ከጥቅምት 12 እስከ 26 ቀን 2007 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ፤ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 164 በተደነገገው መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የዘንድሮውን መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያካሂድ ሰንብቷል፡፡ በዚሁ መሠረት የመክፈቻው ሥርዐተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከበዓሉ ዋዜማ ከጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 26 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ለ15 ቀናት ያህል ባደረገው ጉባኤ ጠቀሜታ ባላቸው የአጀንዳ ነጥቦች ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡ ከተላለፉት በርካታ ውሳኔዎች መካከልም ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. የጥቅምቱ 2007 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቅዱስ ፓትርያርክ የመግቢያ ንግግር ከተከፈተ በኋላ ሠላሳ ሦስተኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ያቀረበው የጋራ መግለጫ የ2007 የበጀት ዓመት የሥራ መመሪያ ሆኖ እንዲሠራበት ወስኗል፡፡

2. በቅዱስ ሲኖዶስ የተሠየመው አርቃቂ ኮሚቴ ያቀረበው ረቂቅ ሕገ ቤተ ክርስቲያን፤ ለምልአተ ጉባኤ ቀርቦ ገጽ በገጽ ከተነበበና እርማት ከተደረገ በኋላ ይኸው ሕግ እንዲሠራበት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ አጽድቋል፡፡

3. የግንባታው ሥራ እየተካሄደ ለሚገኘው ለታላቁ የዐባይ ሕዳሴ ግድብ ማከናወኛ አገልግሎት ይውል ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲል ከሃያ ሦስት ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማድረጓ የሚታወስ ነው፤ አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከየአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች የተገኘውን በድምሩ ብር 16,403,091.01 (ዐሥራ ስድስት ሚሊዮን አራት መቶ ሦስት ሺህ ዘጠና አንድ ብር ከዜሮ አንድ ሳንቲም) ገቢ ያደረግን ስለሆነ ይኸው ታውቆ የሕዳሴው ግድብ ለሀገራችን የእድገት ታሪክ ምዕራፍ ከፋች ይሆናል ተብሎ ስለታመነበት ሁሉም ኅብረተሰብ ጠቀሜታውን ከወዲሁ በበለጠ በመረዳት አስፈላጊውን ሁሉ በመፈጸምና በማስፈጸም እንዲረባረብ በዚህ አጋጣሚ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

4. በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን በተለይም በምዕራብ አፍሪካ ዙሪያ እየቀሠፈ የሚታየው ‹‹ኢቮላ›› በመባል የሚታወቀው አዲስ ቀሣፊ በሽታ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንዳይገባና ከዓለም ዙሪያ እንዲጠፋ ከወዲሁ መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ ኅብረተሰቡ በመከላከሉ ረገድ ብርቱ ጥንቃቄ ያደርግ ዘንድ በመገናኛ ብዙኃን ሲነገር ይደመጣል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም የኅብረተሰቡ አገልጋይ ከመሆኗ አንጻር የበኩሏን ድርሻ ልትወጣ የሚገባት ስለሆነ፤ በየአህጉረ ስብከቱ በየአንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ምሕላ ይደረግ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያን ሰጥቷል፡፡

5. በጀትን በተመለከተ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለ2007 ዓ.ም. ተጠንቶ የቀረበውን በጀት አጽድቋል፡፡

6. የሰዎች ሕገ ወጥ ዝውውር የሀገርን ክብር የሚፈታተን ተተኪ ትውልድን የሚያሳጣ ድርጊት በመሆኑ ይህን ሕገ ወጥ አሠራር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትኲረት ሊሰጥበት እንደሚገባ እየተነገረ ነው፤ቤተ ክርስቲያኒቱም ቅድሚያ ለሀገርና ለወገን ክብር በመስጠት ይህን በተመለከተ በማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረት ሁሉ አስፈላጊው ትምህርት እንዲሰጥ ወስኗል፡፡

7. በጋምቤላና በቤንች ማጂ ክልል በነዋሪው ሕዝብ መካከል ስለተከሠተው አለመግባባት ጉዳይ ምልአተ ጉባኤው ተነጋግሮ ለሀገሪቱ ሰላም ለልማትና ለእድገት ዕንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮች እንዲወገዱ፣ ኅብረተሰቡ በሰላምና በመግባባት እንዲኖር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

8. ከሀገር ውጭ ከሚገኙ የሃይማኖት አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው ዕርቀ ሰላም ተጠናክሮ መቀጠሉ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገር የሚበጅ መሆኑ ስለታመነበት አሁንም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስለ ቀጣዩ ሰላም በሰፊው ተነጋግሮ በቤተ ክርስቲያናችን በኩል የሰላሙ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጠል ጉባኤው ወስኗል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ውይይቱን በመቀጠል፤ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ በማስጠበቅ፤
– በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር አመራር ሰጭነት የተጀመሩት ልዩ ልዩ የልማት ድርጅቶች ለውጤት በቅተው አገልግሎትን እንዲሰጡ ለማስቻል፤
– በሀገር ውስጥና በውጭው አህጉረ ስብከት ተመድበው በሚሠሩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አማካይነት የተካሄደውን ሐዋርያዊ ተግባር በመገምገም፤
– ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያንና አረጋውያት የሚጦሩበት፤ አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናት እየተማሩ የሚያድጉበት የምግባረ ሠናይ ተቋማት በየአህጉረ ስብከቱ እንዲቋቋሙ ለማድረግ፤
– ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ እድገትና ልማት የሚበጀውን ሁሉ መፈጸም የሚያስችል መመሪያን ሰጥቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ሕዝባችንን ሀገራችንን ይባርክ፤ ለሀገራችን ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን ይስጥልን፤