አንድ ቀን በየዓመቱ የምናከብረው የርእሰ ዐውደ ዓመት ወይም የዓመት ዙር መነሻ ራስ በዓል በውስጡ የተፈጥሮ፣ የብሉይና የሐዲስ ኪዳናት ምሥጢርን አምቆ የያዘ ነው፡፡ ከጥንተ ተፈጥሮ አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ የቀደሙ አበው እነ አዳም፣ እነ ኖኅ ከዚያም ጥንታውያን የምሥራቅ አገሮች በተለይም ከለዳውያን፣ ግብጻውያንና አይሁዳውያን ጭምር ይከተሉት የነበረ ነው፤የኢትዮጵያ ርእሰ ዐውደ ዓመት፣ በጨረቃ አቈጣጠር ከመሆኑ በቀር ዛሬ ድረስ በእስራኤላውያን ተጠብቆ የሚኖር ከሁሉም የዘመን መለወጫ ይልቅ የዕድሜ ባለ ጸጋ የሆነ ርእሰ ዐውደ ዓመት መሆኑ ለጥንታዊነቱ በቂ ማስረጃ ነው ፤ ከዚህም ጋር ፀሓይና ጨረቃ በየዐሥራ ዘጠኙ ዓመት ዑደታቸውን ጳጕሜን አምስት ቀን እያጠናቀቁ መስከረም አንድ ቀን ሁለቱም ማለትም ፀሓይና ጨረቃ በአንድ ቀን ከአንድ የጊዜ መነሻ ነጥብ አንድ ላይ መነሣታቸው ይህ ቀን እነሱ የተፈጠሩበት ቀን ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ነው፤ የቤተ ክርስቲያናችን የቊጥር መጽሐፍም ዐሥራ ዘጠነኛው ዐውደ አበቅቴ፣ ፀሓይና ጨረቃ መንገዳቸውን ፈጽመው በተፈጠሩበት ኆኅት ተራክቦ ያደርጉበታል በማለት ይህንን መሠረተ ሐሳብ ያጠናክራል፡፡
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ መስከረም አንድ ቀን ላይ እንዲሆን መደረጉ ከቀደምት አበው ትውፊትና የመስከረም አንድ ቀን ዐውደ አበቅቴ የፀሓይና የጨረቃ መነሻና መድረሻ ሆኖ ከመገኘት አንጻር የዘመን መነሻ ቊጥር የተጀመረው መስከረም አንድ ቀን ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ ስለተያዘበት እንደሆነ በዚህ እናስተውላለን፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የዘመነ ብሉይ ማብቃት የዘመነ ሐዲስ መግባት ያበሠረ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ በመሆኑ፣ ከመስከረም አንድ ቀን በፊት የተጠናቀቀው አሮጌው ዘመን እንደ ዘመነ ብሉይ፣ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ የምንቀበለው አዲሱ ዓመት እንደ ዘመነ ሐዲስ በአንድ ወገን፣የአሮጌውን ዘመንና የሐዲሱን ዘመን መለያ ርእሰ ዐውደ ዓመትና የዘመነ ብሉይና የዘመነ ሐዲስ መለያ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በሌላ ወገን በምሥጢራዊ ንጽጽር ተመሥጥሮ ርእሰ ዐውደ ዓመትና ቅዱስ ዮሐንስ አንድ ላይ እንዲከበሩ ተደርጎአል፤ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ይህንን አስመልክቶ ሲናገር “ውስተ ርእሰ ዐውደ ዓመት ተጽሕፈ ተዝካርከ፤ መታሰቢያህ በርእሰ ዐውደ ዓመት ላይ እንዲከበር ተጻፈ” ብሎአል፡፡ ዋናው መልእክት ርእሰ ዐውደ ዓመት የአሮጌውን ዘመን ማብቃት የሐዲሱን ዘመን መግባት በማብሠር አዋጅ ነጋሪ እንደሆነ ሁሉ፣ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስም የብሉይ ኪዳንን ማብቃት የሐዲስ ኪዳንን መግባት በማብሠር አዋጅ ነጋሪ እንደሆነ በማነፃጸር በንስሓ መታደስን ይሰበክበታል፡፡ እንዲሁም አሮጌው ዘመን ከኅልፈተ ዓለም፣ አዲሱ ዘመን ከአዲሱ የመንግሥተ ሰማያት ዘመን፣ ርእሰ ዐውደ ዓመት ከዕለተ ምጽአት በንጽጽር ተመሥጥሮበት የጌታ ምጽአትና የመንግሥተ ሰማያት አዲስ ዘመን ይታሰብበታል፡፡

ከዚህም ሌላ የሀገራችን ሥነ ተፈጥሮ እንደሚያሳየን ከመስከረም አንድ ቀን በፊት ያለው ወርኀ ክረምት ነጐድጓድ፣ መብረቅ፣ የነፋስና የዝናም ውሽንፍር፣ የደፈረሰ ጐርፍ፣ የጉምና የደመና ጽልመት የሚነግሥበት፣ እህሉ አልቆ ሰው ለምግብ እጥረት የሚጋለጥበት ወቅት ነው፡፡ ከመስከረም አንድ ቀን በኋላ ግን ሁሉም ነገር የሚታደስበትና የሚለወጥበት ነው፤ ማለትም የምግብ ዕጥረቱ በአዲስ እሸት የሚተካበት፣ ጨለማው ደመናው ጉሙ መብረቁ ነጐድጓዱ ቦታውን የሚለቅበት፣ በምትኩ ደግሞ የፀሓይ የጨረቃና የከዋክብት ብርሃናት በጠራ ሰማይ ላይ ፍንትው ብለው ደማቅ ብርሃናቸውን የሚያሳዩበት፣ በየዋሻውና በየቋጥኙ ተወሽቀው የነበሩ አእዋፍና ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ እንደልባቸው ወዲያ ወዲህ እየበረሩ በደስታ የሚዘምሩበት፣ ድፍርሱ የጐርፍ ውኃ ወለል ብሎ የሚጠራበት በአጠቃላይ የሥነ ፍጥረት ውበት የሚታደስበት ወቅት፣ ከመስከረም አንድ ቀን በኋላ ነው፤ ከዚህ አኳያ በመንፈስ ቅዱስ የተሟሟቁ ፣ በዕውቀት የተራቀቁ ቀደምት ኢትዮጵያውያን አበው የወርኀ ክረምቱን አስጨናቂ ሥነ ተፈጥሮ የዘመነ ብሉይ መከራና ፍዳ ተምሳሌት አድርገው አመሥጥረውታል፣ በሌላ በኩል ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ያለውን የሥነ ፍጥረት መታደስ የዘመነ ሐዲስ ተምሳሌት አድርገው በማመሥጠርና በመቀመር በሥነ ፍጥረት ውበት ላይ የመንፈስ ውበትን አላብሰውታል፤ ይህ እጅግ ውብና ድንቅ የሆነ መንፈሳዊና ተፈጥሮኣዊ ሀብተ አበው በሚገባ ጠብቆ ለትውልደ ትውልድ ማስተላለፍ ከነፍስ ወከፍ ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፡ ኢትዮጵያዊው የዘመን መለወጫ ርእሰ ዐውደ ዓመት በዋናነት የሚያስተምረን ትምህርት መታደስን፣ መለወጥን፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መውጣትን፣ ከድህነት ወደ ልማት መሸጋገርን፣ ከማጣት ወደ ብልጽግና መራመድን ነው፣ አዲሱ ዓመት ስንፍናን በትጋት፣አለማወቅን በዕውቀት የምንለውጥበትን፣ ካለፈው ዓመት ይልቅ እጥፍ ድርብ የሆነ ሥራ በመሥራት ምርታችንን በከፍተኛ ሁኔታ የምናሳድግበትን አዲስ መንፈስ ሰንቀን ለተሻለ ልማትና እድገት የምንነሣበት መሆን ይኖርበታል፡፡ ታድያ ይህን ሁሉ እውን ማድረግ የምንችለው ከሁሉ በላይ የሆነውን ሀብተ ፍቅር በእያንዳንዳችን የልቡና ኪስ ሲሞላ ነው፡፡ ፍቅር የሁሉም መሠረት ነው፤ ፍቅር ሰላምን ይወልዳል፣ ሰላም አንድነትን ይወልዳል፣ አንድነት ጒልበትን፣ ልማትን፣ እድገትን፣ መታፈርን፣ መፈራትን፣ መከበርን፣ መደመጥን ይወልዳል፤ እንደሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ የቀደመውን ደማቅ ገናንነትዋን መልሶ ለማረጋገጥ ሲሉ ውድ ልጆቿ ለለውጥ ሲባክኑ እነሆ ከስድሳ ዓመታት በላይ ተቆጥሮአል፡፡ ነገር ግን ከሚፈለገው ደረጃ ላይ ሳይደረስ ነገሮች እየተወሳሰቡ ከለውጡ ይልቅ ጥፋት እየቀደመ አሁን ላለንበት ደረጃ ደርሰናል፡፡ ይህ ለምን ሆነ ቢባል ዋና ምክንያት ሆኖ የሚታየው በሀገሪቱ ውስጥ ለዘመናት በበለጸገ ቅዱስ ባህል የተገነባውን የሕዝቡን መንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ ርእዮት ተከትሎ እርሱን ማእከል ባደረገ የእድገትና የለውጥ አስተዳደር ማስፈን ሲቻል በእሱ ፈንታ የውጭ ርእዮትን እንዳለ ተቀብሎ በሕዝቡ ጫንቃ ላይ በግድ ለመጫን የሚደረገው የተሳሳተ አካሄድ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡ ለውጡ ሲጀመር ይቅር ይቅር በመባባል ወደዋናው የለውጥ ተግባር በመሸጋገር ፈንታ የበቀል እርምጃ ወደ መውሰድ ይዞራል፤ ከዚህም የተነሣ መግባባት ስላልተቻለ የሀገር አንድነትና የዜጎች ደኅንነት ሥጋት ላይ እየወደቀ የሀገሪቱና የዜጎችዋ ዕጣ ፈንታ ዋስትና የለሽ እየሆነ መቀጠል ግድ ሆኖበታል፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ ከሦስት ሺሕ ዘመናት በላይ የእግዚአብሔር የመመለኪያ ቤተ መቅደስ የታቦቱና የመስቀሉ ታማኝ መንበር በሆነች ኢትዮጵያ ስመ እግዚአብሔርን እየጠሩና እግዚአብሔርን እየፈሩ ሕዝቡን መምራት የሚያስችል እምነትና ድፍረት መታጣቱ ነገሩ ሁሉ የኋልዮሽ እንዲመለስና ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ አሁንም ከሁሉ በላይ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚበጀው እግዚአብሔርንና ሕዝቡን ማእከል አድርጎ መሥራት ነው፤ እግዚአብሔርን ስናደምጥ ይቅርታ እንጂ መለያየት፣ የለም መጠራጠርና አለመተማመን ቦታ አይኖራቸውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ እንደ ካሁን ቀደሞቹ ፈተና እንዳይገጥመው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለፍቅርና ለይቅርታ ሰፊውን ቦታ ይስጥ፣ የኀይለ ቃላት ውርወራን ያቁም፤ ኀይለ ቃልን የምንጠቀም ከሆነ መቃቃርን ያስከትላል፣ መቃቃር ጥላቻን ያሳድጋል፣ ጥላቻ ግጭትን ይወልዳል፤ ስለዚህ የሚወረወሩ ኀይለ ቃላት ወገንን አስከፍተው ዋጋ እንዳያስከፍሉን ከአዲሱ ዘመን መለወጫ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገድለን እንቅበራቸው፤ የቀደመውን ግድፈት ሁሉ ለታሪክ ትተን ለቀጣይዋ ኢትዮጵያ አንድነትና ለዜጎችዋ ደኅነንት መልካም የሆነውን ማሰብ የዘወትር ተግባራችን ይሁን፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ለሀገር አንድነትና ለዜጎች ደኅንነት ቅድሚያ እየሰጣችሁ በሰላምና በሰላም ብቻ መንገድ እየተጓዛችሁ ለሀገር የሚበጀውን በማድረግ ኀላፊነታችሁን እንድትወጡ፣ የጥበብ ባለሙያዎች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን ሁላችሁም የቃላት ውርወራን አቁማችሁ ፍቅርንና ይቅርታን፣ የዜጎች ደኅንነትንና የሀገር አንድነትን እንድትሰብኩ በዚህ አጋጣሚ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም፡ ባለፈው ዓመት በሀገራችን የታዩ የሰላምና የአንድነት ጠንቅ የሆኑ ግድፈቶች እንደአሮጌው ዘመን አሳልፈንና ፋይላቸውን ዘግተን በአዲስ ፍቅር፣ በይቅርታ፣ በአንድነት የሕዝቡን መንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ ነባር ዕሴትን በመጠበቅ እግዚአብሔርን በመፍራትና እሱን የበላይ ዳኛ አድርጎ በመቀበል የሀገር አንድነትንና የዜጎችን ደኅንነት በማስጠበቅ አዲሱን ዘመን በፍጹም መታደስ እንድንቀበለው አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡ አዲሱ ዘመን የተባረከና የተቀደሰ የሰላም፣ የፍቅናር የይቅርታ ዘመን ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/e/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc3 https://eotcp.org/e/wp-content/uploads/logo-en.svg tc32018-09-11 13:41:162025-01-28 13:42:35የመስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ዘመን መለወጫ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
  • የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው የዐቢይ ጾምን መግባት በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል
  • ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም የጾመ ነነዌ የሰላምና የጸሎት አዋጅ
  • በቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክና የተከናወኑና በታሪክ የሚዘከሩ ዐበይት ተግባራት፤

Archives

  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በጣና በለስና በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጽሞአል በተባለውን የሰው መግደልና መፈናቀል እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጥተዋል Link to: ነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በጣና በለስና በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጽሞአል በተባለውን የሰው መግደልና መፈናቀል እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጥተዋል ነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ... Link to: መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል ሐዋርያዊ መልእክት Link to: መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል ሐዋርያዊ መልእክት መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top